ሱዳን፡ ኦማር አል በሽር በተቃውሞው በደረሰ ሕይወት መጥፋት ተከሰሱ

የቀድሞው የሱዳን ፕሬዚዳንት ኦማር ሀሰን አል ባሽር Image copyright AFP
አጭር የምስል መግለጫ ኦማር አል በሽር ከሥልጣን ከወረዱ በኋላ አልታዩም

የቀድሞው የሱዳን ፕሬዚደንት ኦማር አል በሽር በተቃውሞ ወቅት በደረሰ የሕይወት መጥፋት ክስ እንደቀረበባቸው የሱዳኑ አቃቤ ህግ አስታወቀ።

ሱዳን ውስጥ የዳቦና የነዳጅ ዋጋ ንሮብናል ያሉ ዜጎች ከፖሊስ ጋር ተጋጩ

አል-በሽር ካቢኔያቸውን በተኑ

ባለፈው ወር በሕዝባዊ ተቃውሞ ከሥልጣን የወረዱት ፕሬዚዳንቱ የተከሰሱት በሕዝባዊ አመፁ ወቅት ከተገደለ አንድ ዶክተር ግድያ ጀምሮ ከሥልጣን እስኪወርዱ ድረስ የእርሳቸውን አስተዳደር በመቃወም አደባባይ በመውጣት ሕይወታቸው ያጡ ዜጎችን ጉዳይ ያካትታል።

አንድ የአይን እማኝ አመፁ በተቀሰቀሰ አምስት ሳምንታት ውስጥ በተቃዋሚዎቹ ላይ ተኩስ እንደተከፈተና በዚህም አንድ ዶክተር እንደተገደለ ተናግሯል።

አጋጣሚውን ሲያስረዳም ዶክተሩ ካርቱም በሚገኘው መኖሪያ ቤቱ ጉዳት ያጋጠማቸውን ተቃዋሚዎች እያከመ የነበረ ሲሆን ፖሊስ በሕንፃው ላይ አስለቃሽ ጭስ ይተኩሳል።

በዚህም ጊዜ ዶክተሩ ከቤት እንደወጣና እጆቹን ወደ ላይ ከፍ በማድረግ ዶክተር እንደሆነ በመግለፅ ላይ ሳለ ነበር ከፖሊስ በተተኮሰ ጥይት ሕይወቱ ያለፈው።

የቀድሞ የመንግስት ባለስልጣናት በቁጥጥር ስር ዋሉ

ከዚያ በኋላም ተቃዋሚዎቹ በወታደራዊ መሥሪያ ቤቱን በመክበብ ወታደራዊ ኃይሉ ፕሬዚደንቱን እንዲያወርዱላቸው መጠየቅ የጀመሩት።

ወታደራዊ ምክርቤቱ ሥልጣኑን እንደሚቆጣጠር ከታወቀም በኋላ ተቃዋሚዎቹ የሲቪል መንግሥት እንሻለን ሲሉ ግፊት ሲያደርጉ ቆይተዋል።

የቀድሞ ፕሬዚደንቱ በሕገ ወጥ የገንዘብ ዝውውርና ሽብርተኛን በመደገፍ ወንጀል ምርመራ እየተደረገባቸው ነውም ተብሏል።

አልበሽር ከሥልጣን ከወረዱ በኋላ የት እንዳሉ ባይታወቅም በእስር ላይ እንደሚገኙ ተገልጿል።

ባለፈው ታኅሳስ ወር የሱዳን መንግሥት በዳቦ ላይ ሦስት እጥፍ የዋጋ ጭማሬ ማድረጉን ተከትሎ የተቀሰቀሰው አመፅ ሃገሪቷን ለ30 ዓመታት የመሩት ፕሬዚዳንት ከሥልጣን እንዲወርዱ ትልቅ ህዝባዊ ቁጣን ማስነሳቱ ይታወሳል።

የወታደራዊ መንግሥቱና የተቃዋሚዎች ስምምነት

ሰኞ ዕለት የተቃዋሚዎች ጥምረትና አገሪቷን እየመራ ያለው ወታደራዊ መንግሥት በሽግግሩ ወቅት ስለሚኖረው የሥልጣን ተዋረድ ሥምምነት ላይ ደርሰዋል።

የተቃውሞ እንቅስቃሴው ቃል አቀባይ ታሃ ኦስማን " በዛሬው ስብሰባችን የሥልጣን ተዋረዱና ክፍፍሉ ላይ ስምምነት ላይ ደርሰናል" ሲሉ ለኤ ኤፍ ፒ የዜና ወኪል ገልፀዋል።

የስልጣን ተዋረዱም የከፍተኛው ምክርቤት፥ የካቢኔት ምክርቤት እና የሕግ አውጭው አካል እንደሆነ ዘርዝረዋል ቃል አቀባዩ።

ወታደራዊ ምክርቤቱም በበኩሉ በሽግግር መንግሥቱ የሥልጣን ተዋረድ ላይ ሥምምነት ላይ መድረሱን አስታውቋል።

ሁለቱ አካላት ዛሬ በሚኖራቸው ስብሰባ የሽግግር መንግሥቱ ለምን ያህል ጊዜ እንደሚቆይና በሥልጣን መዋቅሩ የሚካተቱ አካላት ኃላፊነት ላይ ስምምነት እንደሚደርሱ ይጠበቃል።

ጄኔራሎቹ የሽግግሩ ወቅት ሁለት ዓመት መሆን አለበት ቢሉም ተቃዋሚዎች አራት ዓመታት እንዲሆን ይፈልጋሉ።

ተያያዥ ርዕሶች

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ