ጎንደር ዩኒቨርሲቲ፡ የ6ኛ ዓመት እጩ ሐኪሞች ግቢውን ለቅቀው ወጡ

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ዋና በር Image copyright Gonder University 2010 Batch FB

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ እጩ ሐኪሞች በተደጋጋሚ ያቀረቡት ጥያቄ ባለመመለሱ ያደረጉትን የሥራ ማቆም አድማ ተከትሎ ከዩኒቨርሲቲው አስተዳዳር ጋር ባለመስማማታቸው ግቢውን ለቀው እንደወጡ ለቢቢሲ ገልፀዋል።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው እጩ ሐኪሞች በትናንትናው እለት ግቢውን ለቅቀው የወጡት 250 እንደሚሆኑ ተናግረዋል።

እጩ ሐኪሞቹ ለሰባት ወራት ያህል ይመለሳሉ እየተባሉ ያልተመለሱ ጥያቄዎች በመኖራቸው ግቢውን ለቀው ለመውጣት መወሰናቸውን ተናግረዋል።

"ሀኪሙ ትግሉን አቀጣጠለው እንጂ የሚታገለው ለታካሚው ነው"

እጩ ሐኪም ታሪኩ ወርቁ ከጥያቄዎቻቸው መካከል የሕክምና ግብዓት አለመኖርና ለመስራት ምቹ አለመሆኑ ማኅበረሰቡ ለሐኪም ያለው አመለካከት የተዛባ እንዲሆን ምክንያት ሆኗል የሚል ነው።

"ለቀዶ ሕክምና እንኳን ጓንት የምንገዛው ከመድሃኒት ቤቶች ነው" የሚለው እጩ ሐኪሙ ሕክምና የራሱ የሆነ ሥርዓተ ትምህርት ቢኖረውም ከሥርዓተ ትምህርቱ ውጭ እየሰሩ መሆናቸው ሌላኛው ቅሬታቸው እንደሆነ ይገልፃል።

ሥርዓተ ትምህርቱ ላይ የተቀመጠውን ለመተግበር የሚያስችል ሁኔታ ባለመኖሩም ብቃታቸው እየወረደ መምጣቱንም ያክላል።

"ሥርዓተ ትምህርቱ ብዙ ያልተባባሱና ለሞት የማይዳርጉ ቀዶ ሕክምናዎችን እንድናደርግ የሚያዝ ቢሆንም ያንን ለመስራት ዕድሉን እያገኘን አይደለም፤ በሙያ የእኛ ያልሆኑ ሥራዎች እየሰራን ነው" በማለት ምሳሌ ያጣቅሳል። ይህንንም 'ዘመናዊ ባርነት' የሚል ስያሜ እንደሰጡት ይናገራል።

«በስልክዎ ታካሚና አካሚ እናገናኛለን» ሥራ ፈጣሪው ወጣት

ሙሉ ሕይወታቸውን ለትምህርት የሰጡት ማንኛውም ያልተማረ ሰው ሊሰራ የሚችለውን ለመስራት አለመሆኑንም ይናገራል።

ለ36 ሰዓታት እንደሚሰሩ የሚናገረው ሐኪሙ አብዛኛዎቹ የመንግሥት ሆስፒታሎች ማረፊያ ክፍል ስለሌላቸው ላለፉት ሰባት ወራት በዚህ ሁኔታ ሲሰሩ እንደነበር ያስታውሳል።

ይሁን እንጂ ዩኒቨርሲቲው ቀላል ሥራዎችን የሚሰሩ ሰዎችን በመቅጠር፣ ማረፊያ ቤቶችን በማዘጋጀት፣ እንዲሁም የተወሰኑ ግብዓቶችን በማሟላት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ጽ/ቤት የሥራ ማቆም አድማ ተገቢ እንዳልሆነ በደብዳቤ እንደገለፀላቸው ይናገራል።

ነገር ግን ሌሎች ከክፍያ ጋር የተያያዙ ጥያቄዎቻቸው ሊመለሱላቸው ባለመቻሉ ግቢውን ለቀው ለመውጣት እንደወሰኑ ለቢቢሲ ተናግሯል።

የታሪኩን ሃሳብ የምትጋራው ሌላኛዋ እጩ ሐኪም ፍሬሕይወት አለሙ በሁለት ሳምንታት ጊዜ ውስጥ መልስ እንደሚሰጧቸው ቢነገራቸውም መልስ አለማግኘታቸውን ትናገራለች።

በዚህም ምክንያት የሥራ ማቆም አድማ አድርገዋል። የሚመለከተው አካል ጥያቄዎችን ለመመለስ ድርድር የጀመረ ቢሆንም ባለመሳካቱ እንዲወጡ የሚያዝ ደብዳቤ እንደተለጠፈ ገልፃለች።

የ'ሰከረ' አዋላጅ ሐኪም እናትና ልጅን ገደለ

ስለ ጉዳዩ የጠየቅናቸው የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ወ/ሮ ይዳኙ ማንደፍሮ ሃገራዊ በሆኑ ጉዳዮች ሐኪሞቹ አስር የሚሆኑ የጥቅማጥቅም ጥያቄዎች ያቀረቡ መሆናቸውን ያስታውሳሉ።

እርሳቸው እንደሚሉት ዩኒቨርሲቲው በፌደራል መመለስ የሚገባውን ለሚመለከተው ያስተላለፈ ሲሆን ዩኒቨርሲቲው መመለስ በሚገባው ጉዳዮች ላይ የተለያዩ ኃላፊዎች በተገኙበት ውይይት ተደርጓል።

በጊዜው ጥያቄያቸውን ተቀብለው የሥራና ትምህርት ማቆም አድማ ማድረግ እንደሌለባቸው ተነጋግረው የነበረ ቢሆንም ሐኪሞቹ ወደ ሥራ ማቆም አድማ ገብተዋል።

በመሆኑም የዩኒቨርሲቲው ኃላፊዎች በተገኙበት በድጋሚ ውይይት ተደርጎ እንዲመለሱ የሚያሳስብ ማስታወቂያ ሦስት ጊዜ አውጥተው ሐኪሞቹ ባለመመለሳቸው ዩኒቨርሲቲው አስተዳዳደራዊ እርምጃ ሊወስድ ችሏል ብለዋል- ወ/ሮ ይዳኙ።

ከዚህም በኋላ የዩኒቨርሲቲው ምክር ቤት በድጋሚ ወደ ሥራቸው እንዲመለሱ ጥሪ በማቅረብ ይህንን የማያደርግ ተማሪ ለአንድ ዓመት ያህል እንደሚታገድ የሚገልፅ ማስታወቂያ አውጥቷል ብለዋል።

ወ/ሮ ይዳኙ አክለውም ትምህርታቸውንና ሥራቸውን እንዲቀጥሉ ለማድረግ ዩኒቨርሲቲው የተለያዩ ዘዴዎችን ቢጠቀምም ሐኪሞቹ ወደ ሥራ አለመግባታቸውን ይናገራሉ። በዚህ ምክንያትም ዩኒቨርሲቲው አስተዳደራዊ እርምጃ እንደወሰደባቸው ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

ተያያዥ ርዕሶች

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ