በቻይና የተደረሱት ስምምነቶች የትኞቹ ናቸው?

ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ እና ፕሬዝደንት ዢ ዢንፒንግ

የፎቶው ባለመብት, PM Office

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ የተመራ ልዑክ በቤልት እና ሮድ ፎረም (Belt and Road Forum) ላይ ለመሳተፍ ቻይና ይገኛሉ።

ጠቅላይ ሚንስትሩ እና ልዑኩ ፎረሙ ከሚጀምርበት ቀን በፊት ቀደም ብሎ ወደ ቻይና በማቅናት ከሃገሪቱ ፕሬዝዳንት በተጨማሪ ከተለያዩ አካላት ጋር ውይይት አድርገዋል፤ ስምምነቶችንም ደርሰዋል። ከተደረሱት ስምምነቶች እና ከመወያያ ርዕሶች መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል።

ከወለድ ነጻ ብድር ስረዛ

ጠቅላይ ሚንስትሩ ትናንት ሚያዚያ 16 ከቻይናው ፕሬዝዳንት ዢ ዥንፒንግ ጋር ከቤልት እና ሮድ ፎረም በፊት የሁለትዮሽ ውይይት አካሂደዋል። የውይይቱን ይዘት በማስመልከትም የጠቅላይ ሚንስትሩ ቢሮ፤ ዢ ዥንፒንግ የጠቅላይ ሚንስትሩን አመራር እና ባለፈው አንድ ዓመት በኢትዮጵያ የተመዘገበውን የለውጥ ሂደት እንደሚያደንቁ ተናግረዋል ብሏል።

ከዚህ በተጨማሪም የጠቅላይ ሚንስትሩ ቢሮ ኢትዮጵያ ለቻይና በፈረንጆች አቆጣጠር 2018 ማብቂያ ድረስ መመለስ የነበረባትን ከወለድ ነፃ ብድሮች መሰረዙንም ገልጿል። ምንም እንኳ እስከ 2018 መጨረሻ ድረስ ከወለድ ነጻ ብድሮች ተሰረዙ ቢባልም፤ የዕዳው መጠን ግን በአሃዝ አልተጠቀሰም።

ቻይና አፍሪካ ሪሰርች ኢንሼቲቭ የተሰኘ ድርጅት አደረኩት ባለው ጥናት፤ ኢትዮጵያ ለቻይና መክፈል ያለበትን ዕዳ 13.73 ቢሊዮን ዶላር ያደርሰዋል። ይህ ተቋም እንደሚለው ከሆነ ከአፍሪካ ሃገራት መካከል ከፍተኛ የቻይና እዳ ያለባት ሃገር በነዳጅ ሃብቷ የበለጸገችው አንጎላ ነች። አንጎላ ለቻይና መክፈል የሚጠበቅባት ዕዳ 42.8 ቢሊዮን ዶላር ነው። በ 9.8 ቢሊዮን ዶላር ዕዳ ደግሞ ኬንያ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።

ኃይል ማሰራጫ እና ማከፋፈያ መስመር ዝርጋት

ከጠቅላይ ሚንስትሩ ቢሮ ባገኘነው መረጃ መሰረት፤ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ ከቻይናው ስቴት ግሪድ ከተሰኘ ኩባንያ ጋር ያደረጉትን ውይይት ተከትሎ ለኃይል ማሠራጫና ማከፋፈያ መስመር ዝርጋታ የ1.8 ቢሊዮን ዶላር ኢንቨስትመንት ስምምነት ፊርማ እንዲፈረም አድርገዋል። በኢትዮጵያ በኩል ስምምነቱን ያኖሩት የፋይናንስ ሚንስትሩ አቶ አህመድ ሺዴ ናቸው። አቶ አህመድ ''ዕዳ ሳንፈጥር በቀጥታ ኢንቨስትመንት እድገታችንን ማስቀጠል የሚያስችል ግዙፍ ፕሮጀክት ነው።'' ሲሉ ከኩባንያው ጋር የተደረውን ስምምነት ገልጸውታል።

ይህ ፕሮጀክት ለ16 የኢንዱስትሪ ፓርኮች ኃይል አቅርቦት፣ ለሁለተኛው የአዲስ ጅቡቲ የባቡር መሥመርና ለተለያዩ የሀገሪቱ ከተሞች የኤሌክትሪክ ኃይል ለማዳረስ የሚያስችል ነው ተብሎለታል። ይህ የ1.8 ቢሊዮን ዶላር ኢንቨስትመንት ያልተቋረጠ የኤሌክትሪክ ኃይል ከማቅረብ በተጨማሪ ሥራ ለመፍጠርም ይረዳል ተብሏል።

ሸገርን የማስዋብ ፕሮክት

ሸገርን [አዲስ አበባን] የማስዋብ ፕሮጄክት በጠቅላይ ሚንስትሩ የተጀመረ የሶስት ዓመት ፕሮጀክት መሆኑ ይታወቃል። የፕሮጀክቱን ዓላማ ለማሳካት በጠቅላይ ሚንስትሩ ጋባዥነት በሰው 5 ሚሊዮን ብር የሚያስከፍል የእራት ፕሮግራም እየተዘጋጀ እንደሆነ ተገልጿል። የቻይናው ፕሬዝዳንትም "የዚህን ፕሮጀክት ጠቀሜታ እንገነዘባለን፤ ለፕሮጀክቱ መሳካትም የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ መንግሥታችን እየሠራ ነው" ብለዋል ሲል የዘገበው የጠቅላይ ሚንስትሩ ቢሮ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የቻይና ሬልዌይ ኮንስትራክሽን ኩባንያ (ሲ.ረ.ሲ.ሲ) ኃላፊዎችንም አግኝተዋል። ሲ.ረ.ሲ.ሲ ኢትዮጵያን እና ጅቡቲን የሚያገናኘዉን የባቡር ፕሮጄክት ላይ ተሳታፊ ነበር። የ ሲ.ረ.ሲ.ሲ ኃላፊዎች የሸገርን ማስዋብ ፕሮጀክት ላይ ተሳትፎ እንደሚኖራቸው ለጠቅላይ ሚንስትሩ ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እና ልዑካቸው ከቻይናው ጠቅላይ ሚኒስትር ሊ ኬኪያንግ ጋር የሁለቱን ሃገራት ትብብር የሚያጠናክሩ ስምምነቶች መድረሳቸው ተዘግቧል። ከእነዚህም መካከል የሸገርን ማስዋብና ፕላዛ ፕሮጀክት 12 ኪሎ ሜትር የሚሽፍን የፋይናንስ ስምምነት ይገኝበታል። በዚህ ስምምነት ዙሪያ ከጠቅላይ ሚንስትሩ ቢሮ የተሰጠ ዝርዝር ማብራሪያ የለም።

አሊባባ

ጠ/ሚር ዐቢይ የኢንተርኔት ንግድ ኩባንያ የሆነውን የአሊባባን ዋና መሥሪያ ቤት ጎብኝተዋል። በጉብኝታቸው ወቅትም ከአሊባባ ሊቀመንበር ጃክ ማ ጋር ተገናኝተዋል። ጃክ ማ በኢትዮጵያ እየተካሄዱ ባሉት ለውጦች መደነቃቸውንና ኢትዮጵያ ለኩባንያቸው ቁልፍ አጋር በመሆኗ በዚህ ዓመት መጨረሻ ለጉብኝት ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመጡ የጠቅላይ ሚንስትሩ ቢሮ ዘግቧል።

ናዝራዊት አበራ

ናዝራዊት አበራ በቻይና በአደገኛ እፅ ዝውውር ተጠርጥራ በእስር እንደምትገኝ ይታወሳል። በቻይና የኢትዮጵያ ኤምባሲ እና ቆንስላ ጽ/ቤት የናዝራዊትን ጉዳይ በቅርብ እየተከታተለ መሆኑን የውጪ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ አቶ ነብያት ጌታቸው ለቢቢሲ ገልፀው ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከቻይና ፕሬዝዳነት ጋር በነበራቸው ውይይት የናዝራዊት አበራ እስር እንዳሳሰባቸው ገልጸዋል።