ኮንዶም መጠቀም እያቆምን ይሆን?

የተለያዩ የኮንዶም አይነቶች Image copyright iStock

ሄይሊ የ24 ዓመት ወጣት ነች። ውጪ ከምታሳልፋቸው ምሽቶች በአንዱ ወደ መጠጥ ቤት ጎራ ብላ ነበር። ሌሊቱ ሊጋመስ ጥቂት ሲቀረው ከዚህ በፊት ትምህርት ቤት አብሯት የተማረ ሰው በድንገት አገኘች።

አብረው ሲጠጡ አምሽተው ተያይዘው ወደቤት ገቡ። ያለምንም መከላከያም ግብረ ስጋ ግንኙነት ፈጸሙ። ጠዋት ከእንቅልፌ ስነሳ ሰክሬ ባደረግኩት ነገር ባልደሰትም ይበልጥ ያሳሰበኝ ግን ያለኮንዶም ግብረ ስጋ ግንኙነት መፈጸሜ ነው ትላለች።

ሄይሊ እንደምትለው፤ በግብረ ስጋ ግንኙት ወቅት ኮንዶም ስለመጠቀም ለማውራት ምቾት አይሰጣትም። ''አንዳንዴም መከላከያ ስለመጠቀም ባወራ ጓደኛዬ ምን ይለኛል? ብዬ እተወዋለው።''

ስለኤች አይ ቪ /ኤድስ የሚነገሩ 8 የተሳሳቱ አመለካከቶች

የሚያስወርዱ ሴቶች ቁጥር ከሚወልዱ ሴቶች የሚበልጥባት ሀገር

የእንግሊዙ የማኅበረሰብ ጤና ቢሮ በቅርቡ በሠራው ጥናት መሰረት፤ እድሜያቸው ከ16 እስከ 24 የሆኑ ወጣቶች አብዛኛዎቹ ከፍቅር ጓደኛቸው ጋር ያለኮንዶም የግብረ ስጋ ግንኙነት መፈጸማቸውን ተናግረዋል። ከአስር ወጣቶች አንዱ ደግሞ እስከነጭራሹ ኮንዶም ተጠቅመው አያውቁም።

በአውሮፓውያኑ 2003 በተደረገ ጥናት መሰረት ግን እድሜያቸው ከ16 እስከ 24 ከሆኑ ወጣቶች መካከል 43 በመቶ የሚሆኑት ኮንዶም እንደሚጠቀሙ ተናግረው ነበር።

ከአስር ዓመት በኋላ ያሉትን ቁጥሮች ያመሳከሩት ባለሙያዎች እንግሊዝ ውስጥ ብቻ ኮንዶም የሚጠቀሙ ሰዎች ቁጥር 36 በመቶ ቀንሷል ብለዋል። አሜሪካ ውስጥ ኮንዶም ይጠቀሙ የነበሩ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ቁጥር 2007 ላይ ከነበረው 62 በመቶ፤ በ2017 ወደ 54 በመቶ ቀንሷል።

በዚሁ ጥናት ላይ እንደተጠቆመው፤ በግብረ ስጋ ግንኙት የሚተላለፉ በሽታዎች በብዛት የሚታዩት እድሜያቸው ከ16 እስከ 24 ዓመት ክልል ውስጥ ባሉ ወጣቶች መሆኑ ነገሮችን ይበልጥ አሳሳቢ አድርጓቸዋል።

እንግሊዝ ውስጥ እንደ ጨብጥና ቂጥኝ ያሉ በግብረ ስጋ ግንኙነት የሚተላለፉ በሽታዎች የተያዙ ወጣቶች ቁጥር 2017 ላይ 20 በመቶ ጨምሮ የነበረ ሲሆን፤ ዋነኛ የመተላለፊያ መንገዱ ያለመከላከያ የሚደረግ የግብረ ስጋ ግንኙነት ነው።

Image copyright BBC Three / iStock

የኮንዶም ተወዳጅነት የቀነሰበት ዋነኛ ምክንያት ተብሎ የሚገመተው እርግዝናን የሚከላከሉ የተለያዩ አይነት ዘመን አመጣሽ አማራጮች ቁጥር መጨመር ነው። እንግሊዝ ውስጥ የእርግዝና መከላከያ መድሃኒቶችን የሚገዙ ወጣት ሴቶች ቁጥር ከምን ጊዜውም በላይ ጨምሯል።

በ1950ዎቹ መተዋወቅ የጀመረው ኮንዶም ምንም አይነት ለውጥ ሳይደረግበት እስካሁን ድረስ አለ። ምናልባትም ከኮንዶም ጋር የተያያዙ ብዙ ለውጦች አለመኖራቸው ሰዎች በቀላሉ እንዲሰለቹትና ወደሌሎች አማራጮች እንዲሄዱ ሳያደርጋቸው እንዳልቀረ ይገመታል።

ቤት ሠራሽ ኮንዶሞች ለመጀመሪያ ጊዜ አገልግሎት ላይ መዋል የጀመሩት በጥንት ዘመን ሲሆን፤ የዛኔ የነበሩ ሰዎች የበግ አልያም የፍየል አንጀትና የሽንት ፊኛ ይጠቀሙ ነበር።

ከኤችአይቪ ጋር ተያይዘው የሚሠሩ ማስታወቂያዎችና መልእክቶች መቀነስ በራሱ ለኮንዶም ጥቅም ላይ አለመዋል የራሱን የሆነ አስተዋጽኦ አለው። በተለይ ደግሞ ባደጉት አገራት የኤችአይቪ ስርጭት እጅጉን የቀነሰና ጠፍቷል በሚባል ደረጃ መሆኑ በተለይ ወጣቶች ኮንዶም ለመጠቀም የሚያስገድዳቸው ነገር እንደሌለ እንዲያስቡ አድርጓቸዋል።

ወንዶች የማያወሯቸው አምስት አሳሳቢ ነገሮች

ኤምአርአይ ምንድነው?

ከነዚህ ነገሮች ሁሉ ወጣ ስንል ደግሞ ያልተፈለገ እርግዝና መረሳት የለበትም። ብዙ ወጣት ሴቶች በግብረ ስጋ ግንኙነት ከሚተላለፉ በሽታዎች ይልቅ ያልተፈለገ እርግዝናን ይፈራሉ። ኮንዶም መጠቀም ካለባቸውም እርግዝናን ለመላከል እንደሆነ እያሰቡ ነው የሚያደርጉት።

የሥነ ተዋልዶ ጤና ባለሙያ የሆኑት ፕሮፌሰር ሲንቲያ ግራሃም እንደሚሉት፤ በተለይ ደግሞ ወጣቶች ኮንዶም መጠቀም ከግብረ ስጋ ግንኙነት የሚገኘውን ደስታ ይቀንስብናል ብለው ያስባሉ።

አብዛኛዎቹ ወንዶች ደግሞ ኮንዶም ሲጠቀሙ ብልታቸው በተገቢው ሁኔታ እንደማይነቃቃላቸው ይናገራሉ። ፕሮፌሰር ሲንቲያ ግን ወጣም ወረደም ኮንዶም መጠቀምን የመሰለ ቀላልና ጠቃሚ አማራጭ የለም ብለው ያምናሉ።