የኢራቅ ፍርድ ቤት የአይኤስ አባላት በሆኑ ፈረንሳዊያን ላይ የሞት ፍርድ በየነ

በአብዛኛው እስላማዊ ታጣቂ ቡድኑ የሚጠቀምበትና ግድግዳ ላይ የተሳለ ጥቁር ሰንደቅ ዓላማ Image copyright Reuters
አጭር የምስል መግለጫ ሦስቱ ፈረንሳዊያን እስላማዊ ቡድኑን በመቀላቀል ጥፋተኛ ሆነው ተገኝተዋል።

የኢራቅ ፍርድ ቤት እስላማዊ ቡድኑን በመቀላቀል ጥፋተኛ ሆነው አግኝቻቸዋለሁ ያላቸው ሦስት ፈረንሳዊያን ላይ የሞት ፍርድ አስተላልፏል።

ግለሰቦቹ ሶሪያ ውስጥ በአሜሪካ ተዋጊዎች በቁጥጥር ሥር ከዋሉ 12 የፈረንሳይ ዜጎች መካካል ሲሆኑ ባለፈው የካቲት ወር ወደ ኢራቅ ተላልፈው ተሰጥተዋል።

አይ ኤስን ተቀላቅላ የነበረችው እንግሊዛዊት ዜግነቷን ልትነጠቅ ነው

ክቪን ጎኖት፣ ሊዎናርድ ሎፔዝ እና ሳሊም ማቾ የተባሉት እነዚህ ግለሰቦች የመቃወሚያ ቃላቸውን እንዲሰጡ የ30 ቀናት የጊዜ ቀጠሮ መሰጠታቸውን ኤ ኤፍ ፒ የዜና ወኪል ዘግቧል። ሦስቱ ግለሰቦች በአይ ኤስ ቡድን አባልነት ተጠርጥረው የሞት ፍርድ የተበየነባቸው የመጀመሪያዎቹ ፈረንሳዊያን ናቸው።

በባግዳድ የታየውን የእነዚሁ ግለሰቦች የፍርድ ሂደት አስመልክቶ ፈረንሳይ ያለችው ነገር የለም። ይሁን እንጂ ባለፈው የካቲት ወር ጉዳዩ ሲነሳ የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክክሮን "ይህ የኢራቅ ሉአላዊነት ጉዳይ ነው " ሲሉ አስተያየት ከመስጠት መቆጠባቸው ይታወሳል።

ይህንን ፍርድ አስመልክቶ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ውሳኔውን ተችተዋል። አክቲቪስቶች በበኩላቸው ፍርድ ቤቱ ባለው መረጃ ላይ ተመስርቶ ውሳኔውን እንዳስተላለፈ ተናግረዋል።

ስለ ሦስቱ ፈረንሳዊያን ምን እናውቃለን?

የ32 ዓመቱ ጎኖት የመጣው ከፈረንሳይ ደቡብ ምስራቃዊ ክፍል ነው። ወደ ሶሪያ የገባው በቱርክ በኩል ሲሆን አመጣጡም የአልቃይዳ ቅርንጫፍ የሆነውን ኑስራ ግንባር ለመቀላቀል ነው።

በሶሪያ ከእናቱ፣ ከሚስቱ እና ከወንድሙ ጋር ከሁለት ዓመታት በፊት ለእስር ተዳርጎ ነበር። የፈረንሳይ ፍርድ ቤትም በሌለበት የዘጠኝ ዓመታት እስር ወስኖበት ነበር።

የአይ ኤስ መሪ ባግዳዲ ድምፁ ተሰማ

በፈረንሳይ ሽብርተኝነትን በሚመለከት ውይይት በማካሄድ የሚታወቀው ሲ ኤ ቲ ድርጅት እንዳለው ሌላኛው የ41 ዓመቱ ማቾ በኢራቅና ሶሪያ ላይ ጥቃት የሚያደርሰው የአውሮፓ ተዋጊዎች የአይ ኤስ ህዋስ አባል የነበረ ሲሆን በፓሪስና በብራስልስ ተመሳሳይ ጥቃት ለማድረስ እቅድ ነበረው።

ከፓሪስ የመጣው የ32 ዓመቱ ሎፔዝ ደግሞ ወደ ሶሪያ ከማቅናቱ በፊት ከሚስቱና ከሁለት ልጆቹ ጋር በመሆን በሰሜናዊው የኢራቅ ክፍል ሞሱል በሚገኘው የአይ ኤስ ቡድንን መቀላቀሉን ሲ ኤ ቲ የፈረንሳይ መርማሪዎችን ጠቅሶ ገልጿል።

ይሁን እንጂ ጠበቃው ናቢል ቦንዲ "በደፈናው የተሰጠ ፍትህ" ሲሉ ክሱን አውግዘውታል።

"ሽብር ምንድን ነው ፣ አሸባሪ ማን ነው?" ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ

ከ41 ሺህ በላይ የሚሆኑና ከአስር በላይ አገራት የመጡ የውጭ ዜጎች በሶሪያና በኢራቅ እስላማዊ ታጣቂ ቡድኑን እንደተቀላቀሉ ይገመታል።

ከእነዚህም መካካል አንድ አራተኛ የሚሆኑት ሴቶችና ህጻናት ናቸው። 6 ሺህ የሚሆኑት ደግሞ ከምዕራብ አውሮፓ የመጡ መሆናቸውም ታውቋል። 145 ሴቶችና 50 ህጻናትን ጨምሮ 850 የሚሆኑት ከእንግሊዝ እንደመጡም ተነግሯል።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ