ሰሜን ኮሪያ፡ በ37 ዓመት ታሪክ ያልታየ ከባድ ድርቅ አጋጠሟታል

ሰሜን ኮሪያ Image copyright WFP

ሰሜን ኮሪያ በ37 ዓመት ታሪክ እጅግ ከባድ የተባለ ድርቅ እንደገጠማት ይፋ አድርጋለች። በድርቁ ምክንያትም ሰብሎች ደርቀዋል፤ ዜጎች የሚበሉትን ለማግኘትም ተቸግረዋል።

የተባበሩት መንግሥታት እንዳስታወቀው፤ አስር ሚሊየን የሚደርሱ ሰሜን ኮሪያውያን አስቸኳይ የምግብ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ሲሆን፤ በዚህ ዓመት እያንዳንዱ ሰሜን ኮሪያዊ የእለት የምግብ ፍላጎቱን ለማርካት 300 ግራም ምግብ ብቻ ነው የሚያገኘው።

የሕንድ 21 ሚሊዮን 'ያለተፈለጉ' ሴት ልጆች

በአውሮፓውያኑ 1990 አካባቢ ባጋጠመ ረሃብ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰሜን ኮሪያውያን ህይወታቸው አልፏል። መረጃዎች እንደሚያሳዩት፤ ሀገሪቱ 1.5 ሚሊየን ቶን ምግብ ከውጪ ሀገራት ማስገባት አለባት።

የሰሜን ኮሪያው የመንግሥት ቴሌቪዥን ጣቢያ 'ኬሲኤንኤ' እንደዘገበው፤ በያዝነው ዓመት የመጀመሪያ አምስት ወራት ውስጥ እጅግ ዝቅተኛ ዝናብ የዘነበ ሲሆን፤ ከአውሮፓውያኑ 1982 ጀምሮ አነስተኛው መጠን ነው።

ረሃብ የቀሰቀሰው ፈጠራ

በ2018 ሃገሪቱ ያመረተችው ምርትም እጅግ ዝቅተኛ የሚባል እንደሆነ የዓለም ምግብ ፕሮግራም አስታውቋል።

ከ2006 ጀምሮ ሰሜን ኮሪያ ላይ የተጣለው ማዕቀብ ሃገሪቱ ምርቶቿን ለውጪ ሃገራት ሸጣ የውጭ ምንዛሪ እንዳታገኝ ከልክሏት ቆይቷል።

የሰሜን ኮሪያ መንግሥት ባጋጠመኝ ውጭ ምንዛሪ እጥረት ምክንያት ምግብን ጨምሮ ሌሎች አስፈላጊ ቁሳቁሶችን ወደሃገር ውስጥ ማስገባት አልቻልኩም በማለት በተደጋጋሚ አስታውቋል።

ከሁለት ዓመት በፊት መጠኑ አነስተኛ ቢሆንም ቀላል የማይባል ጉዳት ያደረሰ ድርቅ ሃገሪቱ ገጥሟት የነበረ ሲሆን እንደ ሩዝ፣ በቆሎ፣ ድንችና አኩሪ አተር ያሉ ዋነኛ ምርቶቿ ቀንሰው ነበር።

ቀኝ እጇን ለገበሬዎች የሰጠችው ኢትዮጵያዊቷ ሳይንቲስት

አሁን ያጋጠማት ድርቅ እጅጉን የከፋ ሲሆን፤ ብዙ ዜጎች በምግብ እጥረት ምክንያት ህይወታቸው ሊያልፍ እንደሚችልም ተዘግቧል።

የሰሜን ኮሪያ አብዛኛዎቹ የግብርና መሣሪያዎች ኋላ ቀርና ብዙ ማምረት የማይችሉ ስለሆኑ እንደዚህ አይነት ተፈጥሯዊ እክሎች ሲያጋጥሙ የአርሶ አደሮች ምርት በእጅጉ ያሽቆለቁላል።