ሱዳን፡ ወታደራዊ ምክርቤቱና ተቃዋሚዎች በሦስት ዓመታት የሽግግር ጊዜ ተስማሙ

በሱዳን ካርቱም በነበረው ተቃውሞ ሰልፎኞች የተለያዩ መፈክሮችን ይዘው ያሳያል Image copyright AFP

በሱዳን ወታደራዊ ምክርቤቱና የተቃዋሚዎች ጥምረት የሲቪል መንግሥት ለመመስረት በሦስት ዓመታት የሽግግር ጊዜ ሥምምነት ላይ መድረሳቸውን የሱዳን ወታደራዊ መሪዎች አስታውቀዋል።

የሽግግር ወታደራዊ ምክርቤቱ እንዳለው የተቃዋሚዎች ጥምረት በሕግ አውጭው ምክር ቤት ሁለት ሦስተኛ መቀመጫ ይኖራቸዋል።

ሱዳን ባለፈው ወር ፕሬዚዳንት ኦማር አል በሽር ከሥልጣን ከወረዱበት ጊዜ አንስቶ በወታደራዊ የሽግግር መንግሥት እየተመራች ነው።

ይሁን አንጂ ወታደራዊ መንግሥት ወርዶ የሲቪል መንግሥስት እንዲመራቸው የሚጠይቁ ተቃውሞዎችም አሁንም መሰማታቸውን ቀጥለዋል።

ይህ ሥምምነት ከተነገረ በኋላ እንኳን እዚያው ካርቱም በተፈጠረ ግጭት አምስት የፀጥታ ኃይል አባላት ተገድለዋል።

በሱዳን በተቀሰቀሰ ግጭት ቢያንስ ሰባት ሰዎች ሞቱ

በምን ተስማሙ?

በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የሥልጣን ክፍፍሉ በተመለከተ ያለው የመጨረሻው ሥምምነት ከተቃዋሚ ጥምረት - ዲክላሬሽን ኦፍ ፍሪደም ኤንድ ቼንጅ ፎርስ ((DFCF) ጋር በሃያ አራት ሰዓታት ውስጥ እንደሚፈራረሙ ሌተናንት ጀነራል ያሰር አል አታ ተናግረዋል። ይህም ምርጫ እስከሚደርስ ድረስ አገሪቷን የሚመራ አዲስ ከፍተኛ ምክር ቤት መመሥረትንም ያካትታል።

ሥምምነቱ በ24 ሰዓታት ውስጥ እንደሚጠናቀቅና የሕዝቡን ፍላጎት እንደሚያሟሉ ሌተናንት ጀኔራሉ አክለዋል።

አል-በሽር ካቢኔያቸውን በተኑ

ጄነራል አታ እንዳሉት ዲኤፍ ሲ ኤፍ በሽግግሩ ሕግ አውጭው ምክር ቤት ካለው 300 መቀመጫ ሁለት ሶስተኛውን ይይዛል። ሌሎች ቀሪዎቹ ደግሞ በሌሎች ፓርቲዎች የሚያዙ ይሆናሉ ተብሏል።

የተቃውሞ እንቅስቃሴው መሪ ቃል አቀባይ ታሃ ኦስማን ሁለቱም አካላት በቀጣይ ስለሚኖራቸው የሥልጣን መዋቅርና ክፍፍል በተመለከተም፤ ከፍተኛው ምክር ቤት፣ ካቢኔት ፥ ሕግ አውጭው አካል እንደሚሆኑም ሥምምነት ላይ ተደርሷል።

የዲ ኤፍ ሲ ኤፍ አባል የሆኑት ሳቴ አል ሃጂ የመጨረሻው የሥምምነቱ ዝርዝር በሥልጣን ክፍፍሉ ላይ የሚኖረው ሥምምነት ተስፋ ሰጭ እንደሚሆን ተናግረዋል።

ወታደራዊ ምክር ቤቱ ሁለት ዓመት የሽግግር ጊዜ የተቀዋሚ መሪዎች ደግሞ አራት ዓመታት ጊዜ ይፈልጉ እንደነበር መናገራቸው ይታወሳል።

ተያያዥ ርዕሶች

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ