የቡርቃ ዝምታ፡ የአቶ አዲሱ አረጋ ትችት እና የተስፋዬ ገብረዓብ ምላሽ

አቶ አዲሱ እና ተስፋዬ Image copyright Facebook
አጭር የምስል መግለጫ አቶ አዲሱ እና ተስፋዬ

ከቀናት በፊት የኦሮሞ እና የአማራ ሕዝቦች የትስስር መድረክ ተብሎ በተዘጋጀው መድረክ ላይ የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዲፒ) ጽሕፈት ቤት ኃላፊ የሆኑት አቶ አዲሱ አረጋ የሰጡት አስተያየት በማኀበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ዘንድ መነጋገሪያ ሆኖ ቆይቷል።

በመድረኩ ላይ አቶ አዲሱ፤ የልሂቃን እና የፖለቲከኞች የሃሰት ትርክት የአማራ እና የኦሮሞ ሕዝብን ለመከፋፈል ጥረት አድርጓል ብለዋል።

"ምንም ከህዝብ የሚደበቅ ነገር አይኖርም" አዲሱ የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሽመልስ አብዲሳ

አቶ አዲሱ ''በልሂቃን እና በፖለቲከኞች የሃሰት ትርክት አማራ እና ኦሮሞ እሳት እና ጭድ ናቸው የተባለው የተዛባ አስተሳሰብ ነው። . . . እሳት እና ጭድ አይደለንም። አንዱን በዳይ ሌላውን ተበዳይ አድርጎ ለማቅረብ ከፍተኛ ገንዘብ ወጥቶ፤ በጀት ተመድቦ፤ ሆነ ተብሎ ሁለቱን ሕዝብ ከፋፍሎ በጽናት እንዳይቆሙ ለማድረግም በርካታ ሥራዎች ሲሰሩ ነበር። ለአብነትም 'የቡርቃ ዝመታ' የተሰኘውን የተስፋዬ ገብረዓብን መጽሐፍ መጥቀስ ይቻላል'' ሲሉ ተደምጠዋል።

አቶ አዲሱ እሁድ ሚያዝያ 13፣ 2011 ዓ. ም. ይህን ማለታቸውን ተከትሎ በርካታ የወቀሳ እና የድጋፍ ሃሳቦችም ተሰንዝረዋል።

ኦሮሚያ በአዲስ አበባ በምታገኘው ልዩ ጥቅም ላይ ሊመክር የነበረው ስብሰባ ተበተነ

አቶ አዲሱ ንግግሩን ባደረጉበት ምሽት እንዲሁም ትላንትናም (ሚያዝያ 14፣ 2011ዓ. ም.) በፌስበክ ገጻቸው ላይ '' 'የቡርቃ ዝምታ' መጽሐፍን በተመለከተ የሰጠሁት አስተያየት ብዙዎችን እንዳላስደሰተ ተረድቻለሁ። እኔ ማንሳት የፈለኩት ሃሳብ ጽሑፎች የሚቀርቡበት እና የሚተረኩበት መንገድ፤ ሕዝብ ከጨቋኝ ስርዓት ስር ለመውጣት የታገለውን፤ በሕዝቦች መካከል የተከሰተ ግጭት አድርጎ ማቅረብ በሕዝቦች የወንድማማችነት ግንኙነት ላይ ተጽእኖ ያሳድራል ለማለት ፈልጌ ነው።'' በማለት የይቅርታ አድርጉልኝ መልዕክት አስፍረዋል።

በጉዳዩ ላይ አቶ አዲሱ ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ '' 'የቡርቃ ዝመታ' የተሰኘው መጽሐፍ ሙሉ በሙሉ ውሸት ነው ሳይሆን ያልኩት፤ ታሪኩ የተጻፈበት እና የተተረከበት መንገድ የሕዝቦችን ወንድማማችነት ግምት ውስጥ በሚያስገባ መልኩ አይደለም ነው'' ብለዋል።

አቶ አዲሱ ለቢቢሲ ሲናገሩ፤ ''የተስፋዬ ገብረዓብ መጽሐፍ ብቻ ሳይሆን፤ የታሪክ መጽሐፎችም [ሌሎች] በድጋሚ መታየት አለባቸው። መድረኩ ትልቅ ስለነበር ሃሳቤን በዝርዝር ለማስረዳት በቂ ጊዜ አላገኘሁም። እንዲህ አነጋጋሪ ሊሆን የሚችል ጉዳይ እንደምሳሌ አድርጌ ማቅረብም አልነበረብኝም። ወደፊትም ከዚህ ትምህርት እወስዳለሁ። ሕዝቡም ይህን እንዲረዳልኝ እፈልጋለሁ'' ብለዋል።

አቶ አዲሱ በመጽሐፉ ላይ የሰነዘሩት ትችት እንደ አንድ መጽሐፉን እንዳነበበ ግለሰብ መሆኑንም ጨምረው ተናግረዋል።

ኦዲፒ፡ ኦነግ እንደ አዲስ ጦር መልምሎ እያሰለጠነ ነው

የመጽሐፉ ደራሲ ተስፋዬ ገብረዓብ አቶ አዲሱ የተናገሩት ስህተት ነው ይላል። በኦሮሞ እና በአማራ ሕዝብ መካከል ግጭት ካለ የግጭቱ መንስዔ 'የቡርቃ ዝምታ' ሊሆን አይችልም ብሎም ተናገሯል።

ተስፋዬ ''ችግር ካለ የችግሩ መንስኤ እኔ ልሆን አልችልም። ችግሩ ምንድነው? የሚለውን አጣርቶ መፍትሄ መስጠት እንጂ፤ እንዲህ አይነት ማጭበርበር ወንዝ አያሻግርም'' ብሏል።

አቶ አዲሱ ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ ደራሲው መጽሐፉን ሲጽፍ የኢህአዴግ አመራር ነበር ብለው፤ ''መጽሐፉ በኢህዴአግ ውስጥ እጅጉን ይወደስ ነበር። መጽሐፉ ይወደስ የነበረው ደግሞ ለኦሮሞ ህዝብ ተቆርቋሪ በመሆን እንዳልሆነ አውቃለሁ'' ይላሉ።

«ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለ በረከት አናግረውናል» የአቶ በረከት ስምዖን ባለቤት

መጽሐፉ በስፋት እንዲሰራጭ የሚፈልጉ ግለሰቦች የገንዘብ ወጪ ሲሸፍኑ ማለትም 'ስፖንሰር' ሲያደርጉ እንደነበርም አውቃለሁ ሲሉም አቶ አዲሱ ተናግረዋል።

ደራሲው ተስፋዬ በበኩሉ ''ስሜን ለማጥቆር በማሰብ ወያኔ ይለው የነበረውን ነው መልሶ እየተናገረ ያለው።'' በማለት የአቶ አዲሱን ክስ ያጣጥላል።

''የመንግሥት አካል ሆኖ ይህን መናገሩ በጣም ቢያሳዝነኝም፤ እሱ የተናገረው የመንግሥትን አቋም ያንጸባርቃል ብዬ አላምንም። ይህ መጽሐፍ ታትሞ ሲወጣ ለኪሳራ የተዳረገው ወያኔ ነው። ስለዚህ ይህን መጽሐፍ ያሳተመው ወያኔ ነው ማለት አይቻልም።'' ሲል ተስፋዬ መከራከሪያውን ያቀርባል።

ደራሲ ተስፋዬ በዚህ መጽሐፍ ሳቢያ ለስደት መዳረጉንና መጽሐፉም እየተፈለገ እንዲቃጠል ይደረግ እንደነበር ያስታውሳል።

ተያያዥ ርዕሶች