ናዝራዊት አበራ፡ የጓደኛዋ ስምረት ካህሳይ ቤተሰቦች ምን ይላሉ?

ስምረት ካህሳይ እና ናዝራዊት አበራ Image copyright Facebook/ FANA

ናዝራዊት አበራ በቻይና ዕፅ በማዘዋወር ተጠርጥራ በቁጥጥር ስር መዋሏ ከተሰማ አራት ወራቶች ተቆጥረዋል። አንድ ሰው እፅ ሲያዘዋውር ከተገኘ የሞት ፍርድ እንዲበየንበት የሚያዘው የቻይና ህግ በናዝራዊት ላይ ተግባራዊ ይሆናል በሚል በቤተሰቦቿ፣ በቅርብ ዘመዶቿ እንዲሁም በመላው ኢትዮጵያ ስጋት ተፈጥሮም ቆይቷል።

ዕፁን ይዛ ተገኝታለች የተባለችው ናዝራዊት በጉዋንዡ እስር ቤት የምትገኝ ሲሆን ይህንን አደንዛዥ ዕፅ ለናዝራዊት አበራ ሰጥታታለች የተባለችው ጓደኛዋና አብሮ አደጓ ስምረት ካህሳይም አዲስ አበባ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውላ ጉዳዩ በፍርድ ቤት ተይዟል።

“ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ ከደወሉልን በኋላ ተረጋግተናል” የናዝራዊት አበራ እህት

የተጠርጣሪዋ ስምረት ካህሳይ ቤተሰቦች ለቢቢሲ እንደገለፁት ስምረትና ናዝራዊት ጓደኛማቾች ነበሩ፤ ከሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ጀምሮም አብረው ተምረዋል።

የእህትማማችነት ያክል የጠነከረ ጓደኝነት ነበራቸውም ይላሉ። "አንዳቸው ከአንዳቸው ቤት እየሄዱም አብረው ጊዜ ያሳልፉ ነበር፤ በጣም ነበር የሚዋደዱት" የሚሉት አክስቷ ሰብለወንጌል ከፍያለው ናቸው።

ወይዘሮ ሰብለወንጌል እንደሚሉት ስምረት ጫማና ልብስ ከቻይና እያመጣች ትሸጣለች፤ ናዝራዊትም ከቻይና ልብስ ማምጣት እፈልጋለሁ እያለች ትነግራት ስለነበር አብረው ለመሄድ እንደወሰኑ ይናገራሉ።

ቻይና ለመሄድ አብረው ነበር ትኬት የቆረጡት፤ ይሁን እንጂ በበረራቸው ቀን ጠዋት የስምረት አባት በድንገት ሕይወታቸው ማለፉን ያስታውሳሉ፤ ለዚህም ማስረጃ አለን ይላሉ።

በዚህም ጊዜ ናዝራዊት ከቤተሰቦቿ ጋር ለቅሶ እንደመጣችና ጉዞውን እንድታስተላልፈው ስምረት ብትጠይቃትም 'እኔ ደርሼ እመጣለሁ፤ ጉዞውን አላስተላልፍም' ብላት እንደሄደች ይናገራሉ።

በቻይና የተደረሱት ስምምነቶች የትኞቹ ናቸው?

"ዕፁን ማን ይስጥ፤ ማን ይቀበል የሚለው በፍርድ ቤት የተያዘ በመሆኑ እዚህ ላይ የምለው የለኝም" የሚሉት የስምረት አክስትና አሳዳጊዋ ሰብለወንጌል በተለይ በማህበራዊ ሚዲያዎችና በሌሎችም መገናኛ ብዙሃን ከአንድ ወገን ብቻ ሲዘገብ መቆየቱ ስምረትን በጣም ጎድቷታል ሲሉ ይወቅሳሉ።

እንደ ቤተሰብም ስምረት ካህሳይ ጓደኛዋን አሳልፋ እንደሰጠችት ተደርጎ በድምዳሜ መወራቱ በጣም አሳዝኖናል ብለዋል።

ስምረት ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ አየር መንገድ የበረራ አስተናጋጅ የነበረች ሲሆን በኩላሊት ህመም ምክንያት ሥራውን እንዳቆመችም ገልፀውልናል።

ከጉዞው በኋላ

ናዝራዊት በቻይና በዕፅ ዝውውር መያዟ ይሰማል፤ ያኔ የናዝራዊት ቤተሰቦች ወደ ቤታቸው እንደመጡ የናዝራዊት ታናሽ እህት ዶ/ር ማርነት ካህሳይ ትናገራለች።

"ናዝራዊት ከሄደች ድምጿ አልተሰማም፤ ምን እንደሆነች አናውቅም፤ ነገርግን ቻይና አየር ማረፊያ ስትደርስ በቁጥጥር ስር ውላለች" ሲሉ የናዝራዊት ቤተሰቦች እንደገለፁላቸው ታስታውሳለች። እርሷ እንደምትለው እነርሱም ለጉዳዩ እንግዳ ነበሩ። "ምን ይዛ ነው? ብለን ጠየቅናቸው" ትላለች።

እነርሱም ምንም የሚያውቁት ነገር እንደሌለ ምላሽ የሰጧቸው ሲሆን በወቅቱ ስምረት ቤት ውስጥ አልነበረችም።

" እኔና እናቴ ነበርን ለስምረት የነገርናት፤ በጣም ደነገጠች፤ ምን እንደተፈጠረ ማወቅ አልቻለችም፤ ከዚያም የናዝራዊትን ወንድም ለማነጋገር ሞከረች። ይሁን እንጂ መልሰው እነሱም እርሷን ነበር ሲጠይቋት የነበረው" የምትለው ዶ/ር ማርነት በተደጋጋሚ ስልክ እየደወሉ 'ምንድን ነው ያደረግሻት? የት ነው ያደረሻት?' እያሉ ሲያናግሯት ነበር ትላለች።

"ናዝራዊት አበራ ላይ ክስ አልተመሰረተም" የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር

የስምረት አክስት ወ/ሮ ሰብለወንጌል በበኩላቸው በዚህ ጊዜ ስምረት ለናዝራዊት ሲደረግ የነበረውን የፊርማ ማሰባሰብ ዘመቻ እንደተቀላቀለችና ሌሎች ሰዎችንም ስታነሳሳ ነበር ይላሉ።

"ከታላቅ እህቷም ጋር 'ተገናኝተን እናውራ፤ እንረዳዳ፤ እኔም ተሰምቶኛል' ስትል ከዚህ በኋላ ፍርድ ቤት የያዘው ጉዳይ ስለሆነ ሂጂና ለአቃቤ ህጉ ንገሪው የሚል ምላሽ ነው የተሰጣት" ሲሉ ይገልፃሉ።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ናዝራዊት በቁጥጥር ሥር መዋሏ ከተሰማ በኋላ ባሉት አስር ቀናት ውስጥ ስምረት ኬንያ ደርሳ የተመለሰች ሲሆን ድጋሜ ወደ ታይላንድ ለመሄድ አየር መንገድ ውስጥ ሆና በፖሊስ ቁጥጥር ሥር እንደዋለች ታናሽ እህቷ ዶ/ር ማርነት ታስረዳለች።

በረራዋ ማታ ነበር የምትለው እህቷ እርሷን ወደ ጣቢያ ከወሰዷት በኋላ ፖሊሶች ቤታቸውን እንደፈተሹ ትናገራለች።

ዕጽ በማዘዋወር የተጠረጠረችው ናይጄሪያዊት ከእስር ተለቀቀች

እርሷ እንደምትለው በቀጣዩ ቀን ስምረት ፍርድ ቤት የቀረበች ሲሆን በቂ ማስረጃ ስላልነበራቸው የዋስ መብቷ እንዲጠበቅላት፤ ጉዳዩ እስከሚጣራም ድረስ ፓስፖርቷ እንዲያዝ ብለው በ20 ሺህ ብር ዋስ እንደተለቀቀች ትናገራለች።

ከዚህም በኋላ ስምረት እንደማንኛውም ሰው በሰላም ስትንቀሳቀስ እንደቆየች፤ ነገር ግን ቀኑን በትክክል ባታስታውስም በተለቀቀች በወር ከአራት ቀን ውስጥ በድጋሜ ቤት ውስጥ እያለች በቁጥጥር ሥር እንደዋለች ታስረዳለች- ዶ/ር ማርነት።

ስምረት በመጀመሪያ ዕፅ ለናዝራዊት አበራ ሰጥታለች በሚል ክስ ተጠርጥራ የተያዘች ሲሆን በድጋሜ በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋለችው ያለአግባብ የተገኘ ገንዘብን መጠቀምና ሰዎችን ያለአግባብ ማዘዋወር በሚል ክስ ተጠርጥራ ነው ስትልም አክላለች።

ቀድሞ የተያዘ ፕሮግራም ስለሆነ ስምረት የቻይና ጉዞዋን ለምን አላደረገችም? ለምን ታይላንድ ሄደች? ያልናቸው የስምረት አክስት ሰብለወንጌል በበኩላቸው "ከእጮኛዋ ጋር ነበር ወደ ታይላንድ ልትሄድ የነበረው፤ ፕሮግራም ነበራቸው፤ ሰርፕራይዝ ሊያደርጋት ነበር፤ ልንነግርሽ የማንፈልገው ግላዊ ጉዳይ ነበራቸው" ሲሉ ምላሽ ሰጥተውናል።

እጮኛዋም አብሮ በቁጥጥር ሥር የዋለ ሲሆን፣ ከዚሁ ጉዳይ ጋር በተያያዘ እንደሆነ የስምረት እህት ነግራናለች፤ ይሁን እንጂ ጉዳዩን ህግ ስለያዘው የሚነግሩን ዝርዝር መረጃ የለም ብላናለች።

ስምረት በሶስተኛ ፖሊስ ጣቢያ በእስር ላይ የምትገኝ ሲሆን የፍርድ ሂደቱን እየተከታተሉ እንደሆነም ገልፀውልናል።

"በጥሩ ጤንነት ላይ አይደለችም"

ታናሽ እህቷ ዶ/ር ማርነት "መጀመሪያ በቁጥጥር ሥር ውላ በዋስ ከወጣች በኋላ ሚዲያ ላይ የሚናፈሰውን ስናይ እንደ ቤተሰብ፤ የቤተሰብሽን ክብር ነው ያዋረድሽው ብለን ገለልተኛ አደረግናት" ትላለች የሆነውን ስታስታውስ።

ከአምቦ ከተማ ነዋሪ ለዶ/ር አምባቸው የቀረቡ 4 ጥያቄዎች

ሚዲያ ላይ እንድትወጣና እንድትናገር የገፋፏት ቢሆንም 'እህቴ ናት፤ የእርሷ ጉዳት የእኔም ጉዳት ነው፤ እኔ ሚዲያ ላይ ከወጣሁ የፊርማ ማሰባሰቡን ዘመቻ ሊገታው ይችላል' በማለት ሚዲያ እንደሸሸች ትናገራለች።

"እኔ ተጎድቼ፤ እርሷ ነፃ ትውጣ" ስትልም ነበር፤ ነገር ግን የናዝራዊትን ቤተሰቦች ለማነጋገርና ለማገዝ ብትፈልግም ፈቃደኛ እንዳልነበሩ ትገልፃለች። ይህ ሁሉ ነቀፌታም ሲደራረብባት ጨጓራዋን ታመመች፤ ትርፍ አንጀትም አጋጥሟት ቀዶ ህክምና አድርጋለች።

ሰውነቷም በጣም እንደተጎሳቆለና የቀደመው መልኳ እንደሌለ በሃዘኔታ ይገልፃሉ። ቤተሰቡም እርሷን ይዘው ሐኪም ቤት ለሐኪም ቤት እየተንከራተቱ እንዳሉም ያስረዳሉ።

ስምረት ግን በዚህ ሁኔታ ውስጥም ሆና የናዝራዊትን መፈታት ዜና እንደምትጠባበቅና አዘውትራ እንደምትጠይቃቸውም ይናገራሉ።

ስምረት ናዝራዊት ተፈትታ፤ እውነቱን ተናግራ እርሷንም ነፃ እንደምታወጣት ተስፋ አድርጋለች። የስምረት አክስትና እህት እንደ ቤተሰብ የፍርድ ሂደቱን እየተከታተሉ ሲሆን ለናዝራዊትም ፍትህ እንደሚመኙ ነግረውናል።

የስምረት ቀጣይ ቀጠሮ ሚያዚያ 29/2011 ዓ.ም እንደሆነም ለቢቢሲ ገልፀዋል።

ተያያዥ ርዕሶች

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ