አትሌት ኃይሌ ገብረሥላሴ፡ ትምህርት ቤት ለመገንባት የመሠረት ድንጋይ አስቀመጠ

አትሌት ኃይለ ገ/ሥላሴ በዳስ ትምህርት ቤት ውስጥ Image copyright AMMA

አትሌት ኃይሌ ገብረሥላሴ በአማራ ክልል፤ በዋግ ኸምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ፃግብጅ ወረዳ የዳስ ትምህርት ቤት በመገኘት ትምህርት ቤት ለመገንባት የመሠረት ድንጋይ ማስቀመጡን የዋግ ኸምራ አስተዳደር የትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ሽታው አዳነ ለቢቢሲ ገለፁ።

ወላጆች ለልጆቻቸው የሚመኟቸው ኢትዮጵያዊ መምህር

በዳስ ትምህርት ቤቱ 159 ተማሪዎች የሚማሩ ሲሆን የሚገነባው ትምህርት ቤትም በአትሌት ሻለቃ ኃይለ ገ/ሥላሴ ሥም እንደተሰየመም ገልፀውልናል። የሚገነባው ትምህርት ቤት በቀጣይ 5 ወራት እንደሚጠናቀቅም ይጠበቃል።

አትሌት ኃይለ ገ/ሥላሴ የዳስ ትምህርት ቤቶችን በቴሌቪዥን ተመልክቶ እንዲህ ዓይነት ትምህርት ቤት በዚህ ዘመን መኖር የለበትም የሚል ሃሳብ እንዳደረበት በመገናኛ ብዙሃን መግለፁ የሚታወስ ሲሆን ቦታዎቹን ለመጎብኘት ትናንት ወደ ሥፍራው አቅንቷል።

በአስተዳደሩ በርካታ የዳስ ትምህርት ቤቶች መኖራቸውን የሚናገሩት ኃላፊው የመንግስት ትኩረት አናሳ መሆኑ እና የትምህርት መሠረተ ልማቶች ሳይሟሉ ትምህርት ቤት መክፈት ለዳስ ትምህርት ቤቶች መበራከት አንዱ ምክንያት እንደሆነ ይናገራሉ።

"ችግሮቹ ተደጋግመው ቢነሱም ትኩረት የሰጠው የለም፤ እንዲያውም ትንሽ እንቅስቃሴ የተጀመረውና በማህበራዊ ሚዲያዎች መረጃውን በመልቀቅ ትኩረት ማግኘት የቻሉት ከባለፈው ዓመት ጀምሮ ነው" ይላሉ።

Image copyright AMMA

በእነዚህ የዳስ ትምህርት ቤቶች ዝናብ በሚዘንብበት ጊዜ ትምህርት የሚቋረጥ ሲሆን ፀሐይን ግን በቅጠል በመሸፈን ለመከላከል ጥረት እንደሚደረግ ተናግረዋል።

"በአስተዳደሩ የሚገነቡት ትምህርት ቤቶች በጣም ጠባብና በውል የማያንቀሳቅሱ ከዳስ ያልተሻሉ ናቸው" የሚሉት ኃላፊው በዋግ ኸምራ ከሚገኙት 264 ትምህርት ቤቶች ትምህርት ሚኒስቴር ባወጣው የትምህርት ጥራት ቁጥጥር መሠረት 154ቱ (85 በመቶው) ከደረጃ በታች መሆናቸውን ይገልፃሉ።

የዘንድሮ ተመራቂዎች እንዴት ሥራ ያገኛሉ?

በመደበኛ ትምህርት ቤት 324 የዳስ መማሪያ ክፍሎች ሲኖሩ ህፃናት በእግራቸው ተጉዘው ትምህርት ቤት መድረስ ስለማይችሉ በአቅራቢያቸው የተሰራ 550 የሳተላይት ትምህርት ቤቶችም የዳስ መሆናቸውን አቶ ሽታው ይጠቅሳሉ።

በዋግ ኸምራ አስተዳደር በአጠቃላይ 874 የዳስ መማሪያ ክፍሎች የሚገኙ ሲሆን ከ1500 በላይ ተማሪዎች የሚማሩበትም ነው።

አትሌት ኃይሌ ገ/ሥላሴም ከታላቁ ሩጫ በሚሰበሰብ ገቢ ሁለት ተጨማሪ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን ለመገንባትም ቃል መግባቱንም ኃላፊው አክለዋል።

ተያያዥ ርዕሶች

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ