አልጄሪያና አርጀንቲና ከወባ ነጻ ተባሉ

የወባ ትንኝ Image copyright Getty Images

የዓለም ጤና ድርጅት አልጄሪያና አርጀንቲን ከወባ በሽታ ሙሉ በሙሉ ነጻ መሆናቸውን አረጋገጠ። ከወባ ነጻ የእውቅና (የምስክር) ወረቀት ሃገራት ማግኘት የሚችሉት ለተከታታይ ሦስት ዓመታት በሽታው ከሰው ወደ ሰው እንዳልተላለፈ ሲረጋገጥ ብቻ ነው።

በወባ ትንኝ ንክሻ የሚተላለፈው በሽታው እስካሁን ድረስ በዓለማችን ቀዳሚው ገዳይ በሽታ ነው። በየዓመቱ 219 ሚሊየን ሰዎች በወባ በሽታ የሚያዙ ሲሆን እስከ 400 ሺህ የሚደርሱት ሕይወታቸው ያልፋል። ከሟቾች 60 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ህጻናት ናቸው።

የወባ ትንኝ አደገኛ የሆነችው በሂደት ነው

የወባ በሽታን በትንፋሽ ማወቅ ተቻለ

በአውሮፓውያኑ 1973 የምስክር ወረቀት ካገኘችው ሞሪሽየስ በመቀጠል አልጄሪያ ከወባ ነጻ የተባለች ሁለተኛዋ አፍሪካዊ ሃገር መሆን ችላለች። አርጀንቲና ደግሞ ከፓራጓይ በመቀጠል ከ45 ዓመት በኋላ ከወባ ነጻ የሆነች የደቡብ አሜሪካ ሃገር ሆናለች።

አልጄሪያ ከወባ ነጻ ሆኛለሁ ብላ በአውሮፓውያኑ 2013 ለዓለም ጤና ድርጅት አስታውቀ የነበረ ሲሆን በያዝነው ዓመት እውቅናውን አግኝታለች።

በአልጄሪያና አርጀንቲና የወባ በሽታ ለብዙ መቶ ዓመታት ዜጎችን ሲገድል የነበረ በሽታ ነው። ሙሉ በሙሉ በሽታውን ለማጥፋት ሃገራቱ መራር የሚባል ትግል ማድረጋቸውን አስታውቀዋል። በድንበር አካባቢዎችም የሰዎች እንቅስቃሴና በሽታውን ለመቆጣጠር በተደረገ ከፍተኛ ጥረት እንዲሁም በየጤና ኬላዎች በሚደረግ ነጻ የወባ ምርመራና ህክምና አማካይነት ግባቸውን ሊያሳኩ እንደቻሉ የዓለም ጤና ድርጅት አስታውቋል።

ሁለቱም ሃገራት ወባን ለማጥፋት ባሳዩት ቆራጥነትና የመከላከል ብቃት የምስክር ወረቀቱ ይገባቸዋል ብለዋል- የዓለም ጤና ድርጀት ዳይሬክተር ጄነራል ዶክተር ቴዎድሮስ አድሃኖም።

''የእነሱ ስኬት ወባን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ማጥፋት በርትተው እየሰሩ ላሉ ብዙ ሃገራት ትልቅ ትምህርት ነው።'' ብለዋል።

በቴክኖሎጂ ኢ-ፍትሐዊነትን የምትታገለው ኢትዮጵያዊት

ስለ እንቅልፍ የተሳሳቱ አመለካከቶች

በአልጄሪያ በየዓመቱ እስከ 80 ሺህ የሚደርሱ ሰዎች በወባ በሽታ የሚሞቱ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት በየመንደሮቹ ተሰማርተው የሚገኙትና ተገቢውን ስልጠና ያገኙት የጤና ባለሙያዎች ለዚህ ስኬት እንዳበቋት ይታመናል።

ለሁለቱም ሃገራት ከወባ ነጻ መሆናቸውን የሚያረጋግጠው የምስክር ወረቀት በ72ኛው የዓለም ጤና ጉባኤ ላይ በዶክተር ቴዎድሮስ አድሃኖም አማካይነት የሚበረከትላቸው ይሆናል።

እስካሁን በመላው ዓለም 38 ሃገራት ከወባ ነጻ መሆናቸውን የዓለም ጤና ድርጅት አረጋግጧል።