ሚድ ዋይፎች( አዋላጅ ሐኪሞች) ስለ እናቶች ቀን ምን ይላሉ?

ነፍሰ ጡር እናት ሐኪም ሲመረምራት Image copyright AFP

ክበር ተመስገን ሚድ ዋይፍ ነው። ለዓመታትም በሚድ ዋይፍነት ለዓመታት እያገለገለ ይገኛል። እርሱ እንደሚለው እናትነትን ሲያስብ እናት ለልጇ የምትሰጠውን ፍቅር ነው የሚያስበው።

የልጃቸውን ደፋሪ የገደሉት እናት ነጻ ወጡ

እንደ ሚድዋይፍ ባለሙያነቱም የማዋለድ አገልግሎቱን ከሰጠ በኋላ ሁልጊዜ የሚያስደንቀው ነገር አለ። ይህም እናቶች በአስጨናቂ ምጥ አልፈው ከወለዱ በኋላ ልጃቸውን ሲያዩ የሚደሰቱት ደስታ የእርሱንም እናት ስለሚያስታውሱት ነው።

በርካታ እናቶችን አዋልጃለሁ የሚለው ክበር በጣም ትልቁ ሕመም እናቶች ልጅ ሲወልዱ የሚሰማቸው ሕመም እንደሆነ ይናገራል። "ያለቅሳሉ...ከአቅማቸው በላይ የሆነ ሕመም ነው የሚያሳልፉት፤ በዚህ ጭንቀት ውስጥ ሆነውም የእናታቸውን ስም ነው የሚጠሩት" ይላል። ይሁን እንጂ ልጃቸውን ሲያገኙ በልጃቸው ፍቅር ተሸንፈው ሕመሙን ይረሱታል፤ ይህም እሱን የሚያስገርመው ጉዳይ ነው።

"በተለይ በእናትና በልጅ መካከል ያለው ፍቅር በዓለም ላይ ልዩ የሆነ ፍቅር ነው፤ እናቶች ለዚህ ዓለም የተሰጡ ስጦታዎች ናቸው" ሲልም ይገልፃል።

በልምድም፤ አንድ መጥፎ ነገር ሊሠራ የነበረን ሰው ከድርጊቱ ለማቀብ አሊያም አንድን ነገር ለመጠየቅ 'በእናትህ ወይም በእናትሽ?' ከተባለ ያ ሰው ይሸነፋል የሚለው ክበር እናትነት የሩህሩህነት ምልክት ነውም ይላል። ቃሉም ብዙዎችን ያሸንፋል።

"እናቴ ሁሉ ነገሬ ናት፤ የእኔ ተንከባካቢ ናት" የሚለው ክበር የሚኖረው በእርሷ ፀሎትና እንክብካቤ እንደሆነም ይናገራል።

"ሰዎች ከወለዱ በኋላ ለልጄ ይላሉ፤ እኔ ግን ወልጄም ለእናቴ ነው የምለው" ብሏል።

የሁለት ልጆች እናት የሆነችው ሰላማዊት ላቀም አዋላጅ ሐኪም (ሚድ ዋይፍ ) ናት። እርሷም እናትነትን "ሁሉ ነገር፤ እንደ ሃገርና እንደ ዓለም ነው የማስባት፤ ሁሉም ነገር የሚጀምረው ከእናት ነው" ትላለች።

"በመጨረሻ ላይ ሳትስመኝ መሄዷ ይቆጨኛል" እናት

ጥሩ በሆነች ሃገር ለመኖር ምቹ እንደሚሆነው ሁሉ ጤናዋ የተጠበቀ እናት ስትኖር ጤናማ ልጆች፣ ጤናማ ትውልድ ይፈጠራል የሚል እምነትም አላት።

"በዓለም ዙሪያ ያሉ እናቶች ምርጥ ናቸው። የኢትዮጵያዎቹ ግን አንደኛ ናቸው" ስትልም ትገልፃቸዋለች። ምክንያቷ ደግሞ ምንም ምቹ ባልሆነ ሃገርና ሁኔታዎች ባልተመቻቹበት ሁኔታ፣ ሕመምን ችለው ትውልድን ማስቀጠላቸው ስለሚያስደንቃት ነው።

"እናቶች በሕይወትና በሞት መካከል ሆነው ነው የሚወልዱት፤ በመሆኑም እየሞቱ ልጆችን መውለድ ነው" ትላለች።

ዊኒ ማንዴላ -አልበገር ባይ እናት

በዚህ ሙያ ለረዥም ዓመታት የሠራው በላይነህ አያናው ስለ እናትነት በጠየቅነው ጊዜ "ሁሉም ነገር ነው ብልሽ ይቀለኛል" ይላል። ስለ ሃገር፣ ስለመኖር፣ ስለ ሁሉም ሲወራ እናት ናት፤ መኖርንና ያለመኖርን የሚወሰነውም በእናት ነው" እንደርሱ አገላለፅ።

አንድ እናት በእርግዝና ጊዜ ካለው ውጥረትና ጫና ጀምሮ በምጥ፣ በወሊድ ጊዜ እንዲሁም ከወለዱ በኋላ በሚኖረው ጊዜ ውስጥ ከእራሷም በላይ እየተጨነቀች ማሰብና ማድረግ ብቻውን ቀላል እንዳልሆነ ይናገራል።

በወሊድ ወቅት ሕይወታቸውን ያጡ እንዳሉ የሚያስታውሰው በላይነህ በተለይ በወሊድ ጊዜ ሕይወትን የሚያስከፍል በርካታ ችግሮች ባሉበት ሁሉ ተቋቁማ ልጇን ወልዳ ስታይ፤ መጨነቅ መጠበቧን ረስታ፤ ለልጇ እንደገና ማሰብ የምትጀምርም ናት ሲል ይገልፃታል። በተለይ እንደ ባለሙያ ከምጥ ጭንቀት ወጥታ ልጇን ስታይ የሚሰማት የደስታ ቅፅበት አይረሳም ይላል።

እንደ ፍጡር ለምድራችን፤ እናት አስፈላጊና ከምንም በላይ መመስገን ያለባት ናት የሚለው በላይነህ እናት ከዚህም በላይ ልትወደስና ልትከበር እንደሚገባ ይመክራል።።

ሁሉም ለመላው እናቶች መልካም ምኞታቸውን ገልፀውልናል።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ