በናይሮቢ ወንዞች የአስከሬኖች መገኘት አሳሳቢ ሆኗል

በናይሮቢ ከሚገኙ ወንዞች አንዱ Image copyright Getty Images
አጭር የምስል መግለጫ በናይሮቢ ከሚገኙ ወንዞች አንዱ

የኬንያ ባለሥልጣናት በዋና ከተማዋ ናይሮቢ እያካሄዱት ባለው ወንዞችን የማጽዳት ዘመቻ ወቅት ተጨማሪ ሁለት የሕጻናት አስከሬኖች ማግኘታቸውን አስታወቁ።

በርካታ ሰዎችን ባሳተፈው በዚህ የጽዳት ዘመቻ በናይሮቢ ከሚገኙ ትላልቅ የድሆች መኖሪያ የሆነው የኮሮጎቾ አካባቢን አቋርጦ በሚያልፈውና ክፉኛ እንደተበከለ ከሚነገርለት ወንዝ ነው አስከሬኖቹ የተገኙት።

22 ኢትዮጵያዊያን ናይሮቢ ውስጥ ተያዙ

መንታ እንደሆኑ የተገመቱት ሕጻናት በወንዙ ውስጥ ሲገኙ በፕላስቲክ መያዣ ውስጥ እንደሆነ የተናገሩት ባለስልጣናቱ አንደኛው ሕይወቱ ያለፈ ሲሆን ሌላኛው እንደሚተነፍስ ነገር ግን ለማትረፍ እንዳልተቻለ ገልጸዋል።

የናይሮቢ ከተማ ገዢ የሆኑት ማይክ ሶንኮ ጉዳዩን አስመልክተው እንደተናገሩት ይህ በተደጋጋሚ እየተከሰተ ያለው ነገር በጣም አሳሳቢ እንደሆነና ፖሊስ እሳቸው የሚጠረጥሯቸው ሆስፒታሎችና ክሊኒኮች ላይ ምርመራ እንዲያደርግ እንደሚፈልጉ ገልጸዋል።

አስከሬናቸው የተገኘው ህጻናት ወላጆች ማንነት ስለማይታወቅ በተገኙበት አካባቢ እንዲቀበር መደረጉን የናይሮቢ ከተማ ገዢ ቃል አቀባይ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ኬንያዊቷ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ሞታ ተገኘች

ባለስልጣናት ጨምረውም በከተማዋ በሚካሄደው ወንዞችን የማጽዳት ዘመቻ ባለፉት ጥቂት ወራት የበርካታ ሰዎች አስከሬኖች እንደተገኙ ጠቅሰው፤ በተለይ የጨቅላ ህጻናቱ አስከሬን በተለያዩ ስፍራዎች ከሚፈጸሙ የጽንስ ማቋረጥ ድርጊቶች ጋር ሊያያዝ እንደሚችል አመልክተዋል።

ቀደም ሲል በተካሄዱት የጽዳት ዘመቻዎች የስምንት ሕጻናትን አስከሬን ጨምሮ የአራት ጎልማሶች አስከሬኖች ከወንዞቹ ውስጥ መገኘቱም ተገልጿል።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ