ለልመና ታግቶ የነበረው ታዳጊ ከዓመታት በኋላ ተገኘ

ሳሙኤል አብዱራሂም የታገተው በሰባት ዓመቱ ነበር

ሳሙኤል አብዱራሂም ይባላል። በደቡብ ናይጄሪያዋ ካኖ ከተማ ውስጥ ከሚገኘው የቤተሰቦቹ ቤት ታግቶ የተወሰደው የሰባት ዓመት ታዳጊ ሳለ ነበር።

ቤተሰቦቹ ሳይክል ለመንዳት ከቤት እንደወጣ ገምተው ነበር። ነገር ግን ሳሙኤል በታጋቾች እጅ ወድቆ ነበር።

ታላቅ እህቱ ፊርዳውሲ ኦኬዚ ሳሙኤልን ለማግኘት ያልፈነቀሉት ድንጋይ እንደሌለ ትናገራለች።

ወንድሟ ሲታገት እሷ የ21 ዓመት የዩኒቨርስቲ ተማሪ ነበረች። ወደቤተሰቦቿ ስትደውል አዘውትሮ ስልኩን የሚመልሰው ሳሙኤል ድምጹ ሲጠፋባት ነበር የወንድሟን መታገት ያወቀችው።

ከአራት ሚስቶቻቸው 17 ልጆች የወለዱት አባታቸው ወንድሟ በጠፋበት ወቅት ቤት ውስጥ የነበረችው ሞግዚት በቁጥጥር ሥር እንድትውል አድርገው ነበር። በጋዜጣ ማስታወቂያ በማውጣት ልጃቸውን ማፈላለግም ጀምረው ነበር።

ከማደጎ ልጅነት ወደ እውቅ ገጣሚና የማንችስተር ዩኒቨርሲቲ ሃላፊነት

በስተመጨረሻ የሳሙኤል አባት ተስፋ ቆርጠው ልጃቸው እንደሞተ ቤተሰቡ ማመን እንዳለበት ነገሯቸው። እህቱ ፊርዳውሲ ግን ተስፋዋ አልከሰመም ነበር።

ከዩኒቨርስቲ ከተመረቀች በኋላ ሀይማኖቷን ከእስልምና ወደ ክርስትና ቀይራ ቤተክርስቲያን ትሄድ ጀመር።

እናቷ የሚሠሩትን ካናቴራ እየሸጠች ራሷን ለማስተዳደር ብላ የካናቴራ መደርደሪያ እያዘጋጀች ሳለ አንድ የሚለምን ሰው "ስለ አላህ" አያለ ምጽዋት ሲጠይቅ ሰማች። የሚለምነው ሰው አይነ ስውር ሲሆን፤ አንድ ልጅ ከፊት ለፊት እየሄደ ሲመራው ተመለከተች።

አይነ ስውሩን የሚመራውን ታዳጊ በአንክሮ ስትመለከት ታናሽ ወንድሟ ሳሙኤል መሆኑን ተረዳች።

እንዴት ታገተ?

ሳሙኤል አሁን 30 ዓመት ሆኖታል። ከቤተሰቦቹ ቤት እንዴት እንደተሰረቀ ባያስታውስም፤ አጋቾቹ ረዥም መንገድ በባቡር እንደወሰዱት ይናገራል። ሌጎስ ውስጥ በርካታ በልመና የሚተዳደሩ አካል ጉዳተኞች የሚኖሩበት አካባቢ ከተወሰደ በኋላ፤ በቀን በ500 ናይራ (140 ብር ገደማ) አይነ ስውር እንዲመራ ተደረገ።

ሴቶች 'ፌሚኒስት' መባልን ለምን ይጠላሉ?

ናይጄሪያ ውስጥ የሚለምኑ አይነ ስውሮችን የሚመሩ ታዳጊዎች መመልከት የተለመደ ነው።

ሳሙኤልን ለሚለምኑ ሰዎች ያከራዩት ሴት ሌሎች ታዳጊዎችም ያከራዩ እንደነበረም ያስታውሳል።

የባርነት ሕይወት

በልመና ላይ የተሰማሩ ሰዎች ሳሙኤልን ለሳምንት ወይም ለወር ይከራዩት ነበር።

"ባሪያቸው ነበርኩ። የትም የመሄድ መብት አልነበረኝም" ይላል።

የተነጠቀ ልጅነት

አልፎ አልፎ ከሚለምኑት ሰዎች ልጆች ጋር ይጫወት ነበር። ሰዎች ምግብ ሳይሰጧቸው ሲቀሩ በየምግብ ቤቱ እየተዘዋወሩ ትራፊ ምግብ ይለቃቅሙ ነበር። ቆሻሻ መጣያ ገንዳ ውስጥ የተጣለ ምግብም ይመገቡ ነበር።

ሳሙኤል ጎረቤት ሀገር ቤኒን ድረስ ለልመና ተወስዷል።

"አይነ ስውራን የመስማት ችሎቻቸው ከፍተኛ ነው። የሰው ድምጽ ወደሰሙበት ቦታ እንድወስዳቸው ያደረጉ ነበር" ይላል።

"ተአምር"

እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር 2000 ላይ 'ዊነር ቻፕል' የተባለ ቤተክርስቲያን እርዳታ መስጠት መጀመሩን የሚለምኑ ሰዎች ሰምተው ሳሙኤልን አስከትለው ሄዱ። ቤተክርስቲያኑን የሳሙኤል እህት ፊርዳውሲ ታዘወትረው ነበር።

"ሳየው መሬት ላይ ወደቅኩ" ትላለች ቅጽበቱን ስታስታውስ።

የቤተክርስቲያኑ አገልጋዮች ሳሙኤልን ሰውነቱን አጥበው ልብስ ቀየሩለት። የሳሙኤል መገኘት "ተአምር ነው" ተባለ።

ሳሙኤል ከተገኘ በኋላ ሌሎች ታዳጊዎችንም ከባርበነት ማውጣት እንደነበረባት እህትየው ትናገራለች።

Image copyright Firdausi Okezie

"ባደጉ አገሮች እንደዚህ ያሉ ወንጀሎችን ለፖሊስ ሪፓርት ማድረግ ይቻላል። እኛ ሀገር ግን ፖሊሶች ጉቦ ይጠይቃሉ። እኔ ደግሞ በወቅቱ ገንዘብ አልነበረኝም" ስትል ሌሎች ታዳጊዎችን ማዳን አለመቻሏን ታስረዳለች።

የ13 ዓመት ወንድሟን መንከባከብ ካሰበችው በላይ ከባድ ነበር። ለልመና የሚመራቸው አይነ ስውራን አጥብቀው ይይዙት የነበረው ቀኝ እጁ ተጣሞ ስለነበር ፊዚዮቴራፒ ተከታትሏል።

"ቂም አልይዝም"

ሳሙኤል ለስድስት ዓመታት ያለትምህርት በማሳለፉ ማንበብና መጻፍ አይችልም ነበር። እሱን ትምህርት ቤት ማስገባትም ቀላል አልነበረም።

እድሜው ከመጀመሪያ ደረጃ ተማሪነት አልፏል በሚል ብዙ ትምህርት ቤቶች አልተቀበሉትም። በስተመጨረሻ ሳሙኤል ቤተክርስቲያን ውስጥ ሲገኝ የተመለከቱ ግለሰብ ሳሙኤልን ትምህርት ቤታቸው ለማስገባት ፈቀዱ።

Image copyright Samuel Abdulraheem

በ17 ዓመቱ የዩኒቨርስቲ መግቢያ ፈተና ወሰደ። በጥሩ ውጤት አልፎም ኬሚካል ኢንጅነሪንግ ማጥናት ጀመረ።

የአራተኛ ዓመት ተማሪ ሳለ ግን የሌሎች ተማሪዎችን የቤት ሥራ ሲሠራ ተይዞ ከዩኒቨርስቲው ተባረረ። አሁን በግንባታ ሥራ እራሱን ያስተዳድራል።

"ገንዘብ ሲኖረኝ ትምህርቴን እቀጥላለሁ" የሚለው ሳሙኤል፤ ኮምፒውተር ሳይንስ የማጥናት ፍላጎት እንዳለው ይገልጻል።

ታግቶ የነበረበትን ዓመታት ሲያስብ ትምህርት የቀሰመበት ወቅት እንደነበረ ያምናል። "ሰዎች ምንም ቢያደርጉ ቂም አልይዝም። አንድ የሕይወት አካል እንደሆነ አስባለሁ" ይላል።

"በወንድሜ ለአምስት ዓመታት ተደፍሬአለሁ"

የሚለምኑ ሰዎች ሲገጥሙት ገንዘብ ሳይሆን ምግብ ይሰጣል። እሱን ተጠቅመው ይለምኑ የነበሩ አይነ ስውራን ለሱ ገንዘን እንደማይሰጡት ማስታወሱ በልመና ላይ የተሰማሩ ሰዎችን የሚያይበትን መንገድ ቀይሮታል።

ሰዎች ታዳጊዎችን ከሚለምኑ ሰዎች ጋር ሲያዩ ገንዘብ ሰጥቶ ከማለፍ ይልቅ "ይህ ልጅ እርዳታዬን ይፈልግ ይሆናል" ብለው ቆም ብለው እንዲያስቡም ይጠይቃል።