በባህር ዳር የእምቦጭ አረምን የሚያጠፉት ጢንዚዛዎች አልጠፉም

የእምቦጭ አረም

በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ግቢ ውስጥ 'ዊቭል' የተባለ የጥንዚዛ ዓይነት ማራቢያ ይገኛል። ማራቢያው ጢንዚዛዎቹ የሚፈልጉትን ሙቀት የሚሰጥ ማሞቂያ እና ለምግብነት እና ለመራቢያ የሚያስፈልጋቸውን እንቦጭ አረም ይዟል።

ማራቢያው በቀላሉ ከሚበሰብስ ጨርቅ ነው የተሰራው። ከቆይታ ብዛትም ጣሪያው በአንድ በኩል ተቀዶ ነበር። የጣሪያው መቀደድ በማህበራዊ ሚዲያው ላይ ስጋት የሚያጭሩ መረጃዎች እንዲወጡ ምክንያት ሆኗል።

በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ መምህር እና ተመራማሪ የሆኑት ረዳት ፕሮፌሰር ጌታቸው በነበሩ "በማህበራዊ ሚዲያ የተባለው ከእውነት የራቀ ነው፤ የክልሉን፤ የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲንና የአካባቢ ጥበቃን ገጽታ ለማበላሸት ብቻ ሳይሆን ከኋላም ድብቅ አጀንዳ ያለው ነው፤ እምቦጩ እንዳይጠፋ የሚፈልግ ሰው አለ ወይንም የራሱ የሆነ ትርፍ ለማግኘት ያለመ ሰው አለ" ሲሉም የተሰራጨው መረጃ አሉቧልታ እንደሆነ ያረጋግጣሉ። ፕሮፌሰሩ አክለውም "የዊቭሎቹን (ጢንዚዛዎቹ) ባህሪ ስለማውቅ፤ የእኔ ፍራቻ የነበረው ጦጣዎች ወደ ቦታው ገብተው ማራቢያውን እንዳያበላሹት ነው" ይላሉ።

በአማራ ክልል የአካባቢ ደንና ዱር እንስሳት ጥበቃና ልማት ባለሥልጣን ምክትል ዳይሬክተር የሆኑት አቶ በልስቲ ፈጠነም "ሲወጣ የነበረው መረጃ ሀሰተኛ ሲሆን የሚያሳየውም በቦታው ላይ ያለውን ሀቅ አይደለም" ሲሉ የፕሮፌሰሩን ሃሳብ ይጋራሉ።

በማህበራዊ ሚዲያ 600 የሚሆኑ ጢንዚዛዎች ከኡጋንዳ በዶላር ተገዝተው መምጣታቸው መገለፁን ያነሳንላቸው ዶ/ር ጌታቸው "ስህተቱ የሚጀመርው ከዚህ ነው" ብለዋል።

የጣና ሐይቅን ሌሎችም አረሞች ያሰጉታል

እምቦጭ የጣና ቂርቆስ መነኮሳትን ከገዳሙ እያስለቀቀ ነው

የቦይንግ 737 ማክስ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ምን ይሆን?

እርሳቸው እንደሚሉት ጢንዚዛዎቹ ከሁለት ዓመት በፊት የመጡት ከወንጂ ስኳር ፋብሪካ የምርምር ተቋም ሲሆን ያመጣቸውም በተቋሙ ለሦስተኛ ዲግሪ ማሟያ ምርምር የሚያደርግ ግለሰብ ነው።

ግለሰቡ ምርምሩን ማጠናቀቁን ተከትሎ ፋብሪካው 150 ዊቭሎችን እንደሰጧቸው ይገልጻሉ። "የጸሐይ ብርሃን አይወዱም፤ በዚህም ምክንያት ሌሊት ነው ያጓጓዝናቸው" ይላሉ በወቅቱ ስለነበረው ሲያስታውሱ።

በወቅቱም ከጉዞው ይልቅ አስቸጋሪው ሥራ ጢንዚዛዎቹን አዲስ አካባቢ ማላመድ ነበር። በመሆኑም የተለየ አካባቢ ስለሆነባቸው የተወሰኑት ሞተው ነበር።

ከሰባት ወራት በፊት በተደረገ ቆጠራም ቁጥራቸው ከሁለት ሺህ በላይ የነበረ ሲሆን አሁን ቁጥሩ እንደሚጨምር ይገምታሉ።ዶ/ር ጌታቸው ጢንዚዛዎቹ መራቢያ ሥፍራቸውን ሙሉ ለሙሉ ለቀው ወጥተዋል የሚባለውም ከእውነት ስለመራቁ ሁለት ምክንያቶችን ያስቀምጣሉ።

ዊቭልሶች መብረር የማይችሉ ከመሆኑም በላይ የሚንቀሳቀሱትም በሌሊት መሆኑ፤ ተንቀሳቀሱ ከተባለም በጣም ጥቂት ሜትር መጓዛቸውና የሚኖሩት የእንቦጭ አረም ባለበት አካባቢ በመሆኑ ለመንቀሳቀስ የውሃ ግፊትን መጠቀማቸው አንደኛው ምክንያታቸው ሲሆን፤

የተከፈተው ጣሪያ ትንሽ ከመሆኑም በላይ በአፋጣኝ ጥገና መደረጉንና በዘላቂነት ለማሰራትም ከአካባቢ ጥበቃ ጋር እየተነጋገሩ መሆናቸውን ሌላኛው ምክንያታቸው እንደሆነ ገልፀዋል።

አቶ በልስቲም በበኩላቸው "ጣሪያው ባይኖርም አይሄዱም፤ ያለ እንቦጭ መኖር አይችሉም፤ በማህበራዊ ሚዲያ የተጻፈው እና ሳይንሱ አይገናኙም" ሲሉ የባለሙያውን ሃሳብ ይደግፋሉ።

አጭር የምስል መግለጫ ዶ/ር ጌታቸው በነበሩ

ባለሙያው እንደገለፁልን ከ20 ዓመት በፊት ኡጋንዳ ውስጥ እምቦጭ ተከስቶ ነበር። ይህንን ለመቆጣጠርም የተለያዩ ዘዴዎችን ተግባራዊ አድርገዋል። ከተለያዩ ሙከራዎች በኋላ ዊቭልስን ተጠቅመው ውጤታማ ሆነዋል።

ታዲያ ይህንኑ ልምድ ለመቅሰም አምስት ባለሙያዎች ወደ ኡጋንዳ ማቅናታቸውን አውስተው ከዚህ ውጭ በተደጋጋሚ የተደረገ የውጭ ጉዞ አለመኖሩን ዶ/ር ጌታቸው ተናግረዋል።

ዊቭልሶቹ ከማራቢያው ቢወጡ በአካባቢው ዕጽዋት ላይ ምን ዓይነት ጉዳት ያስከትላሉ ያልናቸው ባለሙያው "በተለያዩ ወቅቶች የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያሳዩት፤ ነፍሳቱ ወይንም ጢንዚዛው መኖር የሚችለው እንቦጭ ላይ ብቻ ነው" ሲሉ መልሰዋል።

በመሆኑም ነፍሳቱ ወደ አርሶ አደሮች ሰብሎች ወይንም ወደ ሌሎች እጽዋት በመሄድ ጉዳት አያደርሱም።

"ወደ ሐይቁ ሲገቡ በዚያ አካባቢ ተክሎች ላይ ያላቸውን ተጽዕኖ ለማወቅም ወደ 10 የሚደርሱ ተክሎች ላይ ሙከራ አድርገናል፤ ሸንኮራ አገዳ፣ ጫት፣ ሙዝ፣ ባቄላ እና ሩዝ ላይ ሞክረን ምንም ተጽዕኖ የላቸውም" ሲሉ ዶ/ር ጌታቸው ያብራራሉ።

እርሳቸው እንደሚሉት ነፍሳቱ ተክሎቹ ላይ ቢያርፉ እንኳን የመሞት ዕድላቸው ከፍተኛ ነው። ተክሎቹን ቢመገቡም እንቁላል መጣል ስለማይችሉ አይራቡም። በመሆኑም ኬሚካልም ሆነ ሌላ ነገር መጠቀም ሳያስፈልግ የሕይወት ዑደታቸው ይቋረጣል። እምቦጭን ለማጥፋት ሦስት ዘዴዎች ተግባራዊ ይደረጋሉ። የሰው ወይንም የማሽን ጉልበት፤ እንደማንኛውም አረም ኬሚካልን፣ ወይም ሥነ ሕይወታዊ ዘዴን በማስፋፋት ነው።

በተለይ በጣና ሐይቅ ላይ ያለውን ችግር ለመቅረፍ የሰው እና የማሽን ጉልበት በስፋት ሥራ ላይ ውሏል። ከችግሩ ስፋት አንጻር ውጤቱ ግን እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። "ከሌሎች አረሙን የማጥፊያ ዘዴዎች በተጨማሪ ሥነ ሕይወታዊ ዘዴ ብንጠቀም፤ እምቦጭ የመቆጣጠር እና የመከላከል ሥራ ላይ በአዎንታዊ መልኩ የሚያግዝ ውጤት ይኖረዋል" ይላሉ አቶ በልስቲ።ባለፉት ወራት ጢንዚዛው በማራቢያው ውስጥ እንቦጩን በመራቢያነት ከመጠቀም ባለፈ ለምግብነት በመጠቀምም ጉዳት እያደረሰበት መሆኑን የእስካሁኑ ምርምር ውጤት አሳይቷል።

ዶ/ር ጌታቸው እንዳብራሩልን የዊቭል ሕይወት ዑደት እንቁላል፣ ላርቫ፣ ፑፓ እና አደልት የሚባሉ ደረጃዎች አሉት። አደልት የሚባሉት የቅጠሉንና የግንዱን ውጫዊ ክፍል ይመገባሉ። ይህ ክፍል ተጎዳ ማለት ምግብ ማዘጋጀት ስለማይችል ይሞታል።

ሴቷ ዊቭል በቀን እስከ 5 እንቁላል የእንቦጭን ግንድ ቦርቡራ ትጥላለች። ከዚያ ወደ ላርቫ ነው የሚቀየረው። በላርቫ ደረጃ ደግሞ ወደ ሁለት ወር ይቆያል። በዚህ ወቅት ላርቫው እስከ ግንዱ ድረስ በመዝለቅ ውስጣዊና ውጫዊ ጉዳት ያደርስበታል።

የእርሶ መሳሪያ ሚዲያ ፕሌይ ባክን ማጫወት ኣልተቻለም።
በባህር ዳር የእምቦጭ አረምን የሚያጠፉት ጢንዚዛዎች አልጠፉም

ከላይም አደልቱ ይመገበዋል፤ ላርቫው ደግሞ ከውስጥ ይበላዋል። ላርቫው ትልቁን ጉዳት ስለሚያደርስ ተመራጭ ነው።

እንቁላሎቹ የሚጣሉት እንደስፖንጅ በሆነው የእንቦጩ ግንድ ውስጥ ነው። በዚህም ግንዱ ስለሚከፈት ውሃ ይገባና ክብደቱን ጨምሮ ወደ ውሃው ውስጥ ገብቶ እንዲበሰብስ ያደርገዋል።

"እስካሁን በሥነምህዳሩ ላይ ተጽዕኖ የለውም፤ ባህርዳር ዩኒቨርሲቲም አጥንቷል፤ በዩጋንዳ የታየውም ይህ ነው" ሲሉ አቶ በልስቲ ያክላሉ። እምቦጭ ጣና ሐይቅን ጨምሮ በሃገሪቱ የተለያዩ የውሃ ክፍሎች ላይ ጉዳት እያደረሰ ባለበት ወቅት ይህ ሥነ ሕይወታዊ ዘዴ እስካሁን ተግባራዊ አልተደረገም የሚሉት ዳሬክተሩ በፍጥነት ወደ ሥራ ገብተው ኅብረተሰቡ እፎይ ይላል የሚል ግምት ነበራቸው።

"ይህ ባዮሎጂካል ዘዴ ስለማይታወቅ በሚዲያው ብዙ ሰው ተሳልቆብናል፤ ይህቺ ናት ወይ እምቦጭን የምታጠፋው ተብሏል . . . " ይላሉ።

ዶ/ር ጌታቸው በበኩላቸው ለልምድ ልውውጡ ኡጋንዳ አቅንተው በተመለሱ ወቅትም ይህንኑ ተግባራዊ ለማድረግ 35 ገጽ ያለው ብሔራዊ መተግበሪያ ሰነድ እንዳዘጋጁ ነግረውናል።"የእኛ ሰው ስሜታዊ ነው፤ መጀመሪያ ትልቁም ትንሹም 'ማሽን ማሽን' ብሎ ጮኸ፤ አሁን ደግሞ የክልሉም ሆነ የፌደራል መንግስት እኛን መደገፍ ጀምሯል" ብለዋል።

"ዊቭል ለመጠቀም ፈቃድ ያስፈልጋል" የሚሉት ዶ/ር ጌታቸው። ጥያቄው ለሚመለከተው አካል የቀረበ ሲሆን ሥራው ሲጀመር ወዲያውኑ ዊቭሎችን ወደ ጣና ማጓጓዝ የለብንም ብለው እንደወሰኑ ያስረዳሉ።

በመጀመሪያ በመረጧቸው አራት ቦታዎች በሚሰሩ ኩሬዎች በስፋት ማምረት እንደሚጀምሩ አክለዋል።

የካቲት ላይ ሥራ ለመጀመር ቢያቅዱም በግዢ መጓተት ምክንያት እስካሁን መቆየታቸውን ገልፀው በሚቀጥለው ዓመት ሙሉ ለሙሉ ወደ ሥራ እንደሚገቡ አቶ በልስቲ ለቢቢሲ አስታውቀዋል።

የወጣቶች ዘመቻ በእምቦጭ አረም ላይ

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ