“ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ ከደወሉልን በኋላ ተረጋግተናል” የናዝራዊት አበራ እህት

ናዝራዊት አበራ እና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ Image copyright Facebook/ BBC

ናዝራዊት አበራ በቻይና በእፅ ዝውውር ተጠርጥራ በቁጥጥር ሥር መዋሏ ከተሰማ አራት ወራቶች ተቆጥረዋል።

አንድ ሰው እፅ ሲያዘዋውር ከተገኘ የሞት ፍርድ እንዲበየንበት የሚያዘው የቻይና ሕግ በናዝራዊት ላይ ተግባራዊ ይሆናል በሚል በቤተሰቦቿ፣ በቅርብ ዘመዶቿ እንዲሁም በመላው ኢትዮጵያ ስጋትን ፈጥሯል።

በመሆኑም ናዝራዊት ጥፋተኛ አለመሆኗን ለመግለፅ የፊርማ ማሰባሰብ ዘመቻ አሁንም እየተካሄደ ነው፤ ጉዳዩም የታዋቂ ሰዎችንና የባለሥልጣናትን ትኩረት መያዝ ችሏል። ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተሉት እንደሆነም ተገልጿል።

በቻይና የተደረሱት ስምምነቶች የትኞቹ ናቸው?

የናዝራዊት ታላቅ እህት ቤተልሔም አበራ እንደሚሉት በወቅቱ ናዝራዊት ላይ የሞት ፍርዱ በአፋጣኝ ተወስኖ ወደ ተግባር ይገባል የሚል ስጋት ነበራቸው፤ ለቤተሰቡም ከባድ ሃዘን ያጠላ ጭንቀት ሰፍኖ ነበር።

ታዲያ በዚህ ጊዜ ነበር የጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ ስልክ ያንቃጨለው።

"ጠቅላይ ሚንስትሩ በእጃችን ስልክ ላይ ነበር የደወሉልን፤ መጀመሪያ ሞት እንደሌለ ነው ያረጋጉን ፤ በቅርቡም ወደ ቻይና እንደሚያቀኑና ከያዟቸው ጉዳዮች አንዱ በመሆኑ የሚኖረውን ሂደት እንደሚያሳውቁን በራሳቸው አንደበት ነግረው ነበር" ይላሉ አጋጣሚውን ሲያስታውሱ።

ይህም በተወሰነ መልኩም ቢሆን ለቤተሰቡ እፎይታ እንደሰጣቸው የናዝራዊት ታላቅ እህት ቤተልሔም ይናገራሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ የገቡላቸው ቃል ባይኖርም የኢትዮጵያ መንግሥት ጉዳዩን እንደሚከታተለውና ለቻይና መንግሥትም ጥያቄውን እንደሚያቀርብ ነግረውናል ይላሉ።

ከቀናት በፊት ለሮድ ኤንድ ቤልት ኢንሼቲቭ ፎረም ወደ ቻይና ያቀኑት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ በቻይና ቆይታቸው የናዝራዊት አበራ ጉዳይ አንዱ ጉዳያቸው እንደሆነ አስታውቀው ነበር።

ጉባዔው ከተጠናቀቀ በኋላ የእርሳቸውን ወደ ኢትዮጵያ መመለስ ተከትሎ 'ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ ናዝራዊትን አስፈትተዋት መጡ' የሚሉ መረጃዎች በተለያዩ ማህበራዊ ድረ ገፆች እየተናፈሱ ነው።

ተስፋዬ ገብረአብ ስለ ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ምን ይላል?

ይሁን እንጂ ያነጋገርናቸው የናዝራዊት ታላቅ እህት ቤተልሔም አበራ "ናዝራዊት አልተፈታችም፤ እስካሁን ቻይና በሚገኘው ጉዋንዡ በእስር ላይ ነው የምትገኘው፤ የሚናፈሰው ወሬም ሀሰት ነው" በማለት ሀሰተኛው መረጃው እየተካሄዱ ያሉትን ዘመቻዎች እንዳያስተጓጉል ስጋታቸውን ይገልፃሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩም ከቻይና ከተመለሱ በኋላ ባይደውሉላቸውም በጠቅላይ አቃቤ ሕግ በኩል ሥራዎች እየተሰሩ እንደሆነ ማረጋገጥ እንደቻሉ ይናገራሉ።

"ቻይና ከሚገኘው የኢትዮጵያ ቆንፅላና ከተለያዩ አካላት ጋር ሆነን በቅርበት እየተከታተልን ነው" የሚሉት ቤተልሔም የኢትዮጵያ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ቢሮ ቻይና ከሚገኘው አቃቤ ሕግ ጋር የመረጃ ልውውጥ እያደረጉ መሆናቸውንም ለቢቢሲ ገልፀዋል።

በዚህም መሰረት ፍርድ ቤት እስከምትቀርብ ድረስ ናዝራዊትን በአካል ማግኘት ባይቻልም በቆንጽላው በኩል መረጃዎች እንደሚለዋወጡ የሚናገሩት ቤተልሔም ሒደቱ ቀላል እንደማይሆን ቢገምቱም በተስፋ ተሞልተው የእርሷን መፈታት እየተጠባበቁ ነው።

"ናዝራዊት በተፈጥሮዋ ጠንካራ ናት" የሚሉት እህቷ እስር ቤት ከባድ ቢሆንም አሁን ተረጋግታ ከሙያዋ ጋር ግንኙነት ያላቸውንና የቋንቋ መጻህፍትን እያነበበች እንደምትጠባበቅ ይገልፃሉ።

ናዝራዊት የተለያዩ መጻህፍት እንዲገቡላት የጠየቀች ሲሆን እስር ቤት ያሉትን ቻይናውያን የእንግሊዝኛ ቋንቋ እያስተማረች ነው፤ የቻይና ቋንቋ ተምራ መውጣትም እንደምትፈልግ መልዕክት አስተላልፋላቸዋለች። ለአንዳንድ ወጪዎች የሚሆናት በወር 100 የአሜሪካ ዶላር (3000 ሺህ ብር ገደማ) በቆንጽላው በኩል እንደሚልኩላት ነግረውናል።

በሌላ በኩል ለናዝራዊት ሻምፖ መሳዩን እፅ ሰጥታለች ተብላ የተጠረጠረችው ጓደኛዋ ስምረት ካህሳይ አዲስ አበባ በሚገኘው ሶስተኛ ፖሊስ ጣቢያ በቁጥጥር ሥር ውላ የነበረ ቢሆንም በማግስቱ በ20 ሺህ ብር ዋስትና እንደተለቀቀች ያስታውሳሉ።

«በስልክዎ ታካሚና አካሚ እናገናኛለን» ሥራ ፈጣሪው ወጣት

ይሁን እንጂ አቤቱታቸውን በማቅረባቸው በድጋሚ በዚያው ፖሊስ ጣቢያ ከጓደኛዋ ጋር በቁጥጥር ሥራ ውላ ጉዳዩ በፍርድ ሂደት ላይ ይገኛል።

በናዝራዊት ላይ የተፈጠረውምን ነበር?

ኢትዮጵያዊቷ ናዝራዊት አበራ በእፅ ዝውውር ባለፈው ታህሳስ 14 ቀን 2011 ዓ.ም በቻይና በቁጥጥር ሥር ውላ በእስር ላይ እንደምትገኝ ይታወሳል። የምህንድስና ሙያ ያላት ናዝራዊት ወደ ቻይና ስትሄድ ከጓደኛዋ የተሰጣት ሻምፖ መሳይ እቃ 1 ኪሎ ግራም ኮኬይን የተባለ እፅ መሆኑ የታወቀው ቻይና በደረሰችበት ጊዜ ነበር።

በዕጽ በማዘዋወር የተጠረጠረችው ናይጄሪያዊት ከሳኡዲ እስር ቤት ተለቀቀች

"እንዴት እንደተያዘች አናውቅም፤ በጓደኛዋ ጋባዥነት አብረው እንደሚሄዱ እናውቃለን፤ ጓደኛዋ አባቴ ሞተ ብላ እርሷን ብቻዋን እንደላከቻት ነግራናለች" ይላሉ የናዝራዊት ታላቅ እህት የተያዘችበትን አጋጣሚ ሲያስታውሱ።

ሐሙስ ቀን ወደ ቻይና ያቀናችው ናዝራዊትም ለሁለት ተከታታይ ቀናት ድምጿ ሲጠፋባቸው የአሁኗ ተጠርጣሪ ጓደኛዋን ይጠይቋታል።

እርሷም ለጓደኛዋ እንድትሰጥላት የሰጠቻት ሻምፖ ምክንያት ሳይሆን እንደማይቀር እንደነገረቻቸው ያስረዳሉ።

በወቅቱ የነበረው ሁኔታ ቤተሰቡን ያስደነገጠ ቢሆንም በተለይ ለእናታቸው የጤና እክል ምክንያት ሆኗል። እናቷ ናዝራዊት እስካሁን የትና በምን ሁኔታ እንዳለች አያውቁም። ባጋጠማቸው ስትሮክ ግማሽ ጎናቸው መንቀሳቀስ እንደማይችልም ሰምተናል።

ዕለት በዕለትም ስለ እርሷ መጠየቃቸውን ቀጥለዋል።

ተያያዥ ርዕሶች

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ