ትራምፕ፡ "ወጣትና የተማሩ ስደተኞችን እንቀበላለን"

ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ Image copyright Reuters

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ስደተኞችን በተመለከተ ባስተዋወቁት አዲስ ሕግ ወጣት፣ በደንብ የተማሩና እንግሊዝኛ መናገር የሚችሉ ግለሰቦች ላይ በትኩረት እንደሚሠሩ ገለጹ።

ፕሬዝዳንቱ በኋይት ሀውስ በሰጡት መግለጫ፤ አሁን ያለውና አሜሪካ ውስጥ ዘመድ ወይም ጓደኛ ላላቸው ስደተኞች ቅድሚያ የሚሰጠውን ሕግ ወደጎን በማለት አዲሱ አሠራር መተግበር አለበት ብለዋል።

ትራምፕ ዲቪን ማስቀረት ይችላሉ?

ትራምፕ ከ'ነጩ ቤተ መንግሥት' ሊባረሩ ይችላሉ?

አክለውም የድንበር ጥበቃ እንደሚጠናከርና ጥገኝነት ጠያቂዎች ላይ ጥብቅ ምርመራ እንደሚደረግ ተናገረዋል።

ከፍተኛ ዴሞክራት ኃላፊዎች በበኩላቸው ውሳኔው ገና ተግባራዊ ሳይደረግ "ያበቃለት ነገር ነው" በማለት አጣጥለውታል።

ትልቅ ህልም ሰንቀው ወደ አሜሪካ የሄዱ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞችና በልጅነታቸው ወደአሜሪካ አቅንተው እስካሁን ዜግነት ያላገኙ ሰዎችን የሚያገልና ተስፋ የሚያስቆርጥ ነው በማለት ተቃውሟቸውን ገልጸዋል።

ፕሬዝዳንቱ አዲሱ ሕግ አሜሪካን ዓለም ሁሉ የሚመኛት ሃገር ያደርጋታል ቢሉም፤ ሕጉ ተግባራዊ እስኪደረግ ብዙ ፈተናዎች እንደሚኖርበት ይጠበቃል።

''ወደ ሃገራችን መግባት የሚፈልጉትን ሁሉ እጃችንን ዘርግተን እንቀበላቸዋለን። ነገር ግን የጥገኝነት ጥያቄያቸው ችሎታና እውቀት ላይ የተመሰረት መሆን አለበት'' ብለዋል ፕሬዝዳንቱ።

"ትልቅ ለውጥ ለማምጣት እየሠራን ሲሆን፤ ችሎታ ያላቸው ስደተኞችን ቁጥር ከ12 በመቶ ወደ 57 በመቶ ከፍ ለማድረግ አስበናል።''

ከዚህ በተጨማሪ ስደተኞች እንግሊዝኛ እንዲማሩ የሚገደዱ ሲሆን የሥነ ምግባር ትምህርትም ይሰጣቸዋል ተብሏል።

ሚሼል ኦባማ በአሜሪካ እጅግ ተወዳጇ ሴት ተባሉ

ዜግነት ለማግኘት ሲባል አሜሪካ ሄዶ መውለድ ሊቀር ይሆን?

የታችኛውን ምክር ቤት ዴሞክራቶች በአብላጫ ድምጽ በሚመሩበት በዚህ ወቅት የዶናልድ ትራምፕ አዲሱ ሕግ በኮንግረሱ ይሁንታ ለማግኘት ሊከብደው ይችላል።

ፕሬዝዳንቱ ከዚህ በፊት የዲቪ ፕሮግራምን ለማስቀረት የቀረበውን ዕቅድ እንደሚደግፉ ገልጸው ነበር። ነገር ግን ፕሮግራሙን የማስቀረት ስልጣን ስለሌላቸው የአሜሪካ ኮንግረስ አዲስ የስደተኞች ሕግ እስኪያወጣ መጠበቅ ይኖርባቸዋል።

አዲሱ ሕግ፤ በሃገሪቱ ሴኔት ውስጥ በወግ አጥባቂዎች ድጋፍ ያገኘውና የስደተኞችን ቁጥር በግማሽ ይቀንሳል የተባለውን እቅድ ለማሳካት ትራምፕን ይረዳቸዋል ተብሏል።