ህልማችንን ለምንድነው የማናስታውሰው?

ህልም Image copyright Emanuel Lafront

ለብዙዎቻችን ህልም የማይያዝ የማይጨበጥ ነገረ ነው። ዕድለኛ ከሆንን ትንሽ ትንሽ ብልጭታዎችን ልናስታውስ እንችላለን። አንዳንዴም ከብዙ ቀናት በፊት ያየነውን ህልም ድንገት ልናስታውስ እንችላለን።

ግን ለምን ህልማችንን ሙሉ በሙለ አናስታውስም?

ህልም ሰዎች ከሚያስቡት በላይ የተወሳሰበ ነገር ነው። ሰውነታችን ቀኑን ሙሉ ድካሙን ለማሳረፍ እንቅልፍ እንቅልፍ ሲለን አንዳንድ የአንጎላችን ክፍሎች ግን ሌሊቱን ሙሉ ብዙ ነገሮችን ሲያከናውኑ ያድራሉ።

አልኮል የማይሸጥባቸው መጠጥ ቤቶች

አረጋውያንን በነጻ የሚያሳፍረው ባለታክሲ

አንጎላችንም ከሃሳብ ሃሳብ፤ ከቦታ ቦታ እኛ ልናስበው ከምንችለው በላይ በሆነ ፍጥነት ይንቀሳቀሳል።

ህልም 'ራፒድ አይ ሙቭመንት' ወይንም በግርድፉ ፈጣን የአይን እንቅስቃሴ ከሚባለው ስርአት ጋር በእጅጉ የተያያዘ ነው። በዚህ ስርአት ውስጥ ሰውነታችን ሲገባ አይናችን እንደተከደነ በፍጥነት ይንቀሳቀሳል፣አተነፋፈሳችን ይቀየራል፣ የደም ዝውወውራችን ይጨምራል፤ በመጨረሻም ሰውነታችንን ማዘዝ ወደማንችልበት ደረጃ እንደርሳለን።

ይህ ደረጃ ደግሞ 'አቶኒያ' ተብሎ ይጠራል። ወደዚህ ደረጃ የምንገባው በአማካይ እንቅልፍ ከወሰደን ከአንድ ሰአት ከ30 ደቂቃ በኋላ ነው። በዚህ ሰአት አንጎላችን ለህልም ዝግጁ ይሆናል።

የስነአእምሮ ባለሙያ የሆኑት ፕሮፌሰር ዲዲዬር ባሬት እንደሚሉት የተወሳሰቡ ታሪኮችና ኩነቶች የበዙባቸው ህልሞች ለማስታወስ እጅግ ከባድ እንደሆኑ ያስረዳሉ።

'በሰውነታችን ውስጥ 'ኖራድሬናሊን' የተባለ ሆርሞን የሚገኝ ሲሆን ዋነኛ ስራው ሰውነታችን እርምጃ እንዲወስድና የሚያደርገውን ነገር እንዲቆጣጠር ማድረግ ነው። ጥልቅ እንቅልፍ ውስጥ ስንገባ ደግሞ ይህ ሆርሞን መጠኑ በጣም ይቀንሳል። ለዚህም ነው ብዙዎቹን ህልሞቻችንን የማናስታውሰውና ከህልማችን ጋር የሚመጣጠን እርምጃ መውሰድ የማንችለው።

በሉዊዜን ዩኒቨርሲቲ የእንቅልፍ ምርምር ዶክተር የሆኑት ፍራንሲስካ ሲክላሪ በእንቅልፍና በህልም መካከል ጥርት ያለ ልዩነት መኖሩና ህልማችንን አለማስታወሳችን ጥሩ ነው ይላሉ።

'' ህልማችንን ሙሉ በሙሉ የምናስታውስ ቢሆን ኖሮ ከእንቅልፋችን ስንነቃ ግራ እንጋባ ነበር። ምክንያቱም የትኛው ዓለም ትክክለኛው እንደሆነ መለየት ሊያቅተን ይችላል። ''

''በህልማችን የሆኑትንና በእውነተኛው ዓለም የሆኑትን ማቀላቀል ከጀመርን ደግሞ ወደ እብደት ልንጠጋ እንችላለን።''

የምግብ ምርጫዎ ስለማንነትዎ ይናገራል?

ህልማቸውን ሙሉ በሙሉ የሚያስታውሱም ሰዎች አሉ። እነዚህ ሰዎች በህልማቸው ያዩትን ነገር ከእንቅልፋቸው ሲነቁ ይቀጥሉታል።

ዶክተር ፍራንሲስካ ሲክላሪ እንደሚሉት ሰዎች ህልማቸውን በደንብ ከማያስታውሱበት ምክንያት አንደኛው በፍጥነት እንቅልፍ ወስዷቸው ሲነቁም በፍጥነት ስለሆነ ነው።

Image copyright Emanuel Lafront

የዘርፉ ባለሙያዎች ደረስንበት እንደሚሉት እንቅልፍ ሲወስደን መቆጣጠር የምንችል ቢሆንና ቀስ በቀስ ወደህልም መግባት ብንለማመድ ምናልባት የማስታወስ አቅማችን ከፍ ሊል ይችላል። ከእንቅልፍ ስንነቃም በህልማችን ደንግጠን አልያም ድምጽ ሰምተን በፍጥነት ባንነሳ ኖሮ የማስታወስ እድላችን ይጨምራል።

ህልማችንን ማስታወስ እንችላለን?

እንደ የእንቅልፍና የስነአእምሮ ጥናት ባለሙያዎች ግኝት ከሆነ ህልማችንን መቆጣጠር እጅግ ከባድ ቢሆንም በጥቂቱ እንኳን ለማስታወስ የሚረዱ ነጥቦችን ለይተዋል። በመጀመሪያ ሁሉም ሰው ሲተኛ የተለያየ አይነት ዓለም ውስጥ ስለሚገባ ለሁሉም ሰው ላይሰሩ እንደሚችሉ ከግምት ውስጥ ማስገባት ያስፈልጋል።

• ልክ ከእንቅልፋችን ስንነሳ በፍጥነት ከአልጋ ወርዶ ወደ ተለመደው ኑሮ መመለስ ህልማችንን ለማስታወስ ምንም አይረዳም። ስለዚህ ከእንቅልፍ ሲነቁ ትንሽ ጊዜ አልጋ ላይ ጋደም ብሎ ለማስታወስ መሞከርና ያስታወስነውን ትንሽ ነገር ቀኑን ሙሉ ማብሰልሰል ጠቃሚ ነው። ምክንያቱም ትንሿን ነገር ስናስታውስ ወደ ትልቁና ዋናው ህልማችን ሊወስደን ይችላል።

• በብዛት ውሃ ጠጥቶ መተኛም በህልማችን ያየናቸውን ነገሮች ለማስታወስ ይረዳል። ቢቻል ሶስት ብርጭቆ ውሃ መጠጣት ጠቃሚ ነው።