ቦይንግ አደጋው ከመድረሱ ከዓመት በፊት ችግሩን አውቅ ነበር አለ

737 ማክስ አውሮፕላን Image copyright Getty Images

አውሮፕላን አምራቹ ቦይንግ ሁለቱም 737 ማክስ አውሮፕላኖች ላይ አደጋ ከማጋጠሙ አንድ ዓመት በፊት ችግር እንደነበረባቸው ያውቅ እንደነበርና ምንም እርምጃ አለመውሰዱን አመነ።

ድርጅቱ እንዳስታወቀው አውሮፕላኖቹ ችግር እንዳለባቸው ባወቀ ጊዜ የጥንቃቄ ስርዓቶችን ከመዘርጋት ይልቅ የአደጋ ጊዜ መጠቆሚያ መተግበሪያዎችን ብቻ ነበር ያዘጋጀው። ይህ እርምጃም አውሮፕላኖቹ ላይ ምንም ችግር አልፈጠረም ብሏል።

149 መንገደኞችንና 8 የበረራ ሰራተኞችን አሳፍሮ ወደ ናይሮቢ ይጓዝ የነበረው ET 302 ቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላን ከቦሌ አለም አቀፍ አውሮፕላን ከተነሳ ከ6 ደቂቃዎች በኋላ ከአብራሪዎቹ ጋር ይደረግ የነበረው ግንኙነት ተቋርጦ ቢሾፍቱ አካባቢ አውሮፕላኑ የመከስከስ አደጋ ማጋጠሙ የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው።

ይህንን ተከትሎም 387 የሚሆኑ ቦይንግ ማክስ 737 አውሮፕላኖች በመላው ዓለም ጥቅም ላይ እንዳይውሉ ታግደዋል።

ባለፈው ጥቅምት ወርም የኢንዶኔዢያ ላየን አየር መንገድ ንብረት የሆነ ተመሳሳይ አውሮፕላን ለበረራ ከተነሳ ከደቂቃዎች በኋላ በከፍተኛ ፍጥነት ቁልቁል ወደ ባህር በመከስከሱ የ189 ሰዎች ሕይወት ጠፍቷል።

''አብራሪዎቹ ትክክለኛው መመሪያ ተከትለዋል''

አደጋው የደረሰበት ቦይንግ 737 የገጠመው ምን ነበር ?

ቦይንግ ለችግሩ መፍትሄ የሚሆነውን አሰራር በመላው ዓለም ተግባራዊ ለማድረግ አስቦ የነበረ ቢሆንም አውሮፕላኖቹን ለአየር መንገዶች ማስረከብ እስከሚጀመርበት ሰዓት ድረስ አለማጠናቀቁን አምኗል።

አየር መንገዶችም አውሮፕላኖቹን ከገዙ በኋላ እንደገና አዲሱን የመተግበሪያ ስርዓት እንዲገዙ ሆኗል። ችግሩንም በአጭር ጊዜ ውስጥ ለመፍታት የማሻሻያ ሥራ እየሰራሁ ነበር ብሏል ቦይንግ።

ሁለቱም 737 አውሮፕላኖች ላይ አደጋ ከማጋጠሙ ከወራት በፊት ችግር እንዳለባቸው ባውቅም፤ አደጋው ያጋጠማቸው በዚሁ ችግር ምክንያት ነው የሚለው ግን ገና በምርመራ የሚታወቅ ነው ብሏል።

የበረራ መረጃ መቅጃው የያዘው መረጃ እንዳሳየው አውሮፕላኑ የተሳሳተ ማዕዘን ጠቋሚ (አንግል ኦፍ አታክ ሴንሰር) ግብዓት ስለነበረው የደህንነት መቆጣጠሪያ ሥርዓቱ (ኤምካስ) ሥራውን እንዲያከናውን ማድረጉ የፓይለቶቹ ጥፋት አይደለም፤ ይህ ደግሞ የሆነው ፓይለቶቹ ሊያጋጥም ስለሚችለው አደጋ ከቦይንግ ሊሰጣቸው የሚገባውን የማሻሻያ ስርዓት አለማግኘታቸውን ያመላክታል።

አደጋው ስፍራ በየቀኑ እየሄዱ የሚያለቅሱት እናት ማን ናቸው?

"የሞተው የኔ ያሬድ ነው ብዬ አላሰብኩም" የካፕቴን ያሬድ የ11 አመት ጓደኛ

በተሳሳተ መረጃ ኤምካስ (ማኑቬሪንግ ካራክተሪስቲክስ ኦጉመንቴሽን ሲስተም) አክቲቬት እንዳይሆን የተሻሻለ ሶፍትዌር እያዘጋጀ እንደነበረና፣ ለአብራሪዎች ስልጠና እና 737 ማክስን በተመለከተ የሥልጠና ፕሮግራሞችን እንዳረቀቀ ገልጿል።

አደጋዎቹም ይህንን ከማድረጉ በፊት መከሰታቸው አሳዛኝ አጋጣሚ ቢሆንም አሁንም ቢሆን አደጋው ከዚህ ጋር ይያያዝ አይያያዝ የታወቀ ነገር የለም ብሏል በመግለጫው።

የአሜሪካው የፌደራል አቪዬሽን ቁጥጥር ባለስልጣን በበኩሉ ቦይንግ ስለችግሩ የኢንዶኔዢያው አየር መንገድ አውሮፕላን ከተከሰከሰ አንደ ወር በኋላ ነው ያሳወቀኝ ብሏል።

ባለስልጣኑ ችግሩን እንደ አነስተኛ ችግር ቢመድበውም ቦይንግ ቀደም ብሎ ማሳወቁ ግን አደጋዎችን ለመከላከል ይጠቅሙ ነበር ብሏል።