ኢንዶኔዥያ፡ እናት አልባዎቹ መንደሮች

ኤሊ ሱሲያዋቲ

በምስራቃዊ ኢንዶኔዢያ በሚገኙ መንደሮች አብዛኛዎቹ ወጣት እናቶች ለተሻለ ስራና ህይወት ፍለጋ ልጆቻቸውን ትተው ወደውጪ ሃገራት ተሰድደዋል።

የሃገሬው ሰውም እነዚህን አካባቢዎች 'እናት አልባዎቹ መንደሮች' ይላቸዋል።

ኤሊ ሱሲያዋቲ እናቷ ጥላት ስትሄድ ገና የ11 ዓመት ልጅ የነበረች ሲሆን አያቷ ናቸው የሚያሳድጓት።

የኤሊ እናት ማርቲያና ከባለቤቷ ጋር ከተፋታች በኋላ ልጇን በተሻለ ሁኔታ ለማሳደግና ቤተሰቦቿን ለመርዳት በማሰብ ሳዑዲ አረቢያ ውስጥ በቤት ሰራተኝነት ለመቀጠር ወሰነች።

ቄሮ፣ ሴታዊት፣ ፋኖ…የትውልዱ ድምጾች

ኤሊ በአስራዎቹ እድሜ ክልል ውስጥ የምትገኝ ሲሆን እናቷ አብራት አለመኖሯ ብዙ ነገር እንዳጎደለባት ትናገራለች።

''ትምህርት ቤት ውስጥ ቤተሰብ ያላቸው ጓደኞቼን ስመለከት እጅጉን አዝናለሁ። እናቴ መቼ ነው የምትመጣው እያልኩ በጣም እጨነቃለሁ።'' ትላለች።

ኤሊ የምትኖርባትና በምስራቃዊ 'ሎምቦክ' የምትገኘው መንደር 'ዋናሳብ' ትባላለች።

በዚች መንደር እናቶች የልጆቻቸውን ፍላጎት ለማሟላትና የተሻለ ህይወት ለመምራት ወደ ውጪ ሃገራት መሄድ የተለመደና የሚበረታታ ነገር ነው።

አብዛኛዎቹ ወንዶች ደግሞ በግብርና ስራ የሚተዳደሩ አልያም በቀን ስራ ህይወታቸውን የሚገፉ ናቸው። ገቢያቸው ሴቶቹ ወደውጪ ሃገራት ሄደው ከሚልኩት ገንዘብ ጋር ሲወዳደር ደግሞ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም።

በመንደሯ እናቶች ወደውጪ ሃገራት ሲሄዱ ቤተዘመድ ሰብሰብ ይልና ልጆቻቸውን እንዴት እንደሚያሳድጉላቸው ይመክራል። ሁሉም የቤተሰብ አባል ልጆቹን የመንከባከብ ሃላፊነት አለበት።

ነገር ግን እናቶቻቸውን ለሚሰናበቱት ልጆች ምን ያህል ከባድ ሊሆን እንደሚችል መገመት አይከብድም።

ካሪማቱል አዲቢያ እናቷ ጥላት ስትሄድ ገና የአንድ ዓመት ልጅ የነበረች ሲሆን እንደገና የተገናኙትም የ12 ዓመት ታዳጊ እያለች ነው።

'' ልክ እንዳየኋት ግራ ተጋባሁ። ማን እንደሆነች አላውቅም። እናቴ ስታለቅስ አስታውሳለሁ። ለምን የእኔ ልጅ እንደሆነች አትረዳም እያለች አያቴን ትጠይቅ ነበር።'' ትላለች።

ካሪማቱል እናቷን ለመጀመሪያ ጊዜ እስከምታያት ድረስ ፎቶዋን እንኳን ተመልክታ አታውቅም። ሙሉ እድሜዋን ያሳለፈችው በአክስቷ ባይቅ ቤት ነው።

ባይቅ በቤቷ ውስጥ ዘጠኝ ልጆችን ታሳድጋለች። ከዘጠኙ ግን የእርሷ የሆነው አንድ ልጅ ብቻ ነው። ካራማቱልን ጨምሮ ስምንቱ ስራ ፍለጋ ወደሌላ ሃገር የሄዱ የእህቶቿ ልጆች ናቸው።

ሜድ ኢን ቻይና- የሀገር ባህል አልባሳቶቻችን

በአንዳንድ ሃገራት ጉርሻ መስጠት እንደ ስደብ እንደሚቆጠር ያውቃሉ?

የኢንዶኔዢያ ሴቶች ወደተለያዩ ሃገራት ስራ ፍለጋ መሄድ የጀመሩት በጎርጎሳውያኑ አቆጣጠር 1980ዎቹ ውስጥ ሲሆን አብዛኛዎቹ ለጥቃትና ሌሎች ተዛማጅ ችግሮች የተጋለጡ ናቸው።

ስራ ፍለጋ ዘመድ አዝማድ ተሰናብተው፤ ልጆቻቸውን ለቤተሰብ አደራ ሰጥተው ወደ ውጪ ሃገራት የሄዱና በሬሳ ሳጥን የተመለሱ ብዙዎች መሆናቸውን 'የዋናሳብ' መንደር ነዋሪዎች ይናገራሉ።

ጾታዊ ጥቃት ይደርስባቸዋል፤ ይደበደባሉ አንዳንዴም የሰሩበት ደመወዝ ሳይከፈላቸው ይባረራሉ።

በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ አንዳንዶቹ ደግሞ ሌሎች ልጆች ወልደው ይመጣሉ። ብዙ ጊዜ በአሰሪዎቻቸው ጾታዊ ጥቃት ደርሶባቸው ነው ልጆቹን የሚወልዷቸው።

የተሻለ ስራ ፍለጋ በተለይ ወደ አረብ ሃገራት ከሚሄዱት ኢንዶኔዢያውያን መካከል ሁለት ሶስተኛውን ቦታ የሚይዙት ሴቶች ሲሆኑ የሚልኩት ገንዘብ ደግሞ ተተኪው ትውልድ ወደ ትምህርት ቤት የመሄዱንና ያለመሄዱን እድል እስከመወሰን ይደርሳል።

ኤሊ እናቷን ለዘጠኝ ዓመታት አላየቻትም፤ ነገር ግን የሚላከው ገንዘብ ቤተሰቡ ምግብ በልቶ ማደሩን ከማረጋገጥ አልፎ ዩኒቨርሲቲ የገባች የመጀመሪያዋ የቤተሰብ አባል መሆን አስችሏታል።

የምግብ ምርጫዎ ስለማንነትዎ ይናገራል?

በአሁኑ ወቅት ኢስላማዊ የገንዘብ አስተዳደር በማጥናት ላይ የምትገኘው ኤሊ እናቷ ያደረገችላትን ነገር መገንዘብ የጀመረች ትመስላለች።

''እሷ ወደ አረብ ሃገር ባትሄድ ኖሮ ቤተሰባችን ምን ይውጠው እንደነበር አላውቅም። ትምህርቴንም መከታተል እንደማልችል ይሰማኛል'' ትላለች።

'' ቤተሰቦቻችን የተማሩ ስላልነበሩ ይህንን መንገድ መርጠዋል። እኛ ደግሞ ተምረን የተሻለ ህይወት እንደምንመራ ተስፋ አደርጋለሁ። ጥሩ ህይወት ለመኖርና ፍላጎቶቻችንን ለማሟላት ወደውጪ ሃገራት የግድ መሄድ የለብንም።''