ኒፕሲ ሃስል፡ በቤተሰቡ ላይ ማስፈራሪያ የደረሰበት ጠበቃ ሥራውን አቋረጠ

ኒፕሲ ሃስል Image copyright Getty Images

ኒፕሲ ሃስልን በመግደል የተጠረጠረው ግለሰብ ጠበቃ በሥራው እንደማይቀጥል አስታወቀ። ጠበቃ ክሪስ ዳርደን እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው ልጆቹንም ጨምሮ በቤተሰቡ ላይ 'ማስፈራሪያ' እየደረሰበት በመሆኑ እንደሆነ ተናግሯል።

የኒፕሲ ሐስል ግድያ ተጠርጣሪ በቁጥጥር ሥር ዋለ

በትውልዱ ኤርትራዊና የሎስ አንጀለስ ነዋሪ ሙዚቀኛ ኒፕሲ ሃስል ወይም ኤርምያስ አስገዶም ከሁለት ወራት በፊት የተገደለው በራሱ መደብር በር ላይ እንደነበር ይታወሳል።

በመግደል የተጠረጠረውና የሞት ፍርድ የሚያሰጋው የ29 ዓመቱ ኤሪክ ሆልደር የፍርድ ቤት ውሳኔውን እየተጠባበቀ ይገኛል።

Image copyright Getty Images
አጭር የምስል መግለጫ ክሪስ ዳርደን (ግራ) የኤሪክ ሆልደር (ቀኝ) ጠበቃ ነው።

ክሪስ ዳርደን በፌስቡክ ገፁ ላይ ስማቸውን ሳይጠቅሱ ሲያስፈራሩት የነበሩትን ሰዎች "ቦቅቧቆች" ሲል ወርፏቸዋል። ይሁን እንጂ የጥብቅና ሥራውን የማቆም ሃሳብ እንደሌለው የተናገረው ክሪስ ለኤሪክ ሆልደር ጥብቅና መቆሙን ግን እንደሚያቋርጥ አስታውቋል።

"በዚህ ዘመን አንድን ጥቁር ወጣት መብቱን ለመከልከል የሚሯሯጡ መኖራቸው ሊገባኝ አልቻለም" ሲል ለተጠርጣሪው ጥብቅና መቆሙ ፈተና እንደሆነበት ተናግሯል።

አክሎም ጥበቅና በመቆሙ እርሱ ላይ ማስፈራሪያ ቢደርሰውም ከእሱ አልፎ በልጆቼ እንዴት ይመጣሉ ብሏል።

በሁለት ትውልደ ኢትዮጵያውያን ግድያ የሚፈለገው ለአሜሪካ ተላልፎ ተሰጠ

ተጠርጣሪው ኤሪክ ሆልደር ለጊዜው በፖሊስ ቁጥጥር ሥር የዋለ ሲሆን ጥፋተኛ አይደለሁም ሲል ቃሉ ሰጥቷል። ፍርድ ቤቱ ደግሞ የ5 ሚሊየን ዶላር ዋስ ወስኗል።

ክሪስ ዳርደን የተከበረና ታዋቂ የአሜሪካ ጠበቃ ነው። በፈረንጆቹ 1995 በዓለም ገናና በነበረው የኦጄ ሲምፕሰን ጉዳይም አቃቤ ሕግ ነበር።

የቀድሞ አሜሪካን ፉትቦል ተጫዋች የነበረው ኦጄ ሲምፕሰን በሚስቱ ኒኮልና በጓደኛዋ ሮናልድ ጎልድማን ሞት ጥፋተኛ አይደለህም ተብሎ መለቀቁ የሚታወስ ነው።

ጠበቃ ክሪስ ያኔም ቢሆን ብዙ ማስፈራሪያዎችን አስተናግዶ እንደነበርና አሁንም ነገሮች እምብዛም አለመቀየራቸው እንደገረመው ይናገራል።

"ዘንድሮ እነዚህ 'ቦቅቧቆች' በደብዳቤ ሳይሆን ከኮምፕዩተር በስተጀርባ ተቀምጠው ነው፤ አንድን ሰው ከነልጆቹ የሚያስፈራሩት" ይላል።

"ለአንዳንድ ሰዎች አስቂኝ ሊሆን ይችላል። እኔ ግን አልስቅም ደግሞም አልረሳውም። ውሸታቸውም ሆነ ማስፈራሪያዎቻቸው ከሥራዬ አያሰናክሉኝም" ሲል ቁርጠኝነቱን ያሳያል።

Image copyright Shareif Ziyadat
አጭር የምስል መግለጫ ድሬክ (ግራ)፣ ኒፕሲ ሃስል (መካከል)፣ ቲአይ (ቀኝ)

በኒፕሲ ሞት እንደ እነ ድሬክ፣ ሪሃና እና ጄ ኮል ያሉ አርቲስቶች የሃዘን መልዕክታቸው አስተላልፈዋል።

ድሬክ "የተከበረ ሰው፤ አለቃ ነው" ሲል የገለፀው ሲሆን ሪሃና ደግሞ በትዊተር ገጿ ላይ ሕልፈቱን ማመን እንዳልቻለች ተናግራ መንፈሴ ታውኳል ብላለች።

በሎስ አንጀለሱ ማራቶን በተሰኘው የልብስ መደብር በራፍ ላይ በተከፈተው ተኩስ ሁለት ሌሎች ሰዎችም ተጎድተዋል።

ሙዚቀኛው ኒፕሲ በዚያው ተኩስ ላይ በጭንቅላቱና በደረቱ በተተኮሱት ጥይቶች ምክንያት መሞቱን ተከትሎ የሎስ አንጀለስ ፖሊስ ግድያ መሆኑን ደምድሟል።

ተያያዥ ርዕሶች

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ