የሸንኮራ አገዳ አምራቾች የወንጂ ስኳር ፋብሪካ ይገባናል አሉ

የሸንኮራ ማሳ

የወንጂ ስኳር ፋብሪካ ያረፈበት እና የሸንኮራ አገዳው የሚመረትበት 5 ሺህ ሄክታር መሬት የአካባቢው ነዋሪዎች ተፈናቅለውበት ስለሆነ የፋብሪካው ግዥ እኛን ይመለከተናል ይላሉ የአካባቢው የሸንኮራ አገዳ አምራች አርሶ አደሮች።

በከፊልም ሆነ ሙሉ በሙሉ ወደ የግል እንዲዘዋወሩ ከተወሰኑ ፋብሪካዎች መካከል አንዱ የወንጂ ስኳር ፋብሪካ ነው። ከአዳማ ከተማ 10 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው ይህ ፋብሪካ ለምርቱ ከሚያገኘው የ12800 ሄክታር መሬት የሸንኮራ አገዳ ምርት ውስጥ 7 ሺው ሄክታር በተደራጁ አርሶ አደሮች አማካይነት የሚቀርብ ነው።

በዚህም የፋብሪካው 60 በመቶ የሸንኮራ አገዳ አቅርቦት በአካባቢው አርሶ አደሮች ሲሆን አሁን የታቀደው የፋብሪካው ሽያጭ ከእጃችን መውጣት የለበትም ይላሉ። አርሶ አደሮቹ የወንጂ አካባቢ የሽንኮራ አገዳ አምራቾች ዩኒየን በሚል ማህበር ስር ተሰባስበው ነው ፋብሪካውን ለመግዛት የፈለጉት።

ይህ የአርሶ አደሮች ዩኒየን ሲመሰረት ከያዛቸው ትልልቅ አላማዎች መካከል አንዱ ፋብሪካውን ሙሉ በሙሉ መግዛት መሆኑን የዩኒየኑ ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ መሃመድ ሁሴን ይናገራሉ።

የስኳር ፋብሪካዎችን ለግል ባለሃብቶች የመስጠት ፋይዳና ፈተናዎቹ

ኮንዶም መጠቀም እያቆምን ይሆን?

"መንግሥት አሁን የያዘው ፋብሪካውን ወደ ግል የማዞር ዕቅድ አላማችንን ለማሳካት ጥሩ አጋጣሚ ነው" በማለት ጨምረውም ፋብሪካው ያረፈበት እና የሸንኮራ አገዳው የሚመረትበት 5 ሺህ ሄክታር የሚሆነው መሬት አርሶ አደሮች የተፈናቀሉበት ስለሆነ እንዲመለስ እናደርጋለንም ብለዋል።

"በመጀመሪያም ፋብሪካው የተገነባው ከአካባቢው አርሶ አደሮች በተወሰደ መሬት ላይ ነው። በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ የፋብሪካውን የአገዳ ምርት 60 በመቶ እኛ ነን የምናቀርበው። ስለዚህም እኛ ይህንን ያህል ግብአት እያቀረብን መንግሥት አሳልፎ ለሌላ ከሚሰጥ ዩኒየኑ ቢገዛው ጥሩ አጋጣሚ ነው" ይላሉ አቶ መሃመድ ዩኒየኑ ፋብሪካውን እንደሚገዛው ያላቸውን ተስፋ በመግለጽ።

የስኳር ፋብሪካው በመንግሥት እጅ በነበረበት ወቅት የሥራ እድል እንዳላገኘ የሚናገረው ወጣት ገዛኸኝ ደምሴ፤ ዩኒየኑ የፋብሪካው ግዥ የሚሳካለት ከሆነ ግን ሰፊ የሥራ ዕድል እንደሚኖር ያምናል። ሌሎች የአካባቢው አርሶ አደሮችም ዩኒየኑ ፋብሪካውን በባለቤትነት መያዝ ከቻለ ግብአት በማቅረብ ተጠቃሚነታችን ይጨምራል ብለው ያስባሉ።

የሽያጭ ሂደት

የወንጂ ስኳር ፋብሪካ ሃገሪቱ ውስጥ ካሉት ቀደምት የስኳር ፋብሪካዎች አንዱ ሲሆን በ1952 ነበር ማምረት የጀመረው። በአሁኑ ወቅትም በዓመት 174 ሺህ ቶን ስኳር እያመረተ ይገኛል። በተጨማሪም ከስኳር ከሚገኘው ተረፈ ምርት ኢታኖልና ሞላሰስ ይመረታል።

በፋብሪካው ሽያጭ ላይ የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽንና የገንዘብ ሚንስቴር በጋራ በመሆን የሽያጭ ቅድመ ሁኔታ ሰነድ በሚያዝያ ወር 2011 ዓ.ም አዘጋጅተዋል። ይህንንም ተከትሎ ፋብሪካውን ለመግዛት ፍላጎት ያላቸው የሃገር ውስጥና የውጪ ተቋማት ተጨማሪ መረጃ እያቀረቡ መሆኑን የስኳር ኮርፖሬሽን የኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተሩ አቶ ጋሻው አይችሉህም ይናገራሉ።

የመጭው ዘመን አምስቱ ምርጥ ምግቦች

ይህም እነዚህን ፋብሪካዎች በከፊልም ሆነ በሙሉ ወደ ግሉ ዘርፍ ለማስተላለፍ የኢንቨስተሮችን ፍላጎት ማወቅ፣ የትኞቹ ፋብሪካዎች ላይ ፍላጎት እንዳለ መለየት፣ የግዥ ፍላጎት ያለቸው ተቋማት ምን አይነት ግዥ እንደሚፈልጉና እነዚህን ተቋማትን የሚገዙ ኢንቨስተሮች የካፒታል ምንጫቸውን ለማወቅ የሚረዳ ሰነድ መሆኑን ይገልጻሉ። ይህንን ፍላጎትም በዝርዝር ለማቅረብ ግንቦት 16/ 2011 ዓ.ም የመጨረሻው ቀን ነው።

የወንጂ ስኳር ፋብሪካን ለመግዛት በማኅበር ተሰባስበው አስፈላጊውን ነገር በማድረግ ላይ የሚገኙትን አርሶ አደሮችን ፍላጎት በተመለከተም የተጠየቁት አቶ ጋሻው እንደሚሉት "ዩኒየኑ የግዥ ፍላጎቱን በመግለጽና በአስፈላጊው ሂደት ውስጥ መሳተፍ እንደሚችልና ለዚህም በራቸው ክፍት መሆኑን" አመልክተዋል።