ብሬግዚት፡ የቴሬሳ ሜይ ውድቀት ምክንያት

ጠቅላይ ሚንስትር ቴሬሳ ሜይ ከስልጣን እንደሚወርዱ ሲያሳውቁ Image copyright Getty Images

የእንግሊዝ የመጀመሪያ ሴት ጠቅላይ ሚንስትር ማርጋሬት ታቸር እና ሁለተኛዋ ሴት ጠቅላይ ሚንስትር ቴሬሳ ሜይን ምን ያመሳልላቸዋል? ቢባል መልሱ፤ "ሁለቱም እንግሊዝ ከአውሮፓ ጋር ያላትን ግንኙነት በማስመልከት ባላቸው አቋም ሳቢያ በወግ አጥባቂዎች ከስልጣን ወርደዋል" ይሆናል።

ቴሬሳ ሜይ እንደማርጋሬት ታቸር ለአገራቸው ባበረከቱት አስተዋጽኦ አይታወሱ ይሆናል። እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር 2016 ላይ ወደ ጠቅላይ ሚንስትር ቢሮ ሲያቀኑ የሰነቁት ተስፋ ይህ አልነበረም።

ህልማቸው የነበረው የተዘነጉ የአገሪቱን ክፍሎች ማስታወስ፣ ኢ-ፍትሀዊነትን መዋጋት ወዘተርፈ . . . ነበር። ነገር ግን የስልጣን ዘመናቸው በአንድ ጉዳይ ተዋጠ። ብሬግዚት በሚሉት ጉድ!

የብሬግዚት እቅድ በ432 የተቃውሞ ድምጽ ውድቅ ተደረገ

እንግሊዝ ከአውሮፓ ኅብረት የምትሰናበትበት ብሬግዚትን የተመለከተው ሕዝበ ውሳኔ የተወጠነው ከሳቸው በፊት ስልጣን ላይ በነበሩት ዴቪድ ካሜሩን ቢሆንም፤ ቴሬሳ ደግሞ ውሳኔው ተግባራዊ ለማድረግ ያልፈነቀሉት ድንጋይ የለም።

ቴሬሳ ከብራሰልስና ዌስትሚኒስተር የገጠማቸው ከፍተኛ ተቃውሞ ሳይበግራቸው ወደፊት ለመጓዝ ያሳዩት ቆራጥነት ተቺዎቻቸውን ሳይቀር አጃኢብ አስብሏል።

ቴሬሳ ሜይ በሶሪያ ላይ ስለሚወሰደው እርምጃ ለመምከር ምክር ቤቱን ጠሩ

ጠቅላይ ሚንስትሯ የሰላ ትችት እየተሰነዘረባቸው እንኳን ተስፋ የቆረጡ አይመስሉም ነበር። በተደጋጋሚ "የእንግሊዝ ሕዝብን ፍቃድ አስፈጽማለሁ" ሲሉ ይደመጡ ነበር።

የ2017ቱን ጠቅላላ ምረጫ ማሸነፍ ቢችሉም፤ ከምክር ቤቱ አባላት አብዛኞቹ አይደግፏቸውም ነበር። የቴሬሳ አለኝታ የነበረው 'ኖርዘርን አየርላንድስ ዴሞክራቲክ ዩኒየኒስት ፓርቲ' ነበር።

አብዛኞቹ የሕዝብ እንደራሴዎች ቴሬሳ ስልጣን ላይ እንዲቆዩ ይፈልጉ የነበረው የብሬግዚት እቅዳቸውን እስኪያሳኩ ብቻ ከመሆኑ ባሻገር፤ ቴሬሳም ከ2011 ምርጫ አስቀድመው ስልጣን እንደሚለቁ ቃል መግባታቸው ይታወሳል።

የመጨረሻው መስዋዕትነት

ቴሬሳ ሜይ ስልጣን መልቀቃቸውን በፓርቲያቸው ውስጥ ላሉት ተቺዎቻቸው ከአውሮፓ ኅብረት መውጣትን ደግፈው ድምፅ የሚሰጡ ከሆነ እንደ መጨረሻ መስዋዕት እንደሚያቀረቡላቸው ተናግረው ነበር። ነገር ግን ረቂቅ ስምምነቱ በፓርላማው ተቀባይነት አግኝቶ እንዲያልፍ ለማድረግ ሳይችሉ ቀርተዋል።

ባለፈው ጥር ወር ላይ ነበር ፓርላማው በታሪክ በእንግሊዝ መንግሥት ላይ በቀረበ ከፍተኛ ተቃውሞ ያቀረቡትን የስምምነት ሃሳብ ውድቅ የተደረገባቸው። ቴሬሳ ሜይ የፓርላማቸውን ተቀባይነት ለማግኘት ሁለት ተጨማሪ ጥረቶችንም አድርገው ነበር።

ነገር ግን በሁለቱም ያሰቡትን ይሁንታ ሳያገኙ ቀርተዋል። ሜይ ከአውሮፓ ኅብረት ለመውጣት በሚያደርጉት ጥረት ወቅት ከተቃዋሚዎቻቸው ጋር ለመደራደር ሁሉ ሞክረው ነበር። በዚህም የሌበር ፓርቲው መሪ ጄሬሚ ኮርቢንን አነጋግረዋል።

ቴሬዛ ሜይ ሥልጣናቸውን እንዳያጡ ተሰግቷል

ለስድስት ሳምንታት የተደረገው ድርድር ካለስምምነት በመጠናቀቁ በርካታ የፓርላማ አባላትን አስከፍቷል። ተጨማሪ ሽንፈት የገጠማቸው ደግሞ ቀደም ሲል የሚታሰብ አይደለም ብለው የተቃወሙትን ዩናይትድ ኪንግደም በአውሮፓ ፓርላማ ውስጥ እንድትሳተፍ መስማማታቸው ነበር።

በርካታ የፓርላማ አባላትም ሜይ የስምምነቶች አደናቃፊ ናቸው በማለት ጆሮ ነስተዋቸዋል። በዚህም "እወደዋለሁ" በሚሉት የጠቅላይ ሚኒስትርነት ሥራ ለመቀጠል እንደማይችሉ ዛሬ ይፋ አድርገዋል። ይህንንም የወግ አጥባቂውን ፓርቲያቸው መሪነትንና የጠቅላይ ሚኒስትረነት ቦታቸውን እንደሚለቁ ውሳኔያቸውን ሲያሳውቁ ስሜታዊ ሆነው ድምጻቸው ይሰባበር ነበር።

መንበራቸውንም ከሁለት ሳምንት በኋላ በይፋ ሲለቁ ፓርቲያቸው ቀጣይ የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ማን ሊሆን እንደሚችል ይወስናል።

Image copyright AFP/Getty Images

ቴሬሳ ሜይ ማናቸው?

የ62 ዓመቷ ቴሬሳ ሜይ ከ1997 ጀምሮ የሜይድንሄድ የሕዝብ እንደራሴ ነበሩ። የአገር ውስጥ ደህንነት ሥራቸውን ተከትሎ በ2016 ላይ ጠቅላይ ሚንስትር ሆነው ተመርጠዋል።

እንግሊዝ፦ 'ከኢራን ጎን ነኝ'

ትምህርታቸውን የተከታተሉት 'ዌልዚ ፓርክ ኮምፕሬንሲቭ' በተባለ የመንግሥት ትምህርት ቤት ሲሆን፤ ለተወሰነ ጊዜ ኦክስፎርድ ውስጥ የሚገኝ 'ሴንት ሂውስ ኮሌጅ' የተባለ ትምህርት ቤት ተምረዋል።

ምግብ ማብሰል የሚወዱት ቴሬሳ፤ ከ150 በላይ የምግብ አሠራር መጻሕፍት እንዳላቸው ይናገራሉ። ለበዓል ከባለቤታቸው ፊሊፕ ሜይ ጋር ተራራ በማውጣት ማሳለፍ ያዘወትራሉ። ቴሬሳ ፋሽን እንደሚወዱ ሲናገሩም ተደምጠዋል።