ጌታባለው መኩሪያው፡ የብስክሌት ጀልባ የሠራው ወጣት

የብስክሌት ጀልባ

በውሃ ላይ የጀልባና የመርከብ ሽርሽር የተለመደ ነው፤ ኢትዮጵያዊው ወጣት ግን የጀልባ ቀዛፊ አሊያም የመርከብ ካፒቴን ሳያስፈልገን በራሳችን እጅ እየዘወርን፤ በእግራችን ፔዳሉን እየመታን ለምን አንንሸራሸርም ብሏል።

ጌታባለው መኩሪያው ይባላል። የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የሜካኒካል ምህንድስና የሦስተኛ ዓመት ተማሪ ነው። በቅርቡ በሞከረው የብስክሌት ጀልባ (Pedal Boat) በርካታ አድናቆቶች ተችረውታል።

በፀሐይ የሚሰራው የሕዝብ ማመላለሻ ጀልባ

አዲስ አበባ፡ የፈጠራ ማዕከል ለመሆን እየጣረች ያለች ከተማ

መኖሪያው ደግሞ የጣና በለስ የስኳር ፕሮጀክት በሚገኝበት አዊ ዞን ጃዊ ከተማ ነው። በከተማው መግቢያ አካባቢ ለሚገኘው የስኳር ፋብሪካ ታስቦ የተገነባ ሰፊ የሸንኮራ አገዳ እርሻ በአካባቢው አለ።

እርሻው ክረምት ክረምት በአካባቢው ከሚጥለው ዝናብ ውሃ የሚጠቀም ሲሆን በበጋ ወቅት ደግሞ ለዚሁ ሲባል ከተገነባው የመስኖ ግድብ ውሃ ያገኛል።

ጌታባለውን ጨምሮ የአካባቢው ልጆች ከአካባቢው ሙቀት ራሳቸውን ለማቀዝቀዝም ሆነ እንደ መዝናኛ ግድቡ ቦታ በመሄድ ይዋኛሉ።

"በዚህ ጊዜ ነው ለምን ጀልባ አልሠራም ብዬ ራሴን የጠየኩት" ሲል የብስክሌት ጀልባ ለመሥራት እንዴት እንዳሰበ ለቢቢሲ የገለጸው። ጌታ ባለው እንደሚለው መጀመሪያ ሊሠራ ያሰበው በብዙ ቦታዎች የሚገኘውንና የተለመደውን ባለመቅዘፊያ ጀልባ ነበር።

በኋላ ላይ ግን ሐሳቡን በመቀየር የብስክሌት ጀልባ የመሥራት ሃሳቡ ሚዛን ደፋበት።

"ቀስ በቀስ ነው ፔዳል የሚለው ሃሳብ የመጣልኝ"ይላል። ሆኖም የብስክሌት ጀልባውን ሠርቶ ለማጠናቀቅ ዓመታትን መጠበቅ ግድ ብሎታል።

"የብስክሌት ጀልባውን ለመሥራት ብዙ ጊዜ አይፈጅም" የሚለው ጌታባለው ወጪው ብዙ በመሆኑ ምክንያት ችግር እንዳጋጠመው ምክንያቱን ያስረዳል።

ይህንን ሁሉ ተቋቁሞ የብስክሌት ጀልባውን እውን ለማድረግ የተነሳው ጌታባለው መጀመሪያ ላይ ሙከራ ያደረገው እጅግ ብዙ ብረት እንዲኖረው አድርጎ ስለነበር ክብደቱ ከፍተኛ መሆኑ ለመንሳፈፍ አስቸጋሪ አድርጎበታል።

በዚህ ወቅት ነው አገልግሎት ከሰጡ እና ክብደት ከሌላቸው ዕቃዎች ጀልባውን መሥራት ጥሩ መፍትሔ መሆኑን በማመን በዚሁ መሠረት መሥራት የጀመረው።

ይህም ጀልባው በቀላሉ እንዲንሳፈፍ ከመርዳቱም በላይ በአነስተኛ ወጪ ሠርቶ ለማጠናቀቅም የሚያስችለው ሆኖ አግኝቶታል።

"ሙሉ ለመሉ ሠርቼ ያጠናቀቅኩት በቅርቡ ቢሆንም ስለ ጀልባው ግን ማሰብ የጀመርኩት ከሁለት ዓመታት በፊት ነው" ሲል ያስረዳል።

የብስክሌት ጀልባው አራት ቱቦዎች፤ አገልግሎት የሰጠ ብስክሌት እና የግራይንደር (የብረት መቁረጫ ማሽን) አናትን በዋናነት ተጠቅሞ ነው የተሠራው።

በፀሐይ የሚሰራው የሕዝብ ማመላለሻ ጀልባ

ቱቦዎች ጀልባው እንዲንሳፈፍ የሚረዱ ናቸው። ብስክሌቱ ደግሞ ለመቀመጫነት የሚያገለግል ሲሆን ጀልባውን ለማንቀሳቀስ እና መሪውን ተጠቅሞ ወደ ተፈለገው አቅጣጫ ለመጓዝ የሚያስችል ነው።

ከብስክሌቱ ፔዳል ጋር የሚገናኘው ተሽከርካሪ ደግሞ ውሃውን ወደኋላ በመግፋት ጀልባው ወደ ፊት እንዲንቀሳቀስ ያግዛል።

የብስክሌት ጀልባዎች ከቦታ ቦታ ለመንቀሳቀስ ከመርዳታቸውም በላይ እንደ አንድ የመዝናኛ መንገድ ጥቅም ላይ የሚውሉ እና አካላዊ እንቅስቃሴ ለማድረግም የሚያግዙ ናቸው።

እንደ ጌታባለው ከሆነ ሌሎች የብስክሌት ጀልባ ዓይነቶችን ከተለያዩ ድረ-ገጾች መመለከት ቢችልም የእሱ የብስክሌት ጀልባ በብዙ ምክንያት ይለያል ይላል።

"ብዙ ዓይነት የብስክሌት ጀልባዎች ቢኖሩም ይሄ በቀላሉ እና አገልግሎት ከሰጡ ዕቃዎች ቤት ውስጥ መሠራቱ ለየት ያደርገዋል" ሲል ምክንያቱን ነግሮናል።

ከዚህ በተጨማሪም በቀላሉ ተፈትቶ የሚገጣጠም ከመሆኑም በላይ ይዞ ለመንቀሳቀስም የሚያስችግር አይደለም።

የዕለት ከዕለት ኑሮን የሚለውጡ ፈጠራዎች

ጌታባለው የብስክሌት ጀልባውን ሠርቶ ሲያጠናቅቅ ጋራዥ ውስጥ ካገዙት ሰዎች ጋር በመሆን ነው የሞከሩት። ሥራውን በሚሠራበት ወቅት ከቤተሰቦቹ ውጭ ድጋፍ ያደረገለት አካል ባይኖርም ጋራዥ ውስጥ የሚሠሩ ጓደኞቹ ያደረጉለት ድጋፍንም ግን ሳያነሳ አያልፍም።

ይሁን እንጅ ስለ ብስክሌት ጀልባው በማህበራዊ ሚዲያ ብዙዎች ከተጋሩት በኋላ የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ባልደረቦች አናግረውት የነበር ቢሆንም ምንም ድጋፍ እንዳላደረጉለት ገልጿል።

"የፈጠራ ሥራው በብዙ መልኩ መሻሻል ይችላል" የሚለው ጌታባለው ተሻሽሎ በሞተር እንዲንቀሳቀስ ማድረግ እንደሚቻል ገልጾልናል።

በአካባቢው ያለው ውሃ ለመስኖ አገልግሎት ተብሎ የተሠራ በመሆኑ ለመዋኘትም ሆነ በጀልባ ለመዝናኛት አይፈቀድም። ጀልባ ለመጠቀም ሴፍቲ ጃኬት መጠቀምም ግዴታ ነው። ይህንን ለማግኘት ባህርዳር ድረስ ሄዶ ቢጠይቅም ሊያገኝ እንዳልቻለ ይናገራል።

ከጋና የፈጠራ ሥራዎች ጀርባ ያለው ሥራ ፈጣሪ

የግድቡ ውሃ ደግሞ አነስተኛ መሆኑ ሌላው ችግር ነው። ይህንን ከግምት ውስጥ በማስገባትም ጣና ሐይቅ ላይ አገልግሎት እንድትሰጥ የብስክሌት ጀልባዋን ወደ ባህርዳር ለመወሰድም አቅዶ ነበር።

ነገር ግን ባህርድዳር ውስጥ የሚያውቀው ሰው ባለመኖሩ ጀልባውን የሚያስቀምጥበት ቦታ ማጣቱን ጌታባለው ይገልጻል። እነዚህ ችግሮች ግን ተስፋ አላስቆረጡትም። ይህ የመጀመሪያው ፕሮጀክት ቢሆንም ሌሎች የሚያስባቸው ሥራዎችም አሉት።

"ብቻዬን መሥራት አልችልም፤ የሚያግዘኝ ተቋምም ሆነ ግለሰብ ሲኖር ነው ወደ ተግባር መግባት የምችለው" በማለት የሌሎች ተባባራ አካላት እርዳታ እንደሚያስፈልገው ያስረዳል።

በዚህም ምክንያት እንዳሰበው ሌሎች ዕቅዶቹን ወደ ሥራ ለማስገባት አልቻለም፤ ዋናው ምክንያቱ ደግሞ የኢኮኖሚ ችግር ነው።

"ተማሪ ነኝ፤ በኢኮኖሚ በኩል ተወስኜ ቆሜያለሁ፤ በብስክሌት ጀልባው ሠርቼ ገቢ ባገኝ ያሰብኩትን እሠራለሁ" ሲል በመጨረሻም ተስፋው ገልፆልናል።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ