ኤቨረስት፡ " ከተራራው ጫፍ ሰዎች ሲወድቁ አይቻለሁ" ሲራክ ስዩም

ሲራክ ተራራውን በመውጣት ላይ Image copyright Sirak Seyoum

ትናንት ቅዳሜ የኤቨረስት ተራራን ወጥቶ ካጠናቀቀ በኋላ የሞተው እንግሊዛዊ ሮቢን ሃይነስ፤ በቅርቡ ተራራው ላይ የሞቱትን ሰዎች ቁጥር 10 አድርሶታል። የ44 ዓመቱ ሮቢን ሕይወቱ ያለፈው ጉዞውን አጠናቆ ተራራውን ሲወርድ ባጋጠመው ህመም ነበር።

ኢትዮጵያዊው ሲራክ ስዩምም ይህንኑ ተራራ ሚያዚያ 15 /2011 ዓ.ም መውጣት መጀመሩን ዘግበን ነበር። ሲራክ ምን ላይ ደርሷል?

ኢትዮጵያዊው የዓለማችን ትልቁን ተራራ መውጣት ጀመረ

ሲራክ በተራራው ላይ ያሉትን አራት ካምፖች ሲለማመድ ቆይቶ የመጨረሻውና አራተኛው ካምፕ ላይ ደርሶ ነበር። ገና ተራራውን ለመውጣት ሲያስብ ፈታኙን ጊዜ የተጋፈጠ ቢሆንም ከካምፕ አራት በኋላ ደግሞ የበለጠ የተራራውን ፈታኝ ሁኔታ ገጥሞታል።

ተራራው አናት ለመድረስ ከሚነሱበት ካምፕ አራት ከደረሱ በኋላ ምግብ ተመግበው፣ ተዘገጃጅተው፣ ኦክስጅን ይዘውና ትንሽ ጋደም ብለው ለጉዟቸው ተሰናዱ።

ሲራክ እንደሚለው ከባህር ጠለል በላይ 8 ሺህ ሜትር ከፍታ በላይ በሆነው በዚህ ካምፕ ላይ መተኛት አይቻልም። የተራራው ከፍታ፣ ነፋሱ፣ ጉጉቱና ያለው ስጋት ተደራርበው እንቅልፍ አላስወሰዳቸውም።

በዚህ ሁኔታ ረቡዕ ግንቦት 7/2011 ዓ.ም ከምሽቱ 3፡00 ሰዓት አካባቢ ካምፑን ለቆ ጉዞ ጀመረ። ወደ ተራራው ጫፍ ለመጠጋትም ለ11 ሰዓታት የሌሊት ጉዞ አድርጓል፤ ይሁን እንጂ ተራራው ጫፍ ላይ ለመድረስ 400 ሜትር ሲቀረው ሳያጠናቅቅ መመለሱን ነግሮናል።

ምክንያቱን የጠየቅነው ሲራክ "እኔ የማስበው የጥፍር፣ የጣትና የእግር መቆረጥን ነበር" ይላል። ኔጋቲቭ 40 ዲግሬ ሴንቲ ግሬድ የተለካውን ቅዝቃዜ አልቻለውም። ቅዝቃዜው የሰውነት መገጣጠሚያዎችን ሰርስሮ ሲገባ የደም ዝውውርን ያስተጓጉላል። ይህም ይበልጥ ተጋላጭ የሆኑ የሰውነት ክፍሎችን መቁረጥ ይጀምራል።

የኤቨረስት ተራራን የወጡ ታዳጊዎች ተሸለሙ

እንዲህ ዓይነት ስጋት ይኑረው እንጂ በጉዞው ስህተት ሰራሁ ብሎ የሚያስበውንም ሳይጠቅስ አላለፈም። የጉዞ መሪው ጭንቅላትን ከጉዳት የሚከላከለው ቆብ(ሄልሜት) ክፍተት ስላለውና ይበልጥ ቅዝቃዜ ስለሚያስገባ እንዲተወው ቢመክረውም አለመስማቱ አንዱ ምክንያት እንደሆነ ይጠቅሳል። በኋላ ላይ ግን ሄልሜቱን አውልቆ ጉዞውን ለመቀጠል ሞክሮ ነበር።

ይህ ብቻም ሳይሆን ቀደም ሲል በቂ ውሃ ባለመጠጣቱ አቅም ሲያንሰውና ሰውነቱ የፈሳሽ እጥረት ሲገጥመው እንደታወቀው ይናገራል።

" በሻንጣዬ የያዝኩትን ምግብም ይሁን ፈሳሽ አልነካሁትም ነበር" የሚለው ሲራክ አረፍ ብሎ ምግብ ተመገበ፤ ውሃም ጠጣ፤ ነገር ግን ሰውነቱ ቀድሞውኑ ስለተዳከመ የጉዞ መሪው ፎቶግራፍ ተነስተው እንዲመለሱ መከረው፤ እርሱም ተስማማ።

ሲራክ በጉዞው ምን አጋጠመው?

"የትም ስንሄድ እንደ ታማሚ ኦክስጅን በአፋችን ላይ አድርገን ነው" የሚለው ሲራክ በካምፕ አራት ድንኳኑ ውስጥ ተኝቶ ሳለ በአጋጣሚ አፉ ላይ ተገጥሞ የሚተነፍስበት ኦክስጅን ወልቆ ነበር። አጋጣሚ ሆኖ አብሮት የነበረው ካናዳዊ ተራራ ወጪ ቀስቅሶ ኦክስጅኑን እንዲያደርግ ባይነግረው ኖሮ በዚያው የሚያሸልብበት አጋጣሚ ከፍተኛ ነበር።

"አንዳንድ ተራራ ወጪዎች፤ ኦክስጅን ይጨርሱና ወደ ጎረቤት ድንኳን ለመዋስ ይመጣሉ፤ ነገር ግን ማን ይሰጣቸዋል" ሲል ሁሉም ሰው ከራሱ በስተቀር ሌላ ሰው መርዳት የማይችልበት ቦታም እንደሆነ ይናገራል።

ተራራውን መውጣት በራሱ ልምድን የሚጠይቅና ፈታኝ ቢሆንም እርሱ ግን የከፋ ጉዳት ሳይገጥመው ሊመለስ ችሏል።

Image copyright AFP/PROJECT POSSIBLE
አጭር የምስል መግለጫ በዚህ ዓመት ብቻ 20 የሚሆኑ ተራራ ወጪዎች ሕይወታቸው አልፏል

የተራራ ወጪዎችን ሕይወት የሚቀጥፈው ምንድን ነው?

"ተራራውን ስወጣ ከተራራው አናት ላይ ሰው ሲወድቅ አይቻለሁ" የሚለው ሲራክ በወቅቱ የሆነውን አይቶ ማመን አልቻለም ነበር።

እርሱ እንደሚለው ሰውዬው እየወጣ የነበረው በኔፓል አቅጣጫ ባለው የተራራው ክፍል ቢሆንም የወደቀው ግን በቻይና በኩል በሚገኘው ሌላኛው የተራራው ክፍል ነው። "አስክሬኑን ለማንሳት የወደቀበት አቅጣጫ ቢታወቅም፤ አካሉን ማግኘት ግን የማይቻል ነው" ይላል- አስከፊነቱን ሲገልፅ። በጣም በመደንገጥም ውስጡን ማዳመጥ ጀምሮ ነበር።

በተለይ በዚህ ዓመት በርከት ያሉ ተራራ ወጪዎች ሕይወት እንዳለፈ ሲራክ ይናገራል።

አንድ የእርሱ የቡድን አባል የሆነም ሰው ተራራውን ወጥቶ ከጨረሰ በኋላ እግሩ ከፍተኛ ጉዳት አጋጥሞት ከካምፕ ሁለት በሄሊኮፕተር መወሰዱን ይገልፃል።

ተራራ ወጪዎች ወደ ተራራው ሲወጡ፣ አጠናቀው ሲመለሱ፣ አሊያም አገር ሰላም ብለው በተኙበት ድንኳናቸው ውስጥ ሕይወታቸው ሊያልፍ ይችላል።

ተራራው ጫፍ ደርሰው ከተመለሱ ሁለት ህንዳዊያንም፤ ካምፕ አራት ከእነርሱ ድንኳን ብዙም ሳይርቅ ጠዋት ሲነሱ የአንደኛውን አስክሬን እንዳዩት ነግሮናል።

ሌላም ተራራ ወጪ እንዲሁ ተራራውን አጠናቆ ከተመለሰ በኋላ ጠዋት ድንኳኑ ሲፈተሽ ከቦታው እንዳልተገኘ ሲራክ ይናገራል።

ለዚህ ሁሉ አንዴ ከፍያለሁ በሚል የራሳቸውን አቅም ሳያገነዘቡ መጓዝ፣ የኦክስጅን ማለቅ፣ የከፍታ ቦታ ፍርሃት፣ ራስን መሳት፣ የትራፊክ መጨናነቅ ዋና ዋናዎቹ ምክንያቶች እንደሆኑ ይናገራል።

እርሱ እንደሚለው በተለይ በተራራው ላይ እንደ ጉንዳን መስመር ሰርተው የሚጓዙት ተራራ ወጪዎች ቀስ ብለው ስለሚራመዱና ብዙ ጊዜ እነርሱን ለማለፍ አስቸጋሪ ስለሚሆን ጉልበት ያልቃል።

በዚህ ጊዜ ባልተገባ መልኩ ለመቅደም ሲሞክሩ አሊያም እዚያው ባሉበት አቅማቸውን ጨርሰው ሕይወታቸው ያልፋል። "አንዳንዴ የደከሙ አሊያም የሞቱ ሰዎችን በገመድ እየጎተቱ ያወርዷቸዋል" ሲል አንዲት በተዓምር የተረፈች ህንዳዊትን ተሞክሮ ያነሳል።

እርሱ ከተራራው እየተመለሰ ሳለ ነበር ይህች ሴት መንቀሳቀስ ተስኗት በረዶው ላይ ተኝታ የተመለከተው። በዚህ ቦታ ማንም ማንንም የሚረዳበት አቅም ስለሌለው እያዩዋት እንዳለፉ ያስታውሳል።

ይሁን እንጂ የጉዞ መሪዋ በገመድ እንደ ዕቃ እየጎተተ ካምፕ ሁለት አድርሷታል። ሲራክ " እንደ ዕድል ተረፈች" የሚላት ሴት ከካምፕ ሁለት በሄሊኮፕተር እንደተወሰደች ለማወቅ ችሏል።

ሌላም ከጉዞ መሪው ጋር በሃሳብ ያልተግባባ ፓኪስታናዊ ሕይወቱ አልፏል።

ሲራክ እንደነገረን 'መውጣት አትችልም፤ መመለስ አለብህ' በሚለው የጉዞው መሪ ምክርና 'ገንዘቤን ስለከፈልኩ መውጣት አለብኝ፤ ከፈለክ ተጨማሪ እከፍልሃለሁ' በሚለው የፓኪስታናዊው ተቃራኒ ሃሳብ የሁለቱን ሕይወት አደጋ ላይ ጥሏል።

ፓኪስታናዊው በዚህ እሰጥ አገባ ውስጥ ጉዞውን ቀጥሎ ተራራው ጫፍ ላይ ሲደርስ ራሱን ስቶ ወድቋል።

በዚህ ጊዜም የጉዞ መሪው እርሱን ለመርዳት ሲል ጣቶቹ እንደተቆረጡና የጉዞ መሪው ከዚያ በኋላ በሙያው ሥራ መስራት እንደማይች ሲራክ ስዩም አውግቶናል።

"ተራራ የመውጣት ልምድ ቢኖረኝም፤ በአሁኑ ጉዞዬ ብዙ ተምሬያለሁ" የሚለው ሲራክ በሚቀጥለው ዓመት ተራራውን ለመውጣት እንደሚያስብም ገልፆልናል።

የኤቨረስት ተራራን በመውጣት ላይ ሳሉ ሕይወታቸው የሚያልፍ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ በመምጣቱ፤ ለተራራ ወጪዎች የሚሰጠው ፈቃድ ውስን እንዲሆን የሚጠይቁ ሰዎች ብቅ እያሉ ነው።

ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር በዚህ ዓመት በርካታ ተራራ ወጪዎች የነበሩ ሲሆን የኤቨረስት ጫፍ ላይ በመድረስ ጉዞውን ያጠናቀቁት ሰዎች ቁጥርም 807 ከፍ ብሏል።

ተያያዥ ርዕሶች

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ