የአርቲስት ፍቃዱ ተክለማርያም ሐውልት ተመረቀ

የተዋናይ ፍቃዱ ተክለማሪያም ሐውልት Image copyright Befekadu Abay

ኦቴሎ፣ ቴዎድሮስ፣ መቃብር ቆፋሪው፣ ባለካባና ባለዳባ፣ ንጉሥ አርማህ፣ የሠርጉ ዋዜማና በሌሎቹም ትያትሮቹ ይታወቃል። ገመና፣ ባለ ጉዳይ እና ሌሎችም የቴሌቪዥን ተከታታይ ድራማዎቹ በርካቶች ያስታውሱታል - አንጋፋው አርቲስት ፍቃዱ ተክለማርያም።

አርቲስቱ ባደረበት የኩላሊት ሕመም በተወለደ በ62 ዓመቱ ሕይወቱ ያለፈው ባለፈው ሐምሌ ወር ነበር። ሐውልቱም ዛሬ ግንቦት 4/ 2011 ዓ.ም በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በሚገኘው መካነ መቃብሩ ላይ ሐውልት ቆሞለታል።

ቀራፂው ስለ አፄ ኃይለ ሥላሴ ሐውልት ይናገራል

አርቲስት ፍቃዱ ተክለማርያም የኩላሊት ሕመም አጋጥሞት ሳለ የሕክምና ገንዘብ ሲያሰባስብ የነበረው ኮሚቴ ዋና ሰብሳቢ አርቲስት ቴዎድሮስ ተስፋዬ ለቢቢሲ እንደገለፀው ዛሬ ከጠዋቱ 1፡00 ላይ ታላላቅ የኪነጥበብ ባለሙያዎች፣ አድናቂዎቹና ቤተሰቦቹ በተገኙበት ሐውልቱ ተመርቋል።

ሐውልቱ ከ'ፋይበር ግላስ' የተሠራ ሲሆን በሠዓሊና ቀራፂ ተፈሪ መኮንን ተቀርጿል።

አርቲስት ቴዎድሮስ ምን ያህል ወጪ እንደወጣ ለጊዜው መግለፅ እንደሚከብደው ቢናገርም "አርቲስት ፍቃዱ ከማረፉ በፊት ለኩላሊት ታማሚዋ ከሰጠው ገንዘብ ጋር ተደምሮ በዚህኛው ኮሚቴ የሂሳብ ቁጥር ከሚገኝ ገንዘብ ወደ 700 ሺህ ብር ገደማ ወጥቶበታል" ብሎናል።

መነኩሴው ለምን በቁጥጥር ሥር ዋሉ?

በሐውልቱ ላይ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ፣ የተወለደበትና ያረፈበት ዓ.ም የተፃፈ ሲሆን መጨረሻ ላይ ግን " ይህንን ሐውልት የኢትዮጵያ ሕዝብ አሠሩላቸው" የሚል ሰፍሮበታል። ይህም ከኢትዮጵያ ሕዝብ በተሰባሰበው ገንዘብ መሠራቱን ለመግለፅ ታስቦ እንደተፃፈ ነግሮናል።

በመጨረሻም አርቲስት ቴዎድሮስ፤ የተውኔት አባት ተዋናይ ወጋየሁ ንጋቱ ሐውልት መፍረሱንና ሐውልቱ የት እንዳለ እንደማይታወቅ ገልፆ፤ የተዋናይ ፍቃዱ ተክለማሪያም ሐውልትም ለበርካታ ዓመታት ባገለገለበት ትያትር ቤት ቢቆም ጥሩ ነበር ሲል ሃሳቡን ይገልፃል።

"መካነ መቃብሩ ላይ ማስታወሻ ቆሞ፤ ሐውልቱ የሠራበት ትያትር ቤት ቅጥር ግቢ ውስጥ ቢቆም ምንኛ ደስ ባለኝ፤ ብዙ ሺህ ሰው ያየው ነበር" ሲልም አክሏል።

ይሁን እንጂ አሁንም የመድረኩ ንጉስ አርቲስት ፍቃዱ ተክለማርያም በዚህ መልኩ መታሰቡ ደስታ የሚሰጥና የሚገባውም ነው ብሏል።

ገንዘብ ለማሰባሰብ ተዋቅሮ የነበረው ኮሚቴ አባላት ውዝግብ ውስጥ እንደገቡ የሚታወስ ሲሆን አርቲስት ቴዎድሮስ ተስፋዬ እንደነገረን 'ዋናው ኮሚቴ (መጀመሪያ የተዋቀረው ኮሚቴ)' ከዛሬ ጀምሮ ኮሚቴው መፍረሱን በማሳወቅ የምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ተጠናቋል።

ተያያዥ ርዕሶች

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ