የሠላም ተጓዧ ሉሲ (ድንቅነሽ) ምን ደረሰች?

ሉሲ (ድንቅነሽ) Image copyright Getty Images

በአገሪቱ በተለያዩ ጊዜያት የሚፈጠሩ የብሔር ግጭቶችን ለመፍታት የተለያዩ እንቅስቃሴዎች እየተከናወኑ ይገኛል። ከእነዚህም መካከል ሉሲ (ድንቅነሽ) ቅሪተ አካል በተለያዩ ክልሎች ' ጉዞ ሉሲ ለሠላምና ፍቅር' የተሰኘ ጉዞ ስታደርግ ቆይታለች።

ጉዞውን በተመለከተም አንዳንዶች "ስለ ሠላም ለመስበክ ሉሲን ይዞ መጓዝ አያስፈልግም፤ ሌሎች በርካታ መንገዶችን መጠቀም ይቻላል" ሲሉ ተችተውታል፤ ቀልድ የሰነዘሩም አልታጡም።

ሌሎች ደግሞ 'ያልተለመደ በመሆኑ ሰዎች ትኩረት ሊሰጡት ይችላሉ፤ በሚኖሩት ዝግጅቶች ትምህርት ሊወስዱ ይችላሉ' የሚል አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

በባህል ቱሪዝም ሚንስቴር የቋንቋና የባህል ቱሪዝም እሴቶች ልማት ዳይሬክተር አቶ አለማየሁ ጌታቸው የጉዞው ዓላማ አገሪቱ ያለችበት ነባራዊ ሁኔታና በየአካባቢው ያሉ ግጭቶቹም ወደ ብሔር ተኮር እያደላ በመምጣቱ ሉሲን እንደ አንድ ነን ማሳያነት ለመጠቀም ነው ብለዋል።

የስኳር ፋብሪካዎችን ለግል ባለሃብቶች የመስጠት ፋይዳና ፈተናዎቹ

አቶ ታደሰ "በዚህ ወቅት ዋስትና አልጠይቅም" አሉ

'ቅሽለት' ስለሚባለው የአእምሮ ጤና ችግር ያውቃሉ?

" ኃይማኖታችንና ፍጥረታችንም የተለያየ ቢሆንም ጠቅላላ የዓለም ህዝብ መነሻው እኛ ነን ፤ አንድ ነን ለማለት ነው " ሲሉ ዓላማውን ያስረዳሉ።

ይህንንም መልዕክት ለማስተላላፍ ሉሲን እንደምክንያት ተጠቀምን እንጂ ሌሎች ዝግጅቶችም መኖራቸውን አክለዋል።

ይህንን መልዕክት መሠረት አድርጎ ሙዚቃዊ ድራማዎች፣ ከጥንት የዘር አመጣጥ፣ ከስፖርታዊ ጨዋነትና ከባህል እሴት ጋር የቀረቡ ጥናታዊ ፅሁፎች እንዲሁም አነቃቂ ንግግሮች በኃይማኖት መሪዎችና በዩኒቨርሲቲ መምህራን ይቀርባል።

Image copyright Anadolu Agency

" ሠላማችንን፣ አንድነታችንንና ፍቅራችንን እንደ ቀደመው ማስቀጠል አለብን" የሚል ሃሳብ የያዘ እንደሆነም ይናገራሉ። ዳይሬክተሩ እንዳሉት ክንውኑ በታዳሚዎች ተቀባይነትን አግኝቷል።

ከዚህም በተጨማሪ ከጥንታዊ የድንጋይ ዘመን፣ ቁሳቁሶችና የሰው ልጅ የእድገት ደረጃን ከሉሲ ጋር በማያያዝ የቀረበ የጥበብ ሥራም ነበር።

በዚህም በየክልሎቹ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መሳተፋቸውን ኃላፊው ገልፀዋል።

ዓላማው አሳክቷል ወይ ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄም " በመድረኮቹ ላይ የተንፀባረቀው፤ ተሳታፊዎች ' የችግሩ ባለቤት ነኝ' በማለት ችግሩን ወደ ራሳቸው ወስደዋል" ብለዋል።

በጉዞው ከኢትዮጵያ ብሮድካስት ኮርፖሬሽን፣ ከብሔራዊ ቲያትር ቡድን፣ ከቅርስ ጥናትና ጥበቃ፣ ከባህልና ቱሪዝም ቢሮ፣ ከከፍተኛ ትምህርትና ሳይንስ ሚንስቴር፣ እንግዶችንና አነቃቂ ንግግር የሚያደርጉ ግለሰቦችን ጨምሮ 80 ሰዎች ተሳትፈዋል።

ይሄው የሉሲ (ድንቅነሽ ጉዞ) በመላ አገሪቱ በሚገኙ ክልሎች እንደሚቀጥል የሚታወቅ ቢሆንም አሁን ላይ ግን አዲስ አበባ ተመልሳለች።

ጉዞዋን አቋርጣ የመመለሷ ምክንያት የተጠየቁት ኃላፊው ጉዞው ያልተቋረጠ መሆኑን ገልፀው በጉዞው የተሳኩና ያልተሳኩ ጉዳዮችን አንጥሮ ለማውጣትና ክፍተቶቹን ለመሙላት ታስቦ የተወሰደ እረፍት እንደሆነ ገልፀዋል።

ይሁን እንጂ ለእረፍትና ለግምገማ ቀድሞ የተያዘ መርሃ ግብር አልነበረም።

የሉሲ(ድንቅነሽ) ጉዞ

ሉሲ ወደተለያዩ የአገሪቱ ክልልሎች ጉዞዋን ለማድረግ በተነሳችበት የካቲት 11 ቀን 2011 ዓ.ም በኢፌዴሪ የተወካዮች ምክር ቤት አሸኛኘት ተደርጎላታል። የክልሎቹ ቅደም ተከተል ከክልሎቹ ዝግጁነት ጋር በተያያዘ እንደሆነ ዳይሬክተሩ አቶ አለማየሁ ገልፀውልናል።

አፋር

ሉሲ የመጀመሪያ ጉዞዋን ያደረገችው ወደ አፋር ክልል ነበር። በዚያም የተለያዩ ትዕይንቶችና የኪነ ጥበብ ዝግጅቶች ለተከታታይ 5 ቀናት በሠመራ፣ ሎጊያ ሀዳር ወደ ተባለው ቦታም ተንቀሳቅሳ በሕዝቡ ተጎብኝታለች።

ሶማሌ

ቀጣይ ጉዞዋን ሶማሌ ክልል ጅግጅጋ አድርጋም በተመሳሳይ ለአምስት ተመሳሳይ ቀናት ቆይታ አድርጋለች። በወቅቱም በርካታ ምሁራንና የከተማዋ ነዋሪዎች የጎበኝዋት ሲሆን ጥናታዊ ፅሁፍም ቀርቧል።

ሐረር

የሉሲ የሐረር ጉዞ ለየት ይላል ይላሉ ኃላፊው። ምክንያታቸው ደግሞ ሉሲ ከአዲስ አበባ ወደ ሠመራ፤ ከሠመራ ወደ አዲስ አበባ ተመልሳ፤ ወደ ሶማሌ ክልል የሄደችው በአውሮፕላን ነበር። ነገር ግን ከጂግጅጋ ከተማ ወደ ሐረር የተጓዘችው በየብስ ትራንስፖርት ነበር። ይህም ለየት ያደርገዋል ብለዋል።

ከጂግጅጋ በከፍተኛ አጀብ የተሸኘችው ሉሲ በሐረር ከተማ የአምስት ቀናት ቆይታ ያደረገች ሲሆን በከተማዋና በሐሮማያ ዩኒቨርሲቲ የተለያዩ ዝግጅቶችም ተከናውነዋል።

ግንቦት 15 ቀን 2011 ዓ.ም በሚጀምረው ሁለተኛ ዙር ጉዞ ሉሲ አዲስ አበባን ጨምሮ ወደ ሰባት የክልል ከተሞች ጉዞ የምታደርግ ሲሆን ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም ድረስ ጉዞው እንደሚጠናቀቅ ገልፀውልናል።

ለዚህ ጉዞ የተመደበው በጀት በውል ባይታወቅም፤ ከፍተኛ እንደሆነ ግን ነግረውናል።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ