ፌስቡክ ሦስት ቢሊዮን አካውንቶችን አገደ

ፌስቡክ Image copyright Reuters

ፌስቡክ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ከጥቅምት እስከ መጋቢት ድረስ በነበሩት ስድት ወራት ውስጥ ከሦስት ቢሊየን በሚልቁ ሐሰተኛ አካውንቶችን በማገድ እርምጃ መውሰዱን አስታወቀ።

በተጨማሪም ከሰባት ሚሊየን የሚበልጡ "የጥላቻ ንግግሮችን" የሚያንጸባርቁ መልዕክቶችን ማስወገዱንም ይፋ አድርጓል።

ፌስቡክ ግላዊ መረጃን አሳልፎ በመስጠት ተከሰሰ

ፌስቡክ ይህንን የገለጸው ከጥቅምት እስከ የካቲት ወር በማኅበራዊ መድረኩ በኩል የተሰራጩ ምን ያህል ተቀባይነት የሌላቸው መረጃዎችና የፌስቡክ ገጾች ላይ እርምጃ እንደወሰደ ባስታወቀበት ሪፖርቱ ላይ ነው።

በፌስቡክ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ከፌስቡክ ገጾች ላይ እንዲሰረዙ በተደረጉ መልዕክቶች ምክንያት ምን ያህሎቹ ማብራራሪያ እንደጠየቁና ምን ያህሎቹም ምርመራ ከተደረገባቸው በኋላ ወደገጾቻቸው እንዲመለሱ እንደተደረገ ይፋ አድርጓል።

ፌስቡክ የጽንፈኛ አመለካከት አራማጆችን ሊያግድ ነው

ፌስቡክ እንዳለው፤ እንዲወገዱ የተደረጉት ሐሰተኛ አካውንቶች ቁጥር መጨመር ምክንያቱ "መጥፎ" ያላቸው አካላት የተለየ ዘዴን በመጠቀም ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ገጾች መክፈት በመቻላቸው ነው።

ነገር ግን ፌስቡክ ከእነዚህ መካከል አብዛኛዎቹ "ጉዳት ለማድረስ" የሚያስችላቸውን አጋጣሚ ከማግኘታቸው በፊት በተከፈቱ በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ በመለየት እንዲሰረዙ ማድረጉን አሳውቋል።

ፌስቡክ የምንጠቀምበት ሰዓት ሊገደብ ነው

የማኅበራዊ መገናኛ መድረኩ ጨምሮ እንደገለጸው፤ እፆችና የጦር መሣሪያዎችን የመሳሰሉ ቁጥጥር የሚደረግባቸውን ነገሮች ሽያጭ የተመለከቱ ምን ያህል መልዕክቶች እንዲነሱ እንዳደረገ ይፋ እንደሚያደርግ አሳውቋል።

ፌስቡክ አሁን ያወጣው ሪፖርት ላይ እንዳመለከተው፤ ባለፉት ስድት ወራት ከአንድ ሚሊዮን በላይ የጦር መሣሪያ ሽያጭን የተመለከቱ መልዕክቶች እንዲነሱ አድርጓል።