ከ27 ዓመታት በኋላ ከ'ኮማ' የነቃችው ሴት

ሙኒራ አብደላ ከ27 ዓመታት በኋለ ከኮማ ነቅታለች

የፎቶው ባለመብት, Science Photo Library

የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ዜግነት ያላት አንዲት ሴት በአውሮፓውያኑ 1991 ላይ ባጋጠማት የመኪና አደጋ ኮማ ውስጥ ገብታ (ዘለግ ላለ ጊዜ አእምሮን ስቶ መቆየት) ቢሆንም ተአምራዊ በተባለ ሁኔታ ከ27 ዓመታት በኋላ መንቃቷ ተሰምቷል።

ሙኒራ አብደላ የመኪና አደጋው ሲያጋጥማት የ32 ዓመት ወጣት የነበረች ሲሆን በወቅቱ እሷ ትጓዝበት የነበረው ተሽከርካሪ ከሕዝብ ማመላለሻ መኪና ጋር ተጋጭቶ ከባድ የጭንቅላት ጉዳት አጋጥሟት ነበር።

አደጋው ሲደርስ ወንድ ልጇን ከትምህርት ቤት ለመቀበል እየሄደች ነበር።

ኦማር ዊቤር እናቱ የመኪና አደጋ አጋጥሟት ኮማ ውስጥ ስትገባ ገና የአራት ዓመት ጨቅላ ነበር። ተሽከርካሪው ውስጥ አብሯት ተቀምጦም ነበር። ነገር ግን እሱ በአደጋው ምንም ጉዳት ሳይደርስበት መትረፍ ችሏል።

''እስከዛሬ ድረስ ተስፋ አልቆረጥኩም። አንድ ቀን እንደምትነቃ አስብ ነበር። የእናቴን ታሪክ ማጋራት የፈለግኩትም ሰዎች በምንም አይነት ሁኔታ ውስጥ ቢሆኑ ተስፋ መቁረጥ እንደሌለባቸው ለማስተማር በማሰብ ነው'' ይላል ኦማር።

''እናቴ አደጋው በደረሰበት ወቅት እኔን ከአደጋው ለመከላከል በማሰብ ጥብቅ አድርጋ አቅፋኝ ነበር'' ሲልም ተናግሯል።

ሙኒራ አብደላ የደረሰባት ጉዳት እጅግ ከፍተኛ ስለነበር የተሻለ ህክምና እንድታገኝ በሚል ወደ እንግሊዝ መዲና ለንደን ተወስዳ ነበር። ነገር ግን ምንም አይነት ለውጥ ማሳየት ስላልቻለች ወደ ሀገሯ እንድትመለስ ተደረገ።

በመጨረሻም በ2017 ከአቡዳቢ መንግሥት በተገኘ ድጋፍ ወደ ጀርመን ሄዳ ህክምናዋን እንድትከታተል ተደረገ። ጀርመን በነበረችበት ወቅትም የተለያዩ ህክናዎችን ብታደርግም ይሄ ነው የሚባል መሻሻል ሳይታይበት ቀርቷል።

ወደ ጀርመን ከተወሰደች ከአንድ ዓመት በኋላ ኦማር ከህክምና ባለሙያዎች ጋር አለመግባባት ውስጥ ይገባና ጭቅጭቅ ይነሳል። በዚህ መሃል እናቱ አንዳንድ የእንቅስቃሴ ምልክቶችን አሳየች።

'' ከህክምና ባለሙያዎቹ ጋር አለመግባባት ሲፈጠር እኔ አደጋ ውስጥ እንደሆንኩ ተሰምቷታል። ለእዛም ነው እንቅስቃሴ ያደረገችው'' ሲል ኦማር ይናገራል።

የነቃችበትን ቅጽበት ሲያስታውስም፤ ''ከሦስት ቀናት በኋላ የሆነ ሰው ስሜን ሲጠራ ከእንቅልፌ ነቃሁ። እናቴ ነበረች ስሜን የጠራችው። በደስታ ያደረግኩትን አላውቅም። ያንን ቀን ለብዙ ዓመታት ስጠብቀው ነበር። መጀመሪያ ያወጣችው ቃል ደግሞ የእኔ ስም ነው።''

ሙኒራ አብደላ አሁን 59 ዓመቷ ነው።

ወደትውልድ ከተማዋ አቡዳቢ የተመለሰች ሲሆን፤ የማገገሚያና የአጥንት እንዲሁም የሙሉ ሰውነት ማጠንከሪያ እንቅስቃሴዎችን በማድረግ ላይ ትገኛለች።