ገበታ ለሸገር፡ ከጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ ጋር ማዕድ የቀረቡት ሰዎች ምን ይላሉ?

ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንግዶችን ተቀብለው ሲያስገቡ Image copyright Office of the Prime Minister-Ethiopia

አቶ ዮሐንስ መኮንን በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሥነ-ሕንፃና የቅርስ ጥበቃ መምህር ናቸው። የዳግማዊ አጤ ሚኒሊክ የቤተ መንግሥት የግብር አዳራሽ እድሳት ሥራው ከተሰራለት በኋላ እያንዳንዱን ቦታ ለማስጎብኘት በበጎ ፈቃደኝነት ከተመረጡና ከተሳተፉ ስምንት ባለሙያዎች መካከል አንዱ መሆናቸውን አጫውተውናል። በእራቱም ላይ ተጋብዘው ከጠቅላዩ ጋር አብረው ገበታ ቆርሰዋል።

የ5 ሚሊዮን ብር እራት ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ጋር

"እራት ለመመገብ አይደለም የምንሄደው" በላይነህ ክንዴ

ተጋባዥ እንግዶችን በማስጎብኘት ሂደት እርሳቸው ብቻቸውን ከ40 በላይ ቻይናውያን ማስጎብኘታቸውን የጠቀሱት አቶ ዮሐንስ አንድ ሰው በአማካይ 30 ሰው በአንዴ ያስጎበኝ ነበር በማለት የነበረውን ሁናቴ ያስታውሳሉ።

ከእንግዶቹ መካከልም በጓድ መንግሥቱ ኃይለማርያም ዘመን ቤተ መንግሥቱን ለማየት እድል ያገኙ የውጪ እንግዶች ሲኖሩበት በወቅቱ የነበራቸውን ትዝታ በማጋራት መደመማቸውን እንዳጫወቷቸው ይናገራሉ።

አጤ ኃይለ ሥላሴ የተቀበሩበትን ስፍራ፣ ከላይ የጓድ መንግሥቱ ቢሮ ከታች የእርሳቸው መቃብር፣ ስድሳዎቹ ሰዎች የተረሸኑበት፣ ጄነራሎቹ የታሰሩበትን ሁሉ ማስጎብኘታቸውን አጫውተውናል።

"ቤተ መንግሥቱ ያረፈው 40 ሔክታር ላይ ነው" የሚሉት ባለሙያው ከዚህ ሁሉ ሥፍራ ለጎብኚ ክፍት ሆኖ በትናንትናው እለት የመታየት ወግ የደረሰው አንድ አራተኛው ነው ሲሉ ግምታቸውን ያሰፍራሉ።

አቶ ይትባረክ ዘገዬ የዋርካ ትሬዲንግ ሃውስ ኃ/የተ/የግ/ማ ባለቤት ሲሆኑ ትናንት በተካሄደው 'ገበታ ለሸገር' የእራት ግብዣ ላይ ከተሳተፉት አንዱ ናቸው።

ፕሮጀክቱን መደገፍ አለብኝ፤ መሰራትም አለበት ብለው 5 ሚሊየን ብር በመክፍል ገበታ ለሸገር እራትን ተጋብዘዋል፤ ፕሮጀክቱንም ደግፈዋል።

" ዋናው እራቱ ሳይሆን ዓላማው ነው፤ እራቱም በጣም ጥሩ ነበር" የሚሉት አቶ ይትባረክ 'ገበታ ለሸገር'ን ከጠበቁት በላይ እንዳገኙት ይናገራሉ።

ገና ወደ ቤተመንግሥት ሲገቡም ጉብኝት እንዳዳረጉና ታሪካቸውን በማወቃቸው እርካታ እንደተሰማቸው ይገልፃሉ።

ለወደፊቱ ፊልም ይሰራበታል እንዲሁም ከመጭው መስከረም ወር ጀምሮ ለጎብኝዎች ክፍት ይሆናል የተባለውን ቤተ መንግሥት ጎብኝተዋል።

እርሳቸው እንደሚሉት ቤተ መንግሥቱን ሲጎበኙ የመጀመሪያ ጊዜያቸው ነው። በዚህም ከአጤ ሚንሊክ ጀምሮ፤ አጤ ኃይለ ሥላሴ እንዲሁም ጠቅላይ ሚንስትሮችና ፕሬዚዳንቶች ሲኖሩበት የነበረውን ቦታ በማየታቸው ደስታ ተሰምቷቸዋል።

ቤተ መንግሥቱ በተለይ በደርግ ዘመን ብዙ ታሪክ የተሰራበት በመሆኑ ቦታውን መጎብኘታቸው የረኩበት እንደሆነ ይናገራሉ። ለሌላው ትውልድ ሊተላለፍ የሚችል ታሪክና ቅርስ ነው ሲሉም ያክላሉ።

የሥነ-ሕንፃ ባለሙያው አቶ ዮሐንስ ለእራቱ ከታደሙት 300 የሚሆኑ እንግዶች መካከል ገሚሱ ኢትዮጵያን ገሚሱ ደግሞ የውጭ ሀገር ዜጎች ነበሩ ብለውናል።

"ቻይና በአፍሪካ ውስጥ የታይታ ፕሮጀክት የላትም" ፕሬዚዳንት ሺ ዢፒንግ

ተጋባዥ እንግዶች በአጠቃላይ እኩል ስላልደረሱ ቀድመው የመጡት የአጤውን ቤተመንግሥትና ተያያዥ ቅርሶች ከጎበኙ በኋላ የኮክቴል ግብዣ እንደተደረገላቸው አቶ ዮሐንስ ጨምረው ያስረዳሉ።

እግረመንገዳቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከእንግዶች ጋር በተናጠልም በቡድንም በአጤ ሚኒሊክ የግብር አዳራሽ በር ላይ ፎቶ ሲነሱ ነበር ብለዋል።

አቶ ይትባረክ ዘገዬም " ከጠቅላይ ሚንስትሩ ጋር ፎቶ ግራፍ መነሳትና መጨባበጥ ብቻም ሳይሆን እንደ ቅርብ ዘመድ ተሳስመናል" ይላሉ።

የኮክቴሉን መሰናዶና መስተንግዶ የተወጣው ሸራተን እንደሆነም አቶ ዩሃንስ ይናገራሉ።

Image copyright Office of the Prime Minister-Ethiopia

እምቢልታ ይነፋ ነጋሪት ይጎሰም

እንግዶች ተጠቃልለው ሲመጡ በጥንቱ ወግና ባህል መሰረት ነጋሪት እየተጎሰመ፣ ግራና ቀኝ የቆሙ የሀገር ባህል ልብስ የለበሱ ሰዎች እምቢልታ እየነፉ ተጋባዥ እንግዶች ወደ ምግብ አዳራሹ ገቡ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ሁሉም እንግዶች ተጠቃልለው እስኪገቡ ድረስ ደጅ በመሆን እንግዶቹን እጅ እየነሱ እንዲገቡ ይጋብዙ ነበር ብለዋል አቶ ዮሐንስ።

አቶ ይትባረክ ከዚህ ቀደም ከነበሩ ጠቅላይ ሚንስትሮች ጋር የመገናኘትና የመጨባበጥ እድሉ ቢኖራቸውም ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ግን ለየት ይላሉ ብለዋል።

የላሙ ፕሮጀክት ቦርድ አባላት በኢትዮጵያ ጉብኝት ሊያደርጉ ነው

ምክንያታቸውንም " እርሳቸው የሰው ቀረቤታና ያለ መሰልቸት ቀርበው የማነጋጋር ችሎታ አላቸው" ሲሉ ያስቀምጣሉ።

በአዳራሹ ሲገኙም " ፍቅር እስከ መቃብርን መፅሐፍ ስላነበብኩ ፊታውራሪ መሸሻ ግብር የሚያበሉበት እልፍኝ ነው የታወሰኝ" ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሁሉም እንግዶች ከገቡ በኋላ ወደ አዳራሹ ገብተው ፕሮጀክታቸውን በሚመለከት ገለፃ አድርገዋል።

በእያንዳንዱ ተጋባዥ ጠረጴዛ በመምጣትም እየጨበጡ ከየትኛው ተቋም እንደመጡ ይጠይቁ እንደነበርና 'ሸገርን በማስዋብ ፕሮጀክት ላይ ተሳታፊ በመሆናቸው ምስጋናቸውን ማቅረባቸውን' አጫውተውናል።

የአብርሐም ወልዴ 'ባላገሩ የባህል ኦርኬስትራ' አስደናቂ ዝግጅት አቅርቧል ያሉት አቶ ዮሐንስ ጠቅላይ ሚንስትሩም አብርሐምን በአደባባይ አመስግነውታል። እንደ ማህሙድ አህመድ ያሉ ሌሎች አንጋፋ ድምፃውያንም ዝግጅታቸውን አቅርበዋል።

Image copyright Office of the Prime Minister-Ethiopia

ምን ተወራ?

ዶክተር አብይ በትናንትናው የእራት ግብዣ ላይ ለእንግዶቻቸው ስለ አዲስ አበባ የወንዞች ልማት ፕሮጀክት እና ሌሎች አዲስ አበባ ውስጥ የሚተገበሩ ፕሮጄክቶች ንግግር አድርገዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ብቻ ሳይሆኑ እንደ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ያሉ ረዳቶቻቸውም ቤተመንግሥት አካባቢ ሊሰራ ስለታሰበውና 20 ሺህ ሰው ያስተናግዳል ስለተባለው ቤተ መፃህፍትም ገለፃ በማድረግ ምን ሊመስል እንደሚችል የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምስል ቀርቧል።

ቤተመፃህፍቱ የሚሰራው ፓርላማው አካባቢ በሚገኝ ሰፊ ቦታ ላይ ይሆናል።

የታችኛው ኢዮ ቤሊዮ ቤተመንግስት ዲዛይንም መጠናቀቁን ጠቅላይ ሚኒስትሩ መናገራቸውን የገለፁት አቶ ዮሐንስ ከፈረንሳይ መንግሥት ጋር በትብብር እየተሰራ ነው ማለታቸውንም አክለውልናል።

ከ2 ቢሊየን ዶላር በላይ ወጪ የሚደረግበት የለገሃሩ ፕሮጄክት በቅርቡ እንደሚጀመርም ተናግረዋል- ጠቅላይ ሚኒስትሩ። ከሳር ቤት እስከ ጎተራ ማሳለጫ ያለውን የትራፊክ ፍሰት የሚያሳልጥ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክትም ተነስቷል እንደ አቶ ዮሐንስ።

"በአጠቃላይ ስድስት ፕሮጀክቶች በጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር ውስጥ ተካትተዋል።" ይላሉ የሥነ ሕንፃ ባለሙያው።

ጓድ መንግሥቱ እንባ የተናነቃቸው 'ለት

ከንግግራቸው እንደ ቁልፍ መልዕክት የወሰድኩት ይላሉ አቶ ዮሐንስ 'አቧራ ከማስነሳት አሻራ ማስቀመጥ' የሚለውን ነው በማለት በተለያየ ምክንያት ግጭቶች ቀስቅሶ አቧራ ማስነሳት ቀላል ነገር ነው። ለትውልድ የሚቆይ አሻራ ማቆየት ግን በጣም ጠቃሚ ሥራ ነው የሚል መልዕክት ማስተላለፋቸውን ነግረውናል።

በንግግራቸው መጨረሻም ላይ የዝግጅቱ ታዳሚዎች በሙሉ ቀኝ እጃቸውን ወደ ላይ እንዲያነሱ በመጠየቅ፣ በኋላም አውራጣታቸውን እንዲያሳይዋቸው ካደረጉ በኋላ፣ አውራ ጣታቸውን ፊት ለፊታቸው ያለ ገበታ ላይ እንዲያሳርፉ አድርገው ቃል አስገብተዋቸዋል።

እንግዶቹ ገበታቸው ላይ አውራ ጣታቸውን ካኖሩ በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚሉትን ደግመው በማለት ቃል ገብተዋል።

በተባበረ ድምፅ "አሻራዬን አኖራለሁ፤ ሀገራዊ ግዴታዬን እወጣለሁ" በማለት ቃል እንደገቡም ያስታውሳሉ።

ከዚህ ሁሉ በኋላ የእራት ግብዣ ተካሂዷል።

ሻኛውን ከዳቢት፣ ቀዮን ከጮማ ማወራረድ ለፈለገ ቁርጥ ስጋ በታዳሚው ዙሪያ እየዞረ፣ ጠጅ በብርሌ ተደርጎ የቀረበ ሲሆን ለውጪ ዜጎቹም የፈረንጅ ምግቦች ቀርበው ተስተናግደዋል።

"በታሪክ መፃህፍት እንዳነበብኩት የመሳፍንቶቹ አይነት ግብዣ ነው የተደረገልን" ይላሉ አቶ ዮሐንስ።

ኢትዮጵያ ለሱዳንና ለጅቡቲ ኃይል ማቅረብ ማቋረጧ ተገለፀ

ቻይናውያን ለብቻቸው ለ65 ሰው መክፈላቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል ያሉት አቶ ዮሐንስ ከውጪ ዜጎቹ በብዛት ቻይናውያን እንደነበሩ ነግረውናል። በርካታ ሴቶችም በአስተናጋጅም በተስተናጋጅነትም መገኘታቸውን ይጠቅሳሉ።

"የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ወ/ሮ መዐዛ አሸናፊ፣ የሸገር ሬዲዮ መስራችና ባለቤት ወ/ሮ መዐዛ ብሩ ነበሩ።"

እንግዶች ማዕድ የቆረሱበት አዳራሽ ፈረስ የሚያስጋልብ ስለነበር እንግዶች እንደልባቸው ለመንቀሳቀስ እድል ነበራቸው ያሉት አቶ ዮሐንስ ሰዎች ከፕሮጀክቱ ጋር የተገናኘ ወሬ፣ ቤተመንግሥቱ በመጎብኘታቸው የደስታ ባህር ውስጥ ነበሩ በማለት የታዘቡትን አጫውተውናል።

"ቤተመንግሥቱ ውስጥ መግባት፣ በአጤ ሚኒሊክ የግብር አዳራሽ ውስጥ በመገኘት መመገብ፣ ለመንግሥት ከፍተኛ ባለስልጣናት ያለው ስሜት በራሱ ቀለል ያለ እንዲሆን አድርጎታል።"

አቶ ዮሐንስ በሙያቸው የሥነ ሕንፃ ባለሙያ ስለሆኑ ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይን ሲያገኟቸው "የተጀመረው ሥራ ጥሩ ነው፤ ግን ብዙ ባለሙያዎች ተሳትፈው ልናዳብረው እንችላለን" ብለው እንደነገሯቸውም ያስታውሳሉ።

Image copyright Office of the Prime Minister-Ethiopia

አቶ ይትባረክ በቤተ መንግሥቱ ውስጥ ያዩትን ለውጥ በማንሳት ይህ ፕሮጀክት በአጭር ጊዜ ውስጥ ተተግብሮ ሥራ ላይ ይውላል የሚል እምነት አላቸው።

ሲጠናቀቅም የቱሪስት መዳረሻ በመሆን ለድሃው የአገሪቱ ሕዝቦች ጠቀሜታ ይኖረዋል የሚል ተስፋ ሰንቀዋል።

"በተለይ በአገር ውስጥ ያሉት መዝናኛዎች ሆቴሎች ናቸው፤ በሆቴል ደግሞ መጠጥና ምግብ ብቻ ነው ያለው" የሚሉት አቶ ይትባረክ ይህኛው ከእነዚህ የመዝናኛ ሥፍራዎች ለየት ስለሚል ለአገር ውስጥም ሆነ ለውጭ አገር ዜጎች ጠቀሜታ እንደሚኖረው አክለዋል።

በቀጣይ ገንዘብ ስለማሰባሰብ በግብዣ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የተባለ ባይኖርም፤ አገርን ለማልማትና ለማሳደግ በምንጠየቅበት ማዋጣትና መስራታችን አይቀርም ብለዋል።

ቢቢሲ፡ ተመሳሳይ የ5 ሚሊየን እራት ቢዘጋጅ ይሳተፋሉ?

አቶ ይትባረክ፡ አቅሜ ከቻለ አስር ጊዜም ቢሆን እሳተፋለሁ

እግረ መንገድ የሚነሱ ነጥቦች

በእርግጥ አዲስ አበባ ዓመቱን ሙሉ ኩልል ብሎ የሚፈስ ወንዝ አላት ይሆን? የሚለው ጥያቄ ከፕሮጀክቱ መፀነስ ጀምሮ በባለሙያዎች እንደሚነሳ የሚናገሩት አቶ ዮሀንስ ይህንን ሀሳብ የሚያነሱ ባለሙያዎች እነ አምስተርዳምን ምሳሌ አድርገው ይጠቅሳሉ ይላሉ።

አቶ ዮሐንስ ግን እንደዚህ አይነት መናፈሻ፣ መልከዓ ምድሩ አዲስ አበባ ውስጥ መሰራቱ በራሱ እንደ በጎ ጅምር በመውሰድ እርሱ ላይ ማደርጀት የምንችል ይመስለኛል በማለት በፕሮጀክቱ ላይ ያላቸውን እምነት ይገልጣሉ።

አክለውም የዲዛይን ሀሳቡ ላይ ሀገርኛ የሆኑ ነገሮች እንዲጨመሩ ጥረት ተደርጓል፤ በጥሩ ሁኔታ ዲዛይን ተደርጓል የሚያስመሰግንም ተግባር ነው በማለት ሀሳባቸውን ይቋጫሉ።

የእለቱ መርሀ ግብር ከቀኑ 9፡00 ጀምሮ ከምሽቱ 3፡50 ላይ ተጠናቋል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ፕሬስ ሴክሬተርያት ብለኔ ሥዩም ለቢቢሲ እንደተናገሩት የእራት ግብዣው የተካሄደበት የአጤ ሚኒሊክ የግብር አዳራሽ ከአጤ ኃይለ ሥላሴ ጀምሮ ተዘግቶ የቆየ ሲሆን ለመጀመሪያ ጊዜ የተከፈተው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ ነው።

ተያያዥ ርዕሶች

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ