የጄኔራል ደምሴ ቡልቶ ልጅ 'መራር' ትዝታ

ጄኔራል ደምሴ ቡልቶ Image copyright ደረጀ ደምሴ

ከግንቦት 1981'ዱ መፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ጠንሳሾች ኹነኛው የነበሩት ጄኔራል ደምሴ ቡልቶ ናቸው። ልጃቸው አቶ ደረጀ ደምሴ ቡልቶ አሁን በአሜሪካን አገር የሕግ አዋቂና ጠበቃ፣ በማሳቹሴት የወንጀል ጉዳይ ጠበቆች ማኅበር ፕሬዝዳንትም ናቸው።‹‹አባቴ ለእናት አገሩ ኢትዮጵያ የነበረው ፍቅር ወደር አልነበረውም›› የሚሉት አቶ ደረጄ የልጅነት ውብ ትዝታቸውን፣ ልክ የዛሬ 30 ዓመት የሆነውን በግርድፉ ለቢቢሲ እንዲህ አጋርተዋል።

በኩርኩም እንወራረድ!

ልጅ እያለሁ…

ከአባቴ ጋር ሰፈር ውስጥ አዘውትረን ‹‹ዎክ›› እናደርግ ነበር። በተለይ ምሽት ላይ…ቦሌ መንገድ ላይ…

ትዝ ይለኛል አባቴ ቀጥ ብሎ፣ ደግሞም አንገቱን ቀና አድርጎ ነበር የሚራመደው። እኔ ደግሞ ብርቱካኔን እያሻሸሁ፣ ከሥር ከሥሩ እየተራመድኩ በጥያቄ አጣድፈዋለሁ…

"በጦርነት ላይ እንዴት ነው መድፍ የሚመታው?"

"አስተኳሹ አለ፤ እሱ የርቀቱን መጠን ለክቶ በሚሰጠው ምልክት ነው የሚተኮሰው። አንዳንድ ጊዜም ግምት መጠቀም የሚገደድበት ሁኔታ አለ"

"ርቀት ሳይለካ እንዴት ማወቅ ይቻላል?

"ዘዴ አለው…"

ጓድ መንግሥቱ እንባ የተናነቃቸው 'ለት

''ኢትዮጵያን ወደተሻለ ስፍራ ሊወስዳት የሚችል ሌላ መሪ የለም'' የሶማሌ ክልል ፕሬዝዳንት

"እንዴት በግምት ይሆናል…አባዬ? ለምሳሌ አንተ ከዚህ እስከዚያ ፎቅ ድረስ ያለውን ርቀት መገመት ትችላለህ?"

"በሚገባ"

"ስንት ሜትር ይሆናል?"

"መቶ ሀምሳ" ፈርጠም ብሎ መለሰልኝ።

"አይሆንም! መቶ ከሞላ ይገርመኛል" አልኩት።

"ትወራረዳለህ?" አለኝ ቆም ብሎ፣ በአባታዊ ፈገግታ እየተመለከተኝ።

"እንወራረድ!" አልኩ የእርምጃ ልኬቱን ለመጀመር ቆም ብዬ…

"በምን ትወራረዳለህ?" አለኝ ሳቁን እየታገለ…

"በኩርኩም"

አባቴ ከት ብሎ ሳቀና፣ "እንዴ! በፈለኩት ሰዓት ጠርቼ ልኮረኩምህ ስችል ለምን በኩርኩም እወራረዳለሁ?'' አለኝ።

"እሺ ታዲያ በምን ይሁን?"

"እንግዲያውስ ከተሸነፍክ የያዝካትን ብርቱካን እበላለሁ፤ ካሸነፍክ ግን ትኮረኩመኛለህ" አለኝ እየሳቀ።

ተስማማሁ።

እያንዳንዱ እርምጃ ወደ አንድ ሜትር እንዲቀርብ ረዘም እያደረክ ቁጠር ብሎ ከቆምንበት ቦታ እርምጃውን እየሳቀ አብሮኝ መቁጠር ጀመረ።

ቤታችን ስንደርስ ለብዙ ሰዓት ያሟሟኋትን ብርቱኳኔን ልጣጯን ልጦ፣ አንዳንዴም በማብሸቅ መልክ ፈገግ ብሎ ቁልቁል እየተመለከተኝ፣ ሳቁ አፍኖት እየበላት ነበር።

Image copyright Getty Images
አጭር የምስል መግለጫ በወቅቱ በልጆች ሳይቀር ይዘወተር የነበረው የሰላምታ አሰጣጥ።

‹‹ማታ ማታ ጄኔራል ፋንታ እኛ ቤት ይመጡ ነበር››

ድሮ ቦሌ ድልድይ አካባቢ ‹‹ካራማራ›› የሚባል ሆቴል ነበር። የኛ ቤት በዚያ ገባ ብሎ ነው፤ ሶማሌ ኤምባሲ ፊት ለፊት።

አባቴ በየአውደ ግንባሩ ውሎ ቤት ሲመጣ እጅግ ደስ ይለናል። እንቦርቃለን። ትምህርት ቤት በሄድንበት ቤት ገብቶ ወጥቶ ከሆነ በሚል ቁምሳጥን ከፍተን ከልብሶቹ ጠረኑን ፍለጋ እናሸታለን።

ከዚያ በፊት ግን በሱ የሥራ ባህሪ ምክንያት ብዙ ቦታ ኖረናል። ለምሳሌ ሐረር። እንዲያውም አባቴ ከጄኔራል መርዕድ ጋ በደንብ የተቀራረቡት ያኔ ይመስለኛል። ለነገሩ እነሱ ድሮ ካዴት እያሉም ይተዋወቃሉ።

የዛሬ 30 ዓመት... የኮ/ል መንግሥቱ አውሮፕላን ለምን አልጋየም?

በኤርትራ የማህበራዊ ድረ ገጾች አገልግሎት ተቋረጠ

ጄ/ል መርዕድ ንጉሤ ለተወሰነ ጊዜ ከሠራዊቱ ወጥተው የሐረርጌ ክፍለ አገር አስተዳዳሪ ሆነው ነበር። ያን ጊዜ ክረምት ነበር። እኔም ካባቴ ጋ ሐረር ነበርኩ። እና ጋሽ መርዕድ የተመደበላቸው ቤት እየታደሰ ስለነበር እኛ ቤት ይኖር ነበር። ማታ ማታ አብረው ሲጫወቱ እኔም እዛ የሚጠጣ ምናምን እያቀረብኩኝ ቁጭ እላለሁ።

ጋሽ መርዕድ ልጆች ይወዳል። በጣም ያቀርበን ነበር። የሚነጋገሩትን ነገሮች በሙሉ እሰማ ነበር። ብዙውን ጊዜ የአገሪቷን ችግር ነበር የሚያወሩት። የጦርነት ሁኔታ እንደረበሻቸው፣ በሰሜኑ ጦርነት የሚያልቀው ሠራዊት ቁጥር ያንገብግባቸው እንደነበር አስታውሳለሁ። እርግጥ ስለመፈቅለ መንግሥት ወይም እንደዚያ የሚመስል ነገር እኔ ፊት ሲያወሩ ትዝ አይለኝም።

የጄ/ል ፋንታ በላይ እና የኔ አባት ግንኙነት እየጠነከረ የመጣው ደግሞ ‹‹የባህረ ነጋሽ›› እና ‹‹የቀይባህር ዘመቻ›› ጊዜ ይመስለኛል። አባቴ ከሐረር ምሥራቅ እዝ አዛዥነት ለተወሰነ ጊዜ ኤርትራ ሄዶ እነዚህን ሁለት ዘመቻዎች በአስተባባሪነት መርቶ ነበር። በዚያ ጊዜ ጄኔራል ፋንታ የአየር ኃይል አዛዥ ነበሩ።

እንዲያውም በባሕር ኃይልና በአየር ኃይል የተቀነባበረ ጥቃት ለአንድ ጦርነት ሲደረግ ለመጀመርያ ጊዜ ይመስለኛል። በዚያ ጦርነት ገፍተው ሄደው ናቅፋን ለመያዝም ጥረት አድርገው ነበር። ከዚያ በፊት ባሬንቱን ጭምር አስለቅቀው ነበር። ያ ጦርነት አባቴንና ጄ/ል ፋንታን አቀራርቧቸዋል ይመስለኛል።

ለምን መሰለህ እንደዚያ የምልህ…ከዚያ በኋላ ማታ ማታ ጄኔራል ፋንታ እኛ ቤት ይመጡ ጀመር። የኔ አባት ከመጣ ጄ/ል ፋንታም ይመጡና ረዥም ሰዓት ያወራሉ። እኛ ቤት ማንኛውም ሚኒስትርም ሆነ ጄኔራል ከመጣ እኛ ልጆች ውጡና ውጭ ተጫወቱ አንባልም፤ ቁጭ ብለን ማዳመጥ ይፈቀድልን ነበር፤ ምንም ችግር አልነበረውም።

ጄ/ል ፋንታ ከመጡ ግን እንደሱ ብሎ ነገር የለም። ለብቻቸው ነው የሚያወሩት፤ ሳሎን ማንም አይገባም። ደግሞ ሳሎን አውርተው ሲበቃቸው አልፎ አልፎም በአንድ መኪና ወጣ ብለው ይመለሳሉ። አስታውሳለሁ ጄ/ል ፋንታ ቶዮታ ነበረቻቸው።

ወንዶች የማያወሯቸው አምስት አሳሳቢ ነገሮች

አሁን መለስ ብዬ ሳብሰለስል ያ ጊዜ 'ስለ መፈንቀለ መንግሥት መወጠን የጀመሩበት ጊዜ ይሆን?' እላለሁ።

ጋሽ መርዕድና ጄኔራል አበራ

እኛ ድሮ ገና ከልጅነታችን ቤታችን ሁልጊዜ ሲመጡ የምናያቸው ጄ/ል መርዕድን ነበር። ከጄ/ል መርዕድ ጋ እኮ በጣም ቅርብ ነበርን። እንዳውም አባቴ የጋሽ መርዕድ የመጀመርያ ወንድ ልጅ የክርስትና አባት ሲሆን እናቴ ደግሞ የትልቋ ሴት ልጃቸው የክርስትና እናት ናት። ያን ያህል ቅርብ ነበርን። ጄ/ል መርዕድ ቤታቸው ጎፋ ቄራ ነበር፡፡ ቢሆንም እኛ ቤት ብዙ ጊዜ ይመጡ ነበር፡፡

ከጄ/ል አበራ ጋ ደግሞ አባቴ የምሥራቅ ዕዝ አዛዥ እያለ እሳቸው ምክትል ነበሩ። ከአየር ወለድ ጀምሮ ከአባቴ ጋር ይተዋወቃሉ። ጄ/ል አበራ ብዙ ልምድ ያላቸው አዋጊ አዛዥ ነበሩ። እና ይቀራረቡ እንደነበር አስታውሳለሁ።

እንግዲህ መርዕድ፣ ፋንታ፣ አበራና አባቴ በዚህ ሁኔታ ተቀራርበው መፈንቅለ መንግሥቱን የወጠኑት ይመስለኛል፡፡

Image copyright Getty Images
አጭር የምስል መግለጫ ከቀኝ ወደ ግራ ኤዲ አሚን ዳዳ፣ ተፈሪ በንቲ፣ መንግሥቱ ኃይለማርያም። ጥር 1፣ 1968፥ አዲስ አበባ።

"የአገሪቱ ኢኮኖሚ ኮዳ መግዛት አይችልም ነበር"

እንግዲህ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ስሰማቸው አገሪቱ ውድቀት ላይ እንደነበረች ነበር የሚያወጉት ብዬኻለሁ። በኤርትራ የሚደረገው ጦርነት በንግግር መፈታት እንዳለበት፥ በትግራይ የነበረው የፖለቲካ ችግር ለመሀል አገርም እንደሚተርፍ ወዘተ...፤ በነዚህ ነጥቦች ላይ ተቀራራቢ አመለካከት የነበራቸው ይመስለኛል።

ለነገሩ የአገሪቱ ኢኮኖሚ ጦርነቱ ከብዶት ነበር። ከቆርቆሮ ኮዳ አቅም እንኳ ፕላስቲክ ኮዳ መግዛት የሚከብደው ነበር። የተራበ ጦር ነበር። ሠራዊቱ ኮቾሮ እየበላ ያን ሁሉ ዓመት መዋጋቱ ራሱ የሚገርም ነው። የቆረቆዘ ኢኮኖሚ ይዞ ግማሽ ሚሊዮን የሚጠጋ ጦር ሠራዊት ማስተዳደር እንደማይቻል አባቴና ጓደኞቹ የተረዱ ይመስለኛል።

በተለይ ሠራዊቱ የሚከፍለው የተጋነነ የሕይወት ዋጋ በየጦር አውድማው ሲመለከቱ እየተበሳጩ እንደመጡ መገመት ይቻላል። ይህን ይህን እያዩ መተኛት ሲያቅታቸው ይመስለኛል ወደ መፈንቅለ መንግሥት ሐሳብ የደረሱት።

ነገር ግን ቀደም ሲልም እንደነገርኩህ እዚህ የደረሱት በአንድ ቀን አይደለም። አሁን ወደ ኋላ ተመልሼ ሳስበው... እኔ ነፍስ አወቅኩ ከምልበት ጊዜ ጀምሮ ነው የምልህ...የሰሜኑ ጦርነት መቆም እንዳለበት ነበር የሚያወሩት።

መቼስ መፈንቅለ መንግሥቱ የዚህ ሁሉ ድምር የወለደው ነው የሚሆነው....፡፡

"አባቴን የማገኘው ጦር ሜዳ እየሄድኩ ነበር"

ከልጅነቴ ጀምሮ ከጦሩ ጋር ነው ያደጉት። ምክንያቱ ደግሞ አባቴ ነው። ሕይወቱ በየአውደ ውጊያው ነበር።፡ እንዲያውም በሦስት የኢትዮጵያ ግንባር የኢትዮጵያን ጦር ለመምራት ዕድል ያገኘ ብቸኛው ጄኔራል አባቴ ይመስለኛል። ምሥራቅ፣ ደቡብና ሰሜን።

እናት አልባዎቹ መንደሮች

መጀመርያ ሐረር አካዳሚ እንኖር ነበር ብዬኻለሁ። አባቴ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የጦር ስልጠናና ትምህርት ዳይሬክተር ነበር። በዚህ ረገድ የመጀመርያው ኢትዮጵያዊ ዳይሬክተር መሆኑ ነው። ከዚያ በፊት እንግሊዞችና ሕንዶች ነበሩ የሚያስተዳድሩት።

እዚያ የመኮንኖች መኖርያ ካምፕ ነበረ፤ ሐረር አካዳሚ ፊት ለፊት። መንገድ ተሻግረን ካዴቶች ሰልፍ ሲሰለፉ ነው የምናየው። እግር ኳስ እንጫወታለን። "ተስፋዬ ቼንቶ" የሚባል በጣም የሚታወቅ ተጫዋች ነበር። ኳስ ያጫውተን ነበር።

አባቴ ደቡብ እዝ እያለ ደግሞ ጦር ሰፈር እንውላለን። ያየነውን በጨዋታ መልክ እንናገራለን። ከዚያ በኋላ የመድፈኛ የታንክ ትርኢቶች፣ የወታደር ምረቃ አንድም አያመልጠንም። ወንድሜ ለምሳሌ ባሌ ዶሎ ፊልቱ ጦር ሜዳ ሄዷል፤ ከአባቴ ጋር። እጅግ ከባድ ጦርነት የተካሄደበት ቦታ'ኮ ነው።

እኔ ደግሞ ጭንአቅሰን፣ ከረን ከዚያ እስከ አፋቤት፣ ግዝግዛ፥ መሳአሊት ሄደናል። በጣም መጥፎ ቦታዎች ነበሩ። ሬሳ እያየህ፣ ጦርነት እየተካሄደ ነው ታዲያ...። መድፍ ወደፊት እየተተኮሰ ሁሉ አባቴ ይዞኝ ይሄድ ነበር። ጋዜጠኛ ሙሉጌታ ሉሌ፥ ቁምላቸው ደጀኔ እዛ እንዳገኘናቸው ትዝ ይለኛል። ኮ/ል አምሳሉ ገብረዝጊም ነበረ። እንዳውም የጦር ሜዳ መነጽር ሁሉ ከሱ ተቀብዬ ተራራ ላይ የሚካሄደውን ጦርነት ሁሉ አይቻለሁ።

እና ከልጅነታችን ጀምሮ አባቴ ስለ ኢትዮጵያ ጦር ሠራዊት እንድናውቅ፤ የአገር ፍቅር እንዲያድርብን ይፈልግ ነበር።

ለምሳሌ አንደኛው ብሔራዊ ውትድርና ጥሪ ሲደረግ የማንም ጄኔራል ልጅ ብሔራዊ ውትድርና የሄደ አልነበረም። የኔ አባት ግን "ይሄ ለኢትዮጵያ ሕዝብ በሙሉ የመጣ ሕግ ነው፤ የኔ ልጅ ከተጠራ መሄድ ነው ያለበት" ብሎ ወሰነ። በዚህም ምክንያት ወንድሜ ብሔራዊ ውትድርና ዘምተ።

እረፍት በማይሰጠው ጦርነት የተነሳ አባቴ እቺን ታህል ፋታ አልነበረውም። እኔ ለምሳሌ በአንድ ወቅት አሥመራ ልጠይቀው ሄጄ ላገኘው አልቻልኩም። እኩለ ሌሊት ነው ወደ ቤት የሚመጣው። ማልዶ ነው ቢሮ የሚገባው። አንዳንድ ጊዜም ቢሮ ያድራል፤ እዛው ታጣፊ ፍራሽ አለችው።

በተደጋጋሚ ብሞክርም ላገኘው ስላልቻልኩኝ መልእክት ላኩበት፤

ኢትዮጵያ ሀይቆቿን መጠበቅ ለምን ተሳናት?

«አባዬ! እዚህ አሥመራ ድረስ መጥቼ ሳንገናኝ ልመለስ ነው ወይ?» ስለው ‹‹እንግዲህ በዚህ ወቅት ሥራ ትቼ ወዳንተ አልመጣም፤ ወይም ለምን የሚሊተሪ ልብስ ለብሰህ ከኔ ጋ ጦር ሜዳ አትመጣም፤ ያለው ዕድል እሱ ብቻ ነው…›› አለኝ።

እንዳለው አደረኩ። ያኔ ምጽዋ እንዳይያዝ የሚደረጉ ጦርነቶች ነበሩ። ጄ/ል ዋሲሁን ንጋቱ ታንከኛ ያሰለጥኑ ነበር፤ እዛ ሄድን። ከረን ጄ/ል ታደሰ ተሰማ የሚመሩት መምሪያ ነበር፤ ተራራ ላይ ያለ። እዛም ሄደን ነበር።

ብቻ ምን ለማለት ነው...ጦር ሜዳ ሄጄ የአባቴን ናፍቆት ተወጥቼ ወደ አዲስ አበባ ተመለስኩ እልኻለው።

Image copyright ደረጀ ደምሴ
አጭር የምስል መግለጫ የሐረር አካዳሚ ምረቃ በዓል፤ ጄኔራል ደምሴ ቡልቶ (ቀኝ) የጦር ትምህርትና ስልጠና የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ዳይሬክተር

"መፈንቅለ መንግሥቱን ያካሄዱት ለሥልጣን ነው የሚሉ ሰዎች ይገርሙኛል"

አባቴን በደንብ ስለማውቀው ነው ይህንን የምናገረው። በጦርነቱ የሚያልቀው ኢትዮጵያዊ ቁጥር ሁልጊዜም ይረብሸው ነበር። የሰሜኑ ችግር በፍጹም በጦር እንደማይፈታ ጠንቅቆ የተረዳ ይመስለኛል።

አንዳንዶች ያንን ዘመን በአሁን መነጽር እያዩት የተሳሳተ ድምዳሜ ላይ ይደርሳሉ። እውነት ለመናገር አባቴን ጨምሮ ብዙዎቹ የገንዘብ፣ የጥቅም ሰዎች አልነበሩም። "ለሥልጣን ነው" የሚሉ ሰዎች ደግሞ ይበልጥ ያስገርሙኛል።

ብዙዎቹ የመፈንቅለ መንግሥቱ አቀናባሪዎች እኮ በአገሪቱ ውስጥ እጅግ ከፍተኛ ሥልጣን የነበራቸው ናቸው። መንግሥት ቢገለበጥም ከያዙት ሥልጣን በላይ ሥልጣን አያገኙም። ከየት መጥቶ? መቼስ በአንድ አገር መሪ የሚሆነው አንድ ሰው ብቻ ነው። የቀሩት ሚኒስትርና የጦር አዛዦች ነው ሊሆኑ የሚችሉት። ናቸውም። አንዳንዴ ጉዳዩን ፍትሐዊ ሆነን በሚዛን መመልከት ጥሩ ነው።

አንድ በአንድ እንየው ካልከኝም እሰየው።

ጄ/ር መርዕድ የኢትዮጵያ ሠራዊት ጠቅላይ ኢታማዦር ናቸው። ፋንታ በላይ ሚኒስትር ናቸው። አባቴ ኢትዮጵያ ውስጥ ግዙፉን የሰሜን ጦር የሚመራ ጄኔራል ነው። ጄ/ል ኃይሉ የምድር ጦር አዛዥ ናቸው፤ አድሚራል ተስፋዬ የባሕር ኃይል አዛዥ ናቸው፤ ጄ/ል አመኃ አየር ኃይል በእጃቸው ነው። ሌሎቹም እንደዚያው።

ሰከን ብለን፣ ወቅቱን አገናዝበን፣ ነገሩን ካሰብነው እያንዳንዳቸው ይሄን አገኛለሁ ብለው አይደለም እንዲህ ዓይነት እሳት ውስጥ የገቡት። በፍጹም የገንዘብ፣ የሥልጣን ሰዎች አልነበሩም ነው የምልህ። መንግሥት ያኔ በነጻ አምስት መቶ ካሬ ሲሰጥ እኮ ያልወሰዱ ናቸው። ከመፈንቅለ መንግሥቱ በኋላ ቤት አልባ የሆኑና የተበተኑ ብዙ ናቸው እኮ።

በኔ እምነት ያን ሙከራ ያደረጉት የኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ እንቅልፍ ነስቷቸው ነው። በፍጹም ስለገንዘብ የሚያስቡ ሰዎች አልነበሩም። ያደጉትም እንደዚያ አልነበረም። ብዙ ጊዜያቸውን አገሪቷ እንዴት አንድነቷ እንደሚጠበቅ ነበር የሚጨነቁት። እንዲያውም ብዙዎቹ ጄኔራሎች ልጆቻቸውን ካስተማሩ ያ በቂያቸው ነበር።

ቆይ እንደውም፣ የኮ/ል ግርማ ተሰማን ታሪክ ታውቀዋለህ? የሚገርሙ ሰው ናቸው…

በመፈንቅለ መንግሥቱ ጊዜ በናቅፋ እስርቤት ውስጥ ነበሩ፤ ተማርከው። የምርኮኞች ተጠሪ ነበሩ። ኩዴታው በማስመልከት የተኩስ ማቆም ስምምነት ተደርጎ ነበር። እሳቸው ጦሩ ወክሏቸው አሜሪካ ድረስ እየሄዱ ንግግር ያደርጉ ነበር። ታዲያ አሜሪካ መጥተው ጥገኝነት አልጠየቁም። እየቻሉ።

"የወከለኝ ጦር እዛ እስር ቤት እያለ እኔ እነሱን ጥዬ አልቀርም" ብለው አሜሪካን አገር ሥራቸውን ሠርተው ተመልሰው ናቅፋ እስር ቤት ነው የገቡት። ማን ነው ይሄን የሚያደርግ? [ይሄ የወቅቱን ሰዎች ሥነልቦና በተወሰነ መልኩ ይወክል እንደሁ አላውቅም።]

ኮ/ል ግርማ ኤርትራ የራሷን መንግሥት ስትመሠርት ተፈተው፣ አዲስ አበባ ሄደው፤ የድሮ ጡረታቸውን እየበሉ ኖረው በቅርብ ነው ያረፉት። ያን ጊዜ ብዙዎቹ የጥቅም ሰዎች አልነበሩም የምልህ ለዚህ ነው።

እነ ደረጀ ደምሴ "ያቺን ሰዓት"

ግንቦት 8 ድንገት ቤታችን ተንኳኳ፡፡

ደጅ የወታደሮችን ሁኔታ ሲያዩ ነው መሰለኝ ዘበኞች በሩን መክፈት ፈሩ። ሄጄ በሩን ከፈትኩ። ከአሥመራ የመጡ ወታደሮች ናቸው። ከወታደሮቹ መሐል የአባቴን አጃቢ ዐሥር አለቃ ጌታቸውን ስላየሁት ተረጋጋሁ። ከነሙሉ ትጥቁ ቆሟል፡፡

«ተልከን ነው የመጣነው» አለኝ፤ ከአሥመራ

ሁለቱ የአባቴ አጃቢዎች፣ ሁለቱ ደግሞ ያን ጊዜ የአባቴ ምክትል የነበሩት የጄ/ል ሁሴን አጃቢዎች ናቸው፡፡

«ምንድነው ምን ተፈጠረ?» ብለን ስንጠይቃቸው አውሮፕላኑ ውስጥ የነበረውን ሁኔታ አስረዱን። እነሱ በቀጥታ ከአሥመራ ስለመጡ መንግሥቱ መገደሉን ነው የሚያውቁት።

በኔ አባት አመለካከት ደግሞ መፈንቅለ መንግሥቱ በታቀለደለት ሁኔታ እየሄደ ነው። ከአሥመራም ይህንኑ የሚያሳካ ጦር ተልኳል። መንጌም አብቅቶለታል። በዚህ ሁሉ ግርግር የተለያዩ ሰዎች ወደኛ ቤት ሊሄዱ ይችላሉ ብሎ ገምቷል። ለዚህ ነው ወታደሮችን የላከው ይመስለኛል።

በዚያ ላይ ሰፈራችን ብዙ ሹማምንት ያሉበት ነው። ከኛ ቤት አለፍ ብሎ የፍቅረሥላሴ ወግደረስ ቤት አለ። በጀርባም በኩል ሌሎች የደርግ አባሎች አሉ። እና ያው አባቴ አጃቢዎቹን የላከልን የተወሰነ ከለላ ከሰጧቸው ብሎ ይመስለኛል።

ነገሩ አላማረንም፡፡ ሁኔታዎች እስኪጠሩ ድረስ ከቤት ወጥተን ማረፍ እንዳለብን ተነጋግረን፤ እናቴም፣ እኔም፣ ወንድሜም ሁለት እህቶቼም ሌላ ቦታ ሄደን አደርን። ዘመድ ቤት ሊደረስበት ስለሚችል ዩሱፍ ዘከሪያ የሚባል የቤተሰብ ወዳጅ ጋ ሄደን ተደበቅን።

Image copyright Getty Images
አጭር የምስል መግለጫ የኤርትራ ነጻ አውጪ ተዋጊዎች በናቅፋ አካባቢ ጦርነት ላይ ሳሉ፤ ሐምሌ 3/1970

ማክሰኞ ግንቦት 8 ምሽት፣ 1981

አዳር አትበለው። አስጨናቂ ምሽት ነበረ። ሬዲዮ ስንጎረጉር ስንጎረጉር…። የአሥመራ ሬዲዮ ምን እንደሚል ለመስማት ነበር ሙከራችን።

ጆሯችን ሬዲዮ አይናችን ቴሌቪዥን ላይ ተክለን ቆየን። እንደሚባለው የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ እየተካሄደ ከሆነ አባታችን ከየትኛው ወገን እንደሚሆን እርግጠኞች ስለሆንን ነው ጭንቀታችን የበዛው።

ምሽት አራት ሰዓት ገደማ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በጥቂት ሰዓቶች ውስጥ የማስተላልፈው ሰበር ዜና አለኝ አለ። የሁላችንም ልብ ቆመ።

ቆይቶ ዜና አንባቢው መጣና በጥቂት ጄኔራሎች መፈንቅለ መንግሥት ተሞክሮ መክሸፉን ተናገረ። የጄ/ል መርዕድና የጄ/ል አመሓን ከዚህ ዓለም በሞት መለየት ጠቀሰ። ክው ብዬ ቀረሁ።

እናቴና እህቴ ተንሰቅስቀው ማልቀስ ጀመሩ።

የአባቴ ሁኔታ ምን ሊሆን እንደሚችል በማሰብ ጭንቅላቴ እረፍት አጣ።

የአሥመራ ሬዲዮ በበኩሉ የመንግሥቱ ኃይለማርያም የ15 ዓመታት አምባገነን አገዛዝ ማክተሙን ያወራል።

አባቴ መቼስ እዚህ ሙከራው መክሸፉን ሲያውቅ አውሮፕላን እስነስቶ ከአገር ይወጣል። ይሄ ለሱ በጣም ቀላሉ ነገር ነው። ራሴን ማጽናናት ጀመርኩ። እናቴንም እንዲሁ ማጽናናት ጀመርኩ…

ረቡዕ፤ ግንቦት 9፣ 1981

በነገታው እሮብ ሁላችንም አንድ ቦታ ማደር እንደሌለብን ተነጋገርን፡፡ መለያየትማ የለብንም አሉ እህቶቼ፡፡ እኛ ደሞ በፍጹም አልን…

እጅህን ካልሰጠህ እንገድላቸዋለን ቢሉትስ፡፡ በዚያ ላይ ትናንት ወደዚህ ቤት ስንመጣ ያየን ሰው ሊኖር ይችላል፡፡ ሌላ የማይጠረጠር ቤት ተበታትነን መቆየት ነው የሚሻለው፡፡ ተስማማን፡፡

እኔና ወንድሜ ሽመልስ የሚባል ጓደኛዬ ጋ፤ እናትና እህቶቼ ባላምባራስ ጥበቡ የሚባሉ ቤተሰብ ጋ ተበተንን፡፡ ባላምባራስ ጥበቡ ባለውለታችን ናቸው፡፡ አሁንም በሕይወት አሉ፡፡

ማታ ከጓደኛዬ ሽመልስ ጋ እናወራለን፤ ጭንቀቱን ለማቅለል፡፡ አባቴ ሙከራው እዚህ አዲሳባ ከከሸፈ ለምን ቶሎ ከአገር አልወጣም እያልኩ እብሰለሰላለሁ፡፡

ረቡዕ ማታ መንግሥቱ ኃይለማርያም ጉብኝታቸውን አቋርጠው ተመለሱ፡፡

የአሥመራ ሬዲዮን ስጎረጉር ግን አሁንም የመንግሥቱ አምባገነን አገዛዝ ማክተሙን፤ የተለያዩ የጦር ክፍሎች ደግሞ ድጋፍ ስለመስጠታቸው ነው የሚያትተው፡፡ ግራ ገባኝ፡፡ አባቴ በዚህ ሁሉ መሀል የት ነው ያለው?

ሐሙስ ግንቦት 10፣ 1981

ሐሙስ ማታውኑ የአሥመራው ሙከራ መክሸፉን ሰማን። ስለ አባቴ ግን ምንም የሰማሁት ነገር አልነበረም።

ጠዋት አካባቢ ድንገት እንዲህ ነው የማልለው ከፍተኛ የስሜት መረበሽ ደረሰብኝ። ምንም የሰማሁት ነገር የለም'ኮ፣ ግን በበዛ ሐዘን ራሴን መቆጣጠር ተሳነኝ።

የመጣው ይምጣ ብዬ ከጓደኛዬ ቤት ወጥቼ ወደ ቤታችን መሄድ ጀመርኩ።

ቤታችን አካባቢ ጄ/ል ግዛው በላይነህን አየኋቸው። አባቴን በጣም ይወዱት የነበሩ ሰው ናቸው። ሌሎች ሰዎችም ቤታችን አካባቢ ይንቀሳቀሳሉ። ደስ አይልም። በቃ ሁኔታውን ገባኝ።

Image copyright ደረጀ ደምሴ
አጭር የምስል መግለጫ (ከግራ) ሜ/ጄነራል አበበ ወ/ማሪያም፣ ሌ/ጄነራል ጃጋማ ኬሎ እና አቶ ደረጀ ደምሴ

ድኅረ-ደምሴ ቡልቶ

በመጀመርያ ደረጃ የኔ አባት የኢትዮጵያን ጦር ለ37 ዓመታት ነው ያገለገለው። በደርግ 15 ዓመት፣ ከዚያ በፊት 22 ዓመት። ያልተዋጋበት የለም። ደቡብ አዛዥ ሆኖ ሲሄድ የሶማሌ ጦር አዋሳን ለመያዝ 60 ኪሌ ሜትር ላይ ነበር። እዚያ ተዋድቋል። ተወው ብቻ…

ግን ከመንግሥት ለቤተሰብ አንድ ደብዳቤ እንኳ አልደረሰንም። ተወው ደብዳቤውን…አስክሬኑ አልተሰጠንም። እንዲያውም ያኔ በግልጽ ሐዘን መቀመጥ መቻላችንን እንደ ዕድል ተደርጎ ነበር የሚወራው።

መንግሥቱ አገር ጥሎ ወደ ዚምባቡዌ ከሸሸ በኋላ ነው የአባቴን ሬሳ ያገኘነው። እናቴ አዲሱን መንግሥት አስፈቅዳ፣ የኤርትራ መንግሥትም ፈቅዶ፣ የተቀበረበትን በአገሬው ሰው ተመርታ አውጥታ ነው የቀበረችው።

እዛ ያኔ አምጸው የነበሩትና በኮ/ል መንግሥቱ ኃይለማርያም ቀጥተኛ ትእዛዝ የተገደሉትን በሙሉ በአንድ ጉድጓድ አሥመራ መንደፈራን አልፎ ያለ አንድ ቦታ ላይ ነበር ቆፍረው የቀበሯቸው።

እናቴ የሁሉንም ቤተሰቦች አስተባብራ አጽማቸውን አስወጥታ በክብር ዮሴፍ ቤተክርስቲያን እንዲያርፍ አስደርጋለች።

"መንግሥቱ ኃይለማርያም ይቅርታ ሊጠይቅ ይገባል"

እሱኮ ኢትዮጵያ ለደረሰችበት ውድቀት ቀጥተኛ ተጠያቂ ሰው ነው። ሰውየው ቤተሰቡን አሽሾ አንድ ቦታ ተጠልሎ ዛሬም ድረስ ይኖራል። ከዚህ ሁሉ ወንጀሉ ጋ ዛሬም ድረስ ከሕሊናው ጋር ተስማምቶ ይኖራል። አስደናቂ ነው። አሁን ዕድሜው ገፍቷል። በትንሹ ሊያደርግ የሚችለው የኢትዮጵያ ሕዝብን ይቅርታ መጠየቅ ነው።

ከዚህ ሁሉ ዘመን በኋላም፣ "ይቅርታ፣ ያኔ የነበረኝ ዕውቀት አገሬን ለማስተዳደር በቂ አልነበረም። ያኔ ሥልጣኑን መቀበል አይገባኝም ነበር። ባለማወቅ ያደረኩት ስለሆነ ይቅርታ አድርጉልኝ" አላለም።

እውነት ለመናገር ታሪክን መለስ ብለህ ስታይ ኢትዮጵያን የመሰለች ትልቅ አገር በሱ ጭንቅላት መመራት አልነበረባትም። እንደ ተፈሪ በንቲ ያሉ የሰከኑ ሰዎች የሰከነ አመራር ለማምጣት ይሞክሩ ነበር። እነ አማን አምዶም ገና ከመነሻው ሰላም ለማምጣት ጥረዋል። በጎ ያሰቡ ሰዎችን በሙሉ ነው አንድ በአንድ የጨረሳቸው።

ያም ሆኖ ግን እሱም ሆነ የሱ የነበሩ ሌሎች ባለሥልጣናት ይቅርታ አልጠየቁም። በየቤተክርስቲያኑ እየሄዱ፣ የድሆችን እግር እያጠቡ ሕዝቡን ይቅርታ መጠየቅ ሲገባቸው ሁሉም ‹‹እኔ ከደሙ ንጹሕ ነኝ›› እያሉ፣ አልፎ ተርፎም መጽሐፍ እየጻፉ በየመድረኩ ያስመርቃሉ፤ ንግግር ያደርጋሉ። የሚገርም ሕሊና ነው ያላቸው። እቺን ታህል እንኳ ጸጸት አይሰማቸውም፤ እቺን ታህል…፡፡

"የአባቴ አሟሟት የማይገኝ ነው"

አዲስ አበባ የከሸፈው ማክሰኞ ግንቦት 8 ማታ ላይ ነው። እሱ የተገደለው ግንቦት 10 ሐሙስ ነው። የኔ አባት አውሮፕላን አስነስቶ መሄድ የሚከለክለው ምን ነገር ነበር? እስከመጨረሻው ድረስ በሕይወቱ ቆርጦ የገባበት ነገር ስለሆነ ነው እንጂ ያን ማድረግ ለሱ በጣም ቀላሉ ነገር ነው።

የሱ ምክትል የነበሩት ጄ/ል ሁሴን አሥመራ ከመያዟ በፊት '83 ላይ አውሮፕላን አስነስተው ነው ወደ ሳኡዲ የሄዱት። እሱም ያን ማድረግ አያቅተውም ነበር። ጄ/ል ንጉሤ መክረውት ነበር። "ነገሩ ከተበላሸ በኋላ ምን ትሠራለህ?" ብለውት ነበር። ይሄን ሁሉ ሰው ጥዬ የትም አልሄድም ነው ያላቸው።

ኮ/ል መንገሻ ነበሩ ያኔ ወደ ተለያዩ ቦታዎች ትእዛዝ እየተቀበሉ ሄሌኮፕተር የሚልኩት።

‹‹ጄ/ል ደምሴ ቢፈልጉ እዛው ቢሯቸው ፊትለፊት አንድ ሄሊኮፕተር ቆሞ እንዲጠብቃቸው ማድረግ ይችሉ ነበር። አልፈለጉትም እንጂ›› ብለውኛል።

ምንድነው ለኔ ትልቅ ትምህርት የሆነህ ካልከኝ የርሱ ዓይነት አሟሟት አይገኝም። ለምን በለኝ…ያመነበትን አድርጓል። ጦሩን አልከዳም…አገሩን አልከዳም…።

ከሱ በተቃራኒ የቆሙት እኮ ሞት አልቀረላቸውም።

የህወሓት ጦር ሲገባ ብዙዎቹን ተሰልፈው እጅ ሰጥተው፣ ለዚያውም ዘርህን ጥራ እየተባሉ፤ ስለ ብሔር ትምህርት ደግሞ ያስፈልግሃልና ተማር እየተባሉ፣ ስለ ዘር ልዩነት ተማር እየተባሉ፣ ትናንትና ሽፍታ ይሉት የነበረው ሰው በአርጩሜ ሂድ እዛ ተሰለፍ እያላቸው። ከዚያም አልፎ ግማሾቹ እዚያው እስር ቤት ሞተዋል።

የኔ አባት ያን ሳያይ ማረፉ ለሱም ትልቅ ግልግል ነው። እኛም ልጆቹ በጣም የምንኮራበት ሥራ ነው የሠራው። ለልጅ ልጅም የሚያኮራ ነው። የአባቴ ዓይነት አሟሟት አይገኝም። እውነተኛ የአገር አንድነት፣ የሕዝብ ፍቅር የነበረው ሰው ነው አባቴ። እንወደዋለን፡፡ እንኮራበታለን።