የምርምርና ስርፀት ሥራዎች ለሕዝቡ ምን ይጠቅማሉ?

ፋብሪካ Image copyright MICHELE CATTANI

አሁን ዓለም ላይ ካለው የቴክኖሎጂ እድገት አንጻር ለአንዲት ሃገር ቀጣይነት ያለው ኢኮኖሚያዊ እድገት የምርምርና ስርፀት ሥራዎች እጅግ አስፈላጊ ናቸው። የአንዲትን ሃገር የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ፈጠራ ደረጃ ለማወቅም ጥቅም ላይ ይውላል።

ኢትዮጵያም እነዚህን ነገሮች ከግምት ውስጥ በማስገባትና በዘርፉ የሚታየውን ክፍተት ለመሙላት ባለፉት ዓመታት የተለያዩ ጥናትና ምርምሮችን አድርጋለች።

ነገር ግን አብዛኛዎቹ ጥናቶች የዓለም አቀፍ መስፈርቶችን አሟልተው አይደለም የተሠሩት። በቅርቡ የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ኢንስቲቲዩት በሠራው አዲስ ጥናት መሠረት ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የምርምርና ስርፀት ደረጃ ዝቅተኛ መሆኑን ጠቁሟል።

ከፀሐይ ኃይል ኤሌክትሪክ ለማመንጨት የሚጥሩ ወንድማማቾች

የብስክሌት ጀልባ የሠራው ወጣት

የኢንስቲቲዩቱ ዳይሬክተር ጀኔራል የሆኑት አቶ ሳንዱካን ደበበ እንደሚሉት ከዚህ በፊት በአውሮፓውያኑ 2010፣ 2013 እና 2016 ጥናቶች ተሠርተው የነበረ ቢሆንም የተሟላ መረጃ ማቅረብ አልቻሉም ነበር።

እአአ 2016 ላይ በተሠራው ጥናት መሠረት ኢትዮጵያ ከአጠቃላይ ሃገራዊ ምርቷ ለምርምርና ሥርፀት 5.05 ቢሊየን ብር መድባ እንደነበር ያሳያል። ከ66 በመቶ በላይ የሚሆነው ወጪ የተሸፈነው ደግሞ ከመንግሥት ካዝና ነው።

ጥናቱ እንደሚጠቁመው በኢትዮጵያ ያሉ የግል ድርጅቶችና የንግድ ተቋማት ለምርምርና ሥርፀት ያወጡት ወጪ ከአጠቃላይ ሃገራዊ ምርቱ ጋር ሲነጻጸር ድርሻቸው አንድ በመቶ ብቻ ሲሆን አብዛኛዎቹ ድርጅቶች ምርምርና ስርፀትን የሚከታተል ባለሙያ እንኳን የላቸውም።

እንደ ደቡብ አፍሪካ ባሉ ሃገራት ግን የምርምርና ስርፀት ሥራዎች 50 በመቶ አንዳንዴም ከዚያ በላይ የሚሆነውን ወጪ የሚሸፍኑት የግል ተቋማትና የንግድ ድርጅቶች ናቸው።

የጥናቱ ግኝቶች ምንድናቸው?

በኢትዮጵያ የሚገኙ 359 ድርጅቶች በጥናቱ የተካተቱ ሲሆን 160 የመንግሥት ድርጅቶች፣ 140 ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት እንዲሁም 32 የግል ድርጅቶች ተሳትፈውበታል።

የአፍሪካ ሃገራት ከአጠቃላይ ሃገራዊ ምርታቸው 1 በመቶ የሚሆነውን በምርምርና ስርፀት ሥራዎች ላይ ለማዋል የተስማሙ ሲሆን ኢትዮጵያም ይህንኑ ስምምነት ፈርማለች።

ኢትዮጵያ በስምምነቱ ላይ ከተቀመጠው ቁጥር ባነሰ መልኩ ከሃገራዊ ምርቷ 0.2 በመቶ ብቻ ነው ምርምርና ስርፀት ላይ ማዋል የቻለችው ብለዋል ዳይሬክተሩ።

ከዚህ በተጨማሪ በምርምርና ስርፀት ላይ ተሰማርተው የሚገኙ ባለሙያዎች ቁጥር 31 ሺህ ብቻ መሆኑን ጥናቱ ያሳያል። ተመራማሪዎቹ ከተሰማሩባቸው ዘርፎች መካከል ግብርና፣ ምህንድስና፣ ጤና እንዲሁም በተፈጥሮና ማህበራዊ ሳይንስ ይጠቀሳሉ።

ከዚህ ውስጥ 49 በመቶ የሚሆኑት ምርምሮች የተተገበሩት ግብርና ላይ ሲሆን 15 በመቶ ምህንድስና እንዲሁም 13 በመቶ ጤና ላይ ነው።

አዲስ አበባ፡ የፈጠራ ማዕከል ለመሆን እየጣረች ያለች ከተማ

ከ100 ሚሊየን በላይ ሕዝብ ባለባት ሃገር 31ሺህ ብቻ ባለሙያዎች በቂ ነው ወይ ለሚለው ጥያቄ አቶ ሳንዱካን ሲመልሱ '' ኢትዮጵያ ውስጥ 305 የምርምርና ስርፀት ባለሙያዎች ለአንድ ሚሊየን ሰዎች ነው የሚዳረሱት። የሌሎች ሃገራትን ቁጥር ከግምት ውስጥ በማስገባት ዝቅተኛ መሆኑን መረዳት ይቻላል።'' ብለዋል።

'' የሴኔጋልን ብናይ ሥርጭቱ 1108 ባለሙያዎች ለአንድ ሚሊየን ህዝብ ሲሆን በግብጽ 2460 ለአንድ ሚሊየን እንዲሁም በደቡብ አፍሪካ 1350 ባለሙያዎች ለአንድ ሚሊየን ሕዝብ ነው። ይህ ከፍተኛ ልዩነት እንዳለ ማሳያ ሊሆን ይችላል። ''

በ2016 ዓ.ም. በተሠራው ጥናት መሠረት ኢትዮጵያ ከአጠቃላይ ሃገራዊ ምርቷ 0.61 በመቶ የሚሆነውን ለምርምርና ስርፀት አውላለች። ይህ ደግሞ ባለፈው ዓመት በዘርፉ ካዋለችው ጋር ሲነጻጸር ከፍ ያለ ነው። ነገር ግን አቶ ሳንዱካን ከዚህ በፊት የነበረው ቁጥር ከፍ ይበል እንጂ ጤናማ ያልሆነ ኢንቨስትመንት ነበር የተደረገው ይላሉ።

'' አብዛኛው ኢንቨስትመንት ሦስተኛ ትውልድ በሚባሉ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ላይ ነው ፈሰስ የተደረገው፤ ለቤተ ሙከራ የሚያገለግሉ ቤቶችን መገንባት፣ ለሠርቶ ማሳያ የሚጠቅሙ መሳሪያዎች እንዲሁም ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ነው ወጪ የተደረገው። ስለዚህ የምርምርና ስርፀት ሥራዎች ላይ ሙሉ በሙሉ ውሏል ማለት አይቻልም'' ብለዋል -አቶ ሳንዱካን።

ዩኒቨርሲቲዎችና ምርምር

የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ኢንስቲቲዩት የሠራው ጥናት እንደሚያመላክተው በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚሰሯቸው የምርምር ውጤቶች አብዛኛዎቹ ወደ መሠረታዊ ጥናት ያጋደሉ ናቸው። ይህ ደግሞ የሕዝቡን ችግር ተረድቶ መፍትሔ ማምጣት የሚችል ዓይነት ጥናት ሳይሆን፤ እውቀት ለማዳበርና የትምህርት ደረጃን ከፍ ለማደረግ የሚሠራ ነው።

በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚሠሩ የምርምርና ስርፀት ውጤቶች ለምንድነው ከመጽሃፍት መደርደሪያ ማለፍ ያልቻሉት? የሚለውን ጥያቄ በጥናታችን አጽንኦት ሰጥተን ነው የሠራነው ይላሉ አቶ ሳንዱካን።

እርሳቸው እንደሚሉት ባለፉት ሃምሳ ዓመታትና ከዚያም በላይ በዩኒቨርሲቲዎቻችን የሚደረጉ የምርምር ውጤቶች የማህበረሰቡን ሕይወት ሲቀይሩ አልታዩም። አሁንም ባለው ሁኔታ ከፖለቲካ አመራሩ እስከ ትላልቅ የግል ድርጅቶች ድረስ ለሚገጥሟቸው ማንኛውም ዓይነት ችግሮች ወደ ውጪ ሃገራት ሄደው የምርምር ውጤቶችን ስለመግዛት እንጂ ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመተባበር ምርምር ስለማድረግ እንደማያስቡም ይናገራሉ።

''ከዚህ በተጨማሪም ዩኒቨርሲቲዎቹ የሚሰሯቸው የምርመር ውጤቶች ወደተለያዩ ዘርፎች ወርደው የገበሬውንና ሌሎች የማህበረሰብ ክፍል ችግሮችን ሲፈቱ አይታዩም።'' በማለት አክለዋል።

አንዲት ሃገር በሃገር ውስጥ በሚሰሩ ምርምሮች ላይ አልያም ከውጪ የሚገቡ የምርምር ውጤቶች ላይ ትኩረት አድርጋ የማትሰራ ከሆነ የምትመራው በስትራቴጂና በፖሊሲ መሆኑ ቀርቶ በደመነፍስ ከመመራት የተለየ እንደማይሆን ባለሙያው አስረድተዋል።

«ሰው ሲበሳጭ ማስታወሻ እይዝ ነበር» አዲስ ዓለማየሁ

ኢትዮጵያ ውስጥ የምርምርና ስርፀት ሥራዎች ቁጥር በእጅጉ ለመቀነሱ ብዙ ምክንያቶች ያሉ ሲሆን የሚከተሉት ግን ዋና ዋናዎቹ ናቸው።

• የመንግሥት ድርጀቶች፣ የግል ተቋማትና ግለሰቦች ምርምርና ስርጸትን እንደ ገንዘብ ብክነት አድርጎ መቁጠር

• የግል ድርጅቶችና የንግድ ተቋማት ዝቅተኛ ተሳትፎ

• በዘርፉ የሰለጠኑ ባለሙያዎች ቁጥር እጅጉን አነስተኛ መሆን እና

• ምርምርና ስርጸትን የሚደግፉ ፖሊሲዎችና ማበረታቻዎች በአግባቡ አለመዘርጋት ናቸው።

ሳይንስና ቴክኖሎጂ ላይ የሚደረጉ ኢንቨስትመንቶች ውጤታቸው በአንድ ጊዜ የሚታይ ሳይሆን ቀስ በቀስ የሚመጣና ውጤታማ ፖሊሲ መዘርጋትን ግድ የሚያደርግ ዘርፍ ነው።

አንዲት ሃገር አስተማማኝ ኢኮኖሚያዊ ሥርዓት መዘርጋት የምትፈልግ ከሆነ የምትሸጣቸውን የግብርናም ምርት ይሁን ኢንዱስትሪ ውጤቶች እንዲሁም ከውጪ ሃገራት የምትገዛቸውን ውጤቶች በምርምርና ስርፀት ማስደገፍ ግዴታ ነው።

ጥናቱ ዋና ዓላማው አድርጎ የተነሳውም ክፍተት የሚታይባቸው ቦታዎችን ለይቶ የምርምርና ስርጸት ሥራዎች ቁጥር እንዲጨምር ተገቢውን መረጃ ማቅረብ እንጂ የምርምር ሥራ ውስጥ መግባት እንዳልሆነ አቶ ሳንዱካን ገልፀዋል።