የስሪ ላንካ ጥቃት፡ ፊትን መሸፈን የተከለከለባቸው የዓለማችን አገራት

ኒቃብ የለበሰች ሴት Image copyright Getty Images

በስሪ ላንካ ከሁለት ሳምንት በፊት በፋሲካ በዓል ወቅት የደረሰውን ጥቃት ተከትሎ ህዝብ በተሰበሰበበት ቦታ ፊትን መሸፈን ተከልክሏል። የአገሪቱ ፕሬዚደንት እንዳስታወቁት ለአገሪቱ ደህንነት ሲባል ማንነትን የሚደብቁ አልባሳት መከልከላቸውን አስታውቀዋል።

ሂጃብ ለባሿ የሕግ ብቃት መመዘኛ ፈተና ላይ እንዳትቀመጥ ተከለከለች

ይህ እግድ ለሰላማችን ይበጀናል ሲሉ የተለያዩ ብሔሮችና ኃይማኖት ተከታዮች ተግባራዊ እንዲያደርጉት ያበረታቱ እንዳሉ ሁሉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ደግሞ በሐይማኖታዊ ግዴታ ልብስን የሚለብሱ ሙስሊም ሴቶችን መብት የጣሰና ያገለለ ነው ሲሉ ተቃውመውታል።

ተመሳሳይ እገዳዎችን የጣሉ የዓለማችን አገራት የትኞቹ ናቸው?

ፈረንሳይ

ፈረንሳይ ሕዝብ በተሰበሰበበት ቦታ ሙሉ በሙሉ ፊትን የሚሸፍን እስላማዊ ልብስ የከለከለች የመጀመሪያዋ አውሮፓዊት አገር ናት፤ እገዳውን የጣለችውም ከስምንት ዓመታት በፊት ሲሆን በአውሮፓ ሰብዓዊ መብቶችን የሚመለከተው ፍርድቤት እገዳውን ያፀደቀው ከአምስት ዓመታት በፊት ነበር።

ዴንማርክ

በዴንማርክም ሙሉ በሙሉ ፊትን የሚሸፍኑ አልባሳት ክልከላ ተግባራዊ መደረጉን ተከትሎ ባለፈው ዓመት ተቃውሞ ተነስቶ ነበር። አንድ ሰው ሙሉ በሙሉ ፊትን የሚሸፍን አልባሳት ለብሶ ህዝብ በተሰበሰበበት ቦታ የተገኘ እንደሆነ 1 ሺህ ክሮን (157 የአሜሪካ ዶላር ወይም 4500 ብር ገደማ) ቅጣትን ያስከትላል።

በተደጋጋሚ ይህን አድርጎ የተገኘም ቅጣቱ በአስር እጥፍ ከፍ ሊልበት ይችላል።

ዴንማርክ ሙሉ የፊት ገጽታን የሚሸፍን 'ሂጃብ' አገደች

ኔዘርላንድስ

የኔዘርላንድስ ምክርቤት ተመሳሳይ ህግ ያስተላለፈው ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር ላይ ነበር። ሕጉ የህዝብ በሆኑ ህንፃዎች ላይ፤ ለምሳሌ እንደ ሆስፒታል፣ ትምህርት ቤቶችና የህዝብ ትራንስፖርት ላይ ፊትን መሸፈንን ይከለክላል፤ ይሁን እንጂ የህዝብ መንቀሳቀሻ መንገዶችን አያካትትም።

ጀርመን

በጀርመን ደግሞ ፊትን ሸፍኖ ማሽከርከር ህገወጥ ነው። የጀርመን የህዝብ ተወካዮች ምክርቤት በከፊልም ቢሆን በዳኞች፣ በመንግስት ሰራተኞች እና ወታደሮች ላይም እግዱን ጥሏል። ሙሉ ፊታቸውን በዓይነ እርግብ የሸፈኑ ሴቶችም ማንነታቸውን ለማሳየት በሚጠየቁበት ጊዜ መገለጥ እንዳለባቸው ያስገድዳል።

አውስትራሊያ

በአውስትራሊያ በህዝብ መገልገያ ቦታዎች፤ ለምሳሌ ትምህርት ቤትና ፍርድቤት ሙሉ በሙሉ ፊትን የሚሸፍን አልባሳትን መልበስ ያገደችው ከሁለት ዓመታት በፊት ነው።

ቤልጂየም

ቤልጂየም ሙሉ ፊትን መሸፈን የሚከለክለውን ህግ ተግባራዊ ያደረገችው ከስምንት ዓመታት በፊት ሲሆን እግዱ ማንኛውንም ዓይነት ማንነትን የማያሳይ ልብስ በተለያዩ መዝናኛ ቦታዎችና መንገዶች ላይ ለብሶ መገኘትን ይከለክላል።

ኖርዌይ

ኖርዌይ በትምህርት ተቋማት ውስጥ ፊትን የሚሸፍን አልባሳትን መልበስ የከለከለችው ባለፈው ዓመት ነው።

ቡልጋሪያ

ከሶስት ዓመታት በፊት የቡልጋሪያ ምክር ቤት ፊታቸውን የሚሸፍኑ ሴቶች የሚያገኙትን ጥቅማ ጥቅም የሚነሳ ረቂቅ ህግ አፅድቃለች።

ሉግዘምበርግ

በሆስፒታል፣ በፍርድቤቶችና ህዝብ በሚገለገልባቸው ህንፃዎች ፊትን መሸፈን በሉግዘምበርግም የተከለከለ ነው።

በኬንያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ የተሞሸሩት ጥንዶች

አንዳንድ የአውሮፓ አገራት በተወሰኑ ከተሞቻቸው አሊያም ክልሎች ብቻ ህጉ ተግባራዊ እንዲሆን አድርገዋል። ይህም ጣሊያን፣ ስፔን እና ስዊዘርላንድን ይጨምራል።

አፍሪካ

ቻድ፣ ጋቦን፣ ካሜሩን ፣ ኒጀርና ሪፐብሊክ ኦፍ ኮንጎ ከሶስት ዓመታት በፊት በተደጋጋሚ ባጋጠማቸው የአጥፍቶ ጠፊ ጥቃት ፈፃሚዎች የተሸፈኑ ሴቶች ሆነው በመገኘታቸው ሙሉ በሙሉ ፊትን መሸፈን ከልክለዋል።

አልጀሪያም ከባለፈው ዓመት አንስቶ ሙሉ በሙሉ ፊትን የሚሸፍን ሂጃብ ማድረግ አግዳለች።

ቻይና

በቻይና ዢንጂያንግ ግዛት ፊትን የሚሸፍን አልባሳት መልበስና ፂምን ማሳደግ በጥብቅ የተከለከለ ነው።

ዢንጂያንግ ኡጉር የተባለች ሙስሊሞች የሚኖሩባት ከተማ ስትሆን ክልከላውም እነርሱን ያገለለ እንደሆነ ተናግረዋል። ግዛቱ ግን የተለያዩ ግጭቶች የሚከሰቱበት ሲሆን መንግስት እስላማዊ ታጣቂ ቡድኑን ተጠያቂ ያደርጋል።

ተያያዥ ርዕሶች

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ