ማሚቱ፡ ፊደል ያልቆጠሩት ኢትዮጵያዊት የቀዶ ህክምና ባለሙያ

ማሚቱ ጋሼ

ማሚቱ ትዳር የመሰረተችው በ14 ዓመቷ ነበር። ከዚያ በፊት ቤተሰቦቿን በሥራ የምትረዳ፣ ከእኩዮቿ ጋር የምትጫወት ታዳጊ ነበረች። ትዳር መስርታ ሁለት ዓመት ከቆየች በኋላ ግን ያልጠበቀችው ሆነ።

ትዳሯን ስትመሰርት በሀገሩ ባህል መሰረት ወደ ቤተሰብ ሽማግሌ ተልኮ የወጉ ሁሉ ተሟልቶ ነው። ያኔ ከተማ ምንድን ነው የሚለውን እንኳ አስባው አታውቅም።

ህልሟ የነበረው ወልጄ ከብጄ እቀመጣለሁ የሚል ብቻ ነበር። ማሚቱ እንደምትለው በወቅቱ እድሜው 25 የሚገመት ወጣት ስታገባ ትዳሯ ሁሉ ነገር የሞላው ነበር፤ ከልጅ በስተቀር።

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ እጩ ሐኪሞች ግቢውን ለቅቀው ወጡ

ለወሲብ ባርነት ወደ ቻይና የሚወሰዱት ሴቶች

ባሏም ደግና አዛኝ፤ ሁሌም እርሷን ለመርዳት ወደኋላ እንደማይል ትናገራለች። በትዳር ሁለት ዓመት ከቆዩ በኋላ የማሚቱ ህልም እውን የሚሆንበት አጋጣሚ ተፈጠረ፤ ፀነሰች።

እርሷም ለልጇ መታቀፊያ ልብስ ገዝታ መጠባበቅ ጀመረች። የስምንት ወር ነፍሰጡር ሳለች አዲስ አበባ ትኖር የነበረች ታናሽ እህቷ ልትጠይቃት መምጣቷን ታስታውሳለች። ከተማን እህቷ ከምታወራላት ውጪ አታውቀውም።

የአራት ቀን ምጥ

ምጧ ሲፋፋም ወዳጅ ዘመድ ተሰብስቦ 'ማርያም ማርያም' ቢል ሕፃኑ ግን ሊወለድ አልቻለም።

አንድ ቀን አለፈ መሸ፤ ነጋ ሁለተኛም ቀን ሆነ። ማሚቱ በላብ ተነክራ ጥርሷን ነክሳ አማጠች፤ ምንም የለም። አራት ቀን ሙሉ እንዳማጠች የምትናገረው ማሚቱ በአራተኛው ቀን ራሷን ሳተች።

ስትነቃ ዘመድ ጎረቤቱ ከቧታል። ከሄደችበት ሰመመን ስትነቃ ከበው በጭንቀት ሲያይዋት የነበሩ ሰዎችን የተፈጠረውን ጠየቀቻቸው። 'ልጄ' አለች በደከመ ድምፅ፤ ልጇ ሞቶ ስለነበር ወጌሻ ተጠርቶ ተጎትቶ እንደወጣ ነገሯት። ለማልቀስ አቅም አጣች፤ ሐዘን ልቧን ሰበረው።

በኋላ ግን ሌላ ችግር በጤናዋ ላይ አስተዋለች፤ ሽንቷንና ሰገራዋን መቆጣጠር አለመቻሏን።

ሰማይ ላይ ወልዳ አሥመራ የምትታረሰው ኢትዮጵያዊት

በፆም ወቅት ሰውነታችን ውስጥ ምን ይካሄዳል?

ከቀን ቀን ይሻልሻል እየተባለች እናቷና እህቶቿ እያገላበጡ፣ እያጠቡ ተንከባከቧት ለውጥ የለም።

እኔም ለውጥ ይኖራል ብዬ ተስፋ እያደረኩ ነበር የምትለው ማሚቱ ለውጥ ስታጣ ተስፋ ቆረጠች። ራሷንም ለማጥፋት ትፈልግ እንደነበር ትናገራለች።

"ሰዎች ሲወልዱ አንደዚህ አይነት ነገሮች አይደርስባቸውም። ልጅ ብሆንም፣ አያለሁ እሰማለሁ። እንዴት እንዲህ አይነት ነገር እኔ ላይ ሊደርስ ቻለ?" በሚል አዘነች።

በአካባቢዋ ያሉ ሰዎች በተኛችበት "ጠገግ አልጋ" ላይ ሆና ሲመለከቷት ሳይሻላት ሲቀር ደሴ እንውሰዳት አሉ። ማንም ስለበሽታዋ ምንነት አያውቅም። የተኛችበት ክፍል በመጥፎ ጠረን ታውዶ ሲመለከቱ ማስታገሻ እንኳን እንድታገኝ በሚል ነበር ሀሳቡን ያቀረቡት።

ማሚቱ ሀፍረት ውጧት ነበር። እናቷ፣ እህቷና ወንድሞቿ ቢያገላብጧትም፣ ቢያፀዷት ቢያጥቧትም እርሷ ግን የወደፊት ሕይወቷ አሳሰባት። ከሰው ተራ እንደጎደለች ተሰማት፤ መብላትና መጠጣቴን ማቆም አለብኝ ብላ እንዳሰበች ትናገራለች።

ያኔ ቤተሰቦቿን ወደ እህቴ፣ አዲስ አበባ ውሰዱኝ በማለት ጠየቀች።

ከዚህ በኋላ ነው በወሬ በወሬ አዲስ አበባ ሕክምና እንዳለ የሰሙት። ወዲያው አዲስ አበባ ያሉ ዘመዶች ይቆጠሩ ጀመር። የእህቷ የክርስትና እናትና እህቷ አዲስ አበባ እኖራሉ። ዘመድ አዝማድ ፈውስ እንድታገኝ ተረባረበ። ዘመድ ለመቼ ነው!

የእርሶ መሳሪያ ሚዲያ ፕሌይ ባክን ማጫወት ኣልተቻለም።
ሕይወት የሚለወጥበት የደስታ መንደር

አዲስ አበባ

የእህቷ ክርስትና እናት ይሰሩበት ወደነበረው ዘውዲቱ ሆስፒታል አመራች። ዘውዲቱ ለ15 ቀን ተኝታ የሕመም ማስታገሻ እየተሰጣት ቆየች።

ከዚያም የእህቷ ክርስትና እናት በወቅቱ ልዕልተ ፀሐይ ይባል ወደነበረው ሆስፒታል ሄደው ጠይቀው ወደዚያው ወሰዷት።

በሆስፒታሉ ደግሞ ዶ/ር ካትሪን ሐምሊንና ባለቤታቸው ዶ/ር ሬጅ ሐምሊን ለፌስቱላ ታማሚዎች ቀዶ ጥገና ይሰጣሉ።

ወደ ሆስፒታሉ ከደረሰች በኋላ አቀባበላቸው እና እንክብካቤያቸው ራሱ በሽታዋን እንድትረሳ እንዳደረጋት ታስታውሳለች።

ሆስፒታሉ ስትደርስ በሆስፒታሉ አስር የሚሆኑ ሴቶች እንደነበሩ እና የእርሷ አይነት ሕመም ታምመው እያገገሙ መሆናቸውን ሲነግሯት ፈውስ ተሰማት። ሌላ ክፍል ታመው የታከሙ እና እያገገሙ ያሉ ሴቶችም ወደ እርሷ እየመጡ መዳን እንደሚቻል ይነግሯት ጀመር።

የተወሰኑ ቀናት ተኝታ መጠንከር ስትጀምር ቀዶ ህክምና ተደርጎላት ተሻላት።

"እኔ ሞቴን ተመኘሁ ፈጣሪ ግን ረዥም እድሜን ሰጠኝ" የምትለው ማሚቱ ታማሚዎች እየታከሙ ወደ መጡበት አካባቢ ሲሄዱ እና ስለሆስፒታሉ ሲናገሩ በርካታ ታካሚዎች መምጣታቸውን ትናገራለች።

ማሚቱ ሲሻላት ለእርሷ ይደረግ የነበረውን እንክብካቤ ለሌሎች ማድረግ ጀመረች።

"የሌሎች ታካሚዎችን አልጋ በማንጠፍ ነው የጀመርኩት" የምትለው ማሚቱ ከዳነች በኋላ ወደ ትውልድ ቀዬዋ ለመመለስ አላሰበችም።

ቤተሰቦቼን በማንኛውም ጊዜ ሄጄ መጎብኘት እነርሱም መጥተው ሊጎበኙን ይችላሉ እዚህ ብቆይ ግን እንደኔው ታማሚ የሆኑትን ብረዳ ብላ ወሰነች።

ባለቤቷ ለህክምና ሁለት ዓመት በቆየችበት ጊዜ መጥቶ ይጎበኛት ነበር፤ እርሷ በደንብ እስኪሻላት እንደምትቆይ ገልጣ እርሱ የራሱን ሕይወት እንዲመራ ነገረችው።

ጉዞ ወደ ቀዶ ህክምና ባለሙያነት

ከዚህ በፊት ታካሚዎቹን ትረዳ የነበረችው ጓደኛዋ ለእረፍት ስትሄድ እርሷን ተክታ መስራት ጀመረች። መርዳት ጀምራ ስታየው እኔ እርዳታ አግኝቼ ሌሎችን ብረዳ ደስተኛ ነኝ በሚል እዚያ ቆይታ መስራት መጀመሯን ትናገራች።

በኋላም እረፍት የሄደችው ሰራተኛ ስትመለስ እርሷ ወደ ማገገሚያ ክፍሏ ተመለሰች። ይኼኔ ዶ/ር ሬጅ ሐምሊን የት ሄደች? ብለው በመጠየቅ እንዳስመጧት ታስታውሳለች።

ዶ/ር ሬጅ ሐምሊን ኦፕራሲዮን ሲሰሩ እንድትመለከት ያደርጓት ነበር። የቀዶ ጥገና ልብሷን ለብሳ ከስር ስር እየተከተለች ሙያቸውን እንድትመለከት በማድረግ አነስተኛ ቀዶ ጥገናዎችን እንድትሰራ እድል ይሰጧት ጀመር።

"እነርሱ ሰርተው ያጠናቀቁትን ቀዶ ህክምና እንድጨርስ እንዲሁም ቀለል ያሉ ቀዶ ህክምናዎችን እነርሱ ባሉበት እንዳከናውን ያደርጉኝ ነበር።"

አዲስ ሆስፒታል ገንብተው ወደዚያ ሲዘዋወሩም ይህንን ተግባር ቀጠሉበት። ዶ/ር ሬጅ ሐምሊንን 'አባዬ' ካትሪን ሐምሊንን ደግሞ 'እማዬ' የምትለው ማሚቱ ሥራዬን በጣም ነው የምወደው ትላለች።

"እንደእኔ የተሰቃዩትን ከዚያ ስቃያቸው መፈወስ ደስታ ይሰጠኛል።"

ከተማ የማታውቀው፣ ሆስፒታል፣ መድሀኒት በቅጡ የማትረዳ የነበረችው ማሚቱ ለፌስቱላ ታማሚዎች የተሳካ ቀዶ ጥገና ብቻዋን ማድረግ ጀመረች።

"ለማከምም የበቃሁት በእነርሱ ተይዤ ነው፣ እንግሊዝኛ ብናገር ከእነርሱ የለመድኩትን ነው። አማርኛ ማንበብ እና መፃፍ ያስተማሩኝ እዚህ ግቢ ውስጥ ነው።"

ማሚቱ ለትምህርት ወደ ሆስፒታሉ የሚመጡትን የሕክምና ተማሪዎችንም ትረዳለች።

ለም አቀፍ እውቅና

አንድ ሰንበት ከእንግሊዝ ሮያል ኮሌጅ የመጡ የቀዶ ህክምና ባለሙያዎች ማሚቱን አገኟት። በወቅቱ እነሐምሊን በግቢው አልነበሩም። በዚያ ሰንበት የቀዶ ህክምና ሥራውን የምትመራው ደግሞ ማሚቱ ነበረች።

ይህንን ድርጊቷን በድጋሚ መጥተው በዶ/ር ሬጅ ሐምሊን ረዳትነት ሙሉ ቀዶ ጥገና ስታከናውን ሲያይዋት ተደነቁ፤ ከዚያም እውቅናን ሰጧት።

በዚህ ተግባሯም ዶ/ር ሬጅ ሐምሊንም እንደኮሩባት የምትናገረው ማሚቱ "እኔም በሥራዬ ኮራሁ" ትላለች።

እስካሁን ለምን ያህል ሰዎች ቀዶ ህክምና እንዳደረገች አታውቅም። ነገር ግን በርካታ ሐኪሞችን መርዳቷን በርካታ ታማሚዎችን ማከሟን ታስታውሳለች። ከእንግሊዝ ሮያል ኮሌጅ እውቅና በኋላ ወደ አሜሪካ ተጠርታ ከኢትዮጵያዊያንም እውቅና ተሰጥቷታል።

ማሚቱ የምትሰራበት ሆስፒታልን ለየት የሚያደርገው በርካታ ሰራተኞች በፌስቱላ ታመው የነበሩና ታክመው የዳኑ መሆናቸው ነው። እነዚህ ሴቶች ከነርሶቹ ስር በመሆን የሚረዱ ሲሆን በሽታውን ስለሚያውቁት ለሕመምተኞቹ ብርታት ይሆኗቸዋል። ይህም በማስተማ ሂደቱም ውስጥ በጎ አስተዋፅኦ እንዳለው ይናገራሉ።

ማሚቱ "ለእኔ የተደረገውን ያህል ለሌሎች በበቂ ሁኔታ ያደረኩ አይመስለኝም" ስትልም ዛሬም በርካቶችን የመርዳት ፍላጎቷን ታስረዳለች።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ