ጅማ ውስጥ የተከሰከሰው አውሮፕላን አብራሪ መሞቱ ተነገረ

የወደቀው አውሮፕላን Image copyright Jimma Zone Comm.

የግል የበረራ አገልግሎት የሚሰጠው አቢሲኒያ ፍላይት ንብረት የሆነ የበረራ መለማመጃ አውሮፕላን ከጅማ ከተማ አቅራቢያ ወድቆ መከስከሱ ተገለጸ።

አደጋው ያጋጠመው በጅማ ዞን ቤየም ወረዳ ጉና ቤየም ቀበሌ ውስጥ ዛሬ ጠዋት ሦስት ሰዓት ተኩል ገደማ እንደሆነ የዞኑ ኮምዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ያህያ አሊ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የኢቲ 302 የመጨረሻዎቹ ስድስት ደቂቃዎች

አቶ ያህያ እንዳሉት አደጋው ባጋጠመበት ጊዜ በአካባቢው ከባድ ጭጋግ እንደነበረ አመልክተው አውሮፕላኑ ሜዳማ ቦታ ላይ እንደወደቀና በውስጡ ከነበረው አብራሪ ውጪ በሌላ ሰው ላይ ጉዳት አልደረሰም።

የአውሮፕላን አብራሪውን ሕይወት ለማትረፍ ጥረት ቢደረግም እንዳልተሳካ ተናግረዋል።

አብራሪው የውጪ ሃገር ዜጋ እንደሆነና ለበረራው ከጅማ ተነስቶ በመጓዝ ላይ እንደነበረ የአቢሲኒያ ፍላይት ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ ካፒቴን ሰለሞን ግዛው ለቢቢሲ የተናገሩ ሲሆን በአብራሪው ላይ ስለደረሰው ጉዳት ግን አሁን መናገር እንደማይችሉ ገልጸዋል።

በኦሮሚያ ሄሊኮፕተር ተከስክሶ 18 ሰዎች ሞቱ

በአቢሲኒያ ፍላይት አውሮፕላን ላይ የደረሰው የዚህን አደጋ ምክንያት ለማወቅ የምርመራ ባለሙያዎች ወደ ሰፍራው መላካቸውን የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን አስታውቋል።

እስካሁነ ድረስ የመላው ዓለም መነጋገሪያ የሆነውና ከሁለት ወር በፊት ቢሾፍቱ አቅራቢያ ተከስክሶ ከ150 በላይ ሰዎች ሕይወትን ከቀጠፈው ከኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን አደጋ በኋላ ይህ ሁለተኛው አደጋ ነው።

ሁለቱን የአውሮፕላን አደጋዎች የሚያመሳስላቸው ነገር አለ

በቅርቡ አንድ በሚድሮክ ባለቤትነት ስር የሚገኘው ትራንስ ኔሽን ኤር ዌይስ ንብረት የሆነ ሄሊኮፕተር ቦሌ አየር ማረፊያ አቅራቢያ መኖሪያ ቤት ላይ ወድቆ በሰው ላይ ጉዳት አለመድረሱ ይታወሳል።

ባለፈው ዓመት ደግሞ የኢትዮጵያ አየር ኃይል አውሮፕላን ሞጆ አቅራቢያ ወድቆ በመከስከሱ ከ15 በላይ ሰዎች ህይወት መጥፋቱ ይታወሳል።