የአሃዱ ኤፍ ኤም ጋዜጠኛ ታምራት አበራ ፍርድ ቤት ሳይቀርብ በመታወቂያ ዋስ ተለቀቀ

አሀዱ ኤፍ ኤም ሎጎ Image copyright Ahadu FM Facebook page

አርብ አመሻሽ ላይ በሠንዳፋ ፓሊስ በሥራ ገበታው ላይ እያለ በቁጥጥር ሥር የዋለው የአሀዱ ኤፍኤም ጋዜጠኛ ታምራት አበራ ዛሬ በመታወቂያ ዋስ መለቀቁን የጣቢያው ምክትል አዘጋጅ ሊዲያ አበበ ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

ጋዜጠኛው ዛሬ ፍርድ ቤት ሳይቀርብ የዋስ መብቱ እንደተከበረለት የተናገሩት ምክትል አዘጋጅዋ እርሳቸው፣ የዜና ክፍል ኃላፊውና ምክትል ኤዲተሩ ረቡዕ ዋስ ይዘው መጥተው ቃላቸውን እንዲሰጡ እንደተነገራቸው ለማወቅ ችለናል።

አርብ ከምሽቱ 11፡00 አካባቢ ሁለት የኦሮሚያ ሰንዳፋ አካባቢ ፖሊስ አባላት ከአዲስ አበባ ቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 8 ፖሊስ መምሪያ ባልደረባ ጋር በመሆን በአሃዱ ኤፍ ኤም ሬዲዮ ጣቢያ ቢሮ በመምጣት ጋዜጠኛ ታምራት እና የሬዲዮ ጣቢያው ሥራ አሥኪያጅ አቶ ጥበቡ በለጠ እንደሚፈለጉ በመግለፅ መጥሪያ ማሳየታቸውን የጣቢያው ምክትል አዘጋጅ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በወቅቱ ጋዜጠኛ ታምራት የተፈለገበት ጉዳይ ምን እንደሆነ ጠይቀው ፖሊስ አስሮ እንዲያመጣቸው መታዘዙን ቀሪውን ፍርድ ቤቱን ትጠይቃላችሁ በማለት ወደ ፖሊስ ጣቢያ ወስደውታል።

የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ይቅርታ ጠየቀ

የጄል ኦጋዴን እስር ቤት ኃላፊ ተይዞ ለኢትዮጵያ ተሰጠ

አይስላንድ አንድ ተማሪ ብቻ የቀረውን ትምህርት ቤት ልትዘጋ ነው

በእለቱ እስከ ምሳ ሰዓት የጣቢያው ሥራ አስኪያጅ አቶ ጥበቡ በሥራ ገበታቸው ላይ የነበሩ ቢሆንም ከሰአት ግን እንዳልነበሩ ያስረዱት ምክትል አዘጋጇ የዛኑ እለት አመሻሽ ላይ ከሀገር ውጪ ለሥራ ወጥተው እንደሚገኙ አረጋግጠዋል።

ፖሊስ ወደ አሀዱ ቢሮ በመጣበት ወቅት በመጥሪያው ላይ ተጠርጣሪዎች ተብለው አራት ሰዎች ስማቸው ሰፍሮ ማየታቸውን የሚናገሩት አዘጋጇ አንደኛዋ የፍርድ ባለ እዳዋ ሲሆኑ ሌሎቹ ሦስቱ የእርሳቸው ቤተሰቦች መሆናቸውን ገልፀዋል።

እነዚህ የፍርድ ባለ እዳ እና ተጠርጣሪዎቸ ክሱ የተመሰረተበት ሰንዳፋ አካባቢ ነዋሪ መሆናቸውንና አሁንም በመኖሪያ ቤታቸው እንደሚገኙ የሚናገሩት ሊዲያ እነርሱ ፍርድ ቤትም ሆነ ፖሊስ ጣቢያ እንዲቀርቡ እንዳልተደረገ ይናገራሉ።

ጋዜጠኛ ታምራት በቁጥጥር ስር በዋለበት ወቅት ጉዳዩ በሽምግልናና በንግግር የሚፈታ ከሆነ በማለት የሬዲዮ ጣቢያው የሚገኝበት ቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 8 ፖሊስ መምሪያ እንደተወሰደ የሚናገሩት ሊዲያ የጣቢያውን አዛዥ በማነጋገር ሠንዳፋ ነው የምንወስደው በማለት ወደዚያው እንደወሰዱት ያስረዳሉ።

በአሁኑ ሰዓት ሠንዳፋ በኬ 02 የሚባል የከተማው ፖሊስ ጣቢያ ውስጥ የሚገኘው ጋዜጠኛ የአሀዱ ሬዲዮ ጠበቃ አቁሞለት እንዲከራከርለት እንዳደረገ ተናግረዋል።

ይህ ዘገባ እስከተጠናቀበት ድረስ ፖሊስ ሁለት ጊዜ የጋዜጠኛውን ቃል መቀበሉን የተናገሩት ሊዲያ ሁለት አቃቢያነ ሕጎች የጣቢያውን ባልደረቦች ቃል መቀበላቸውንም ለማወቅ ችለናል።

ጋዜጠኛ ታምራት በሠንዳፋ ፖሊስ በቁጥጥር ሥር የዋለው በሰራው ዘገባ ምክንያት ነው የሚሉት የጣቢያው ምክትል አዘጋጅ ዘገባው ለጣቢያው የተሰራ ስለሆነ በብሮድካስት አዋጁ መሰረት ሊጠየቅ የሚገባው ጣቢያው ነው በማለት ከዚህ በፊት ፍርድ ቤቱ የዘገባውን ቅጂ ጠይቆ መውሰዱን ያስታውሳሉ።

በዘገባው ምክንያት የተከሰሱት ሥራ አስኪያጅና ሪፖርተሩ ብቻ መሆናቸውን አስረድተዋል።

ጉዳዩ ምን ነበር?

ዘገባው በሠንዳፋ ከተማ የገጠር ቀበሌዎች አካባቢ ባሉ ቀበሌዎች በሁለት ተከራካሪ ቤተሰቦች መካከል ያለ የውርስ ጉዳይ ነው። ወደ አሀዱ ቢሮ የመጡት አንዲት ግለሰብ ከአባታቸው መሬት ወርሰዋል።

ወራሽ ነን የሚሉ የወንድሞቻቸው ልጆች ከስሰው በ2001 ዓ.ም ወደ አሀዱ ቢሮ ለመጡት እናት ተፈርዶላቸው ነበር።

ፌስቡክ የአፍሪካ የዴሞክራሲ ሥርዓት ላይ ተጽዕኖ እያሳደረ ነው?

አያት ለልጅ ልጅ ማውረስ አይችልም በሚል ፍርድ ቤቱ ክሱን ዘግቶት ነበር። ነገር ግን በ2009 ከሳሽ የነበሩት ልጆች በተከሳሽ አባት ስም የአባታቸውን ስም አስቀይረው መጥተው በ2009 ይገባቸዋል ተብሎ ተፈርዶላቸው ነበር።

እኚህ እናት ከይግባኝ ሰሚ ቤት እስከ ሰበር ሰሚ ችሎት ድረስ ሄደው የታችኛው ፍርድ ቤት ውሳኔ ይፅና የሚል ውሳኔ ለልጆቹ ተፈረደ።

እኝህ እናት ሕጋዊ ወራሽ እኔ ሆኜ ሳለሁ የአስተዳደር በደል ደርሶብኛል ሲሉ ወደ አሀዱ ሬዲዮ ጣቢያ መጡ። ጣቢያውም የሚመለከተውን አካል ግራ ቀኝ አነጋግሮ ዘገባ ሰርቷል ይላሉ ምክትል አዘጋጇ።

ጋዜጠኛ ታምራት ላይ የተለያዩ ማስፈራሪያዎች እየደርሱበት እንደነበር የሚገልፁት አዘጋጇ አሀዱ ኤፍ ኤም ከዚህ በፊት በብሮድካስት ባለሰልጣንም ሆነ በሌላ አካል ቅሬታ ቀርቦበት እንደማያውቅ ተናግረዋል።

የኦሮሚያንም ሆነ የሰንዳፋ ፖሊስን ለማነጋገር ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።

የሚዲያ ሕጉ ምን ይላል?

የሕግ ባለሙያና የኢትዮጵያ ሚዲያ ሕግ ማሻሻያ የጥናት ቡድን መሪ የሆኑት አቶ ሰለሞን ጎሹ አንድ ጋዜጠኛ ለሚሠራው ሥራ ኃላፊነት አለበት ያሉ ሲሆን፣ "ተላለፈ በተባለው የሕግ ማዕቀፍ የሚወሰን ቢሆንም እንደተላለፈው ሕግ ግለሰቡም ሆነ የሚዲያ ተቋሙ የሚጠየቅበት አግባብ አለ" ይላሉ።

ይሁን እንጂ እርሳቸው እንደሚሉት አንድ ጋዜጠኛ ለሚሰራው ስህተት የማረሚያ ዕድል ሊሰጠው ይገባል።

የወንጀል ጉዳይ ከሆነ ግለሰቡም ሆነ ተቋሙ ተጠያቂ የሚሆኑበት አግባብ ሲኖር በፍትሃብሄር ሲሆን የጋዜጠኛው ኃላፊነት ተትቶ ተቋሙ የሚጠየቅበት አግባብ ይኖራል ብለዋል።

ነገር ግን እንደ ሁኔታው ጋዜጠኛውም የሚጠየቅበት አግባብ አለ በማለት ያክላሉ።

አቶ ሰለሞን የመገናኛ ብዙሃኑን ሕግ 590ን ጠቅሰው " ጋዜጠኛ በሥህተት አይከሰስም፤ ከተሳሳተ ማረሚያ ያወጣል እንጂ አይከሰስም" ይላሉ።

ባለሙያው እንደሚያስረዱት ከተጠየቀም በሕግ የተቀመጡ የተለያዩ አንቀፆች ላይ ተመስርቶ ነው ሲሉ ያብራራሉ።

የጋዜጠኛ ታምራት ጉዳይን ያነሳንላቸው ባለሙያው የጉዳዩን ዝርዝር ባያውቁትም "ጋዜጠኛ ስህተት መስራት አንዱ የሕይወቱ አካል ነው፤ የሠራቸውን ወንጀሎች አሊያም የሕግ ጥሰቶች ተጠቅሶ ነው መጠየቅ ያለበት" በማለት ያብራራሉ።

አክለውም ጋዜጠኛ ተጠርጥሮ እንኳን ቢታሰር "ሲከራከር ታስሮ አይደለም፤ የዋስትና መብቱን አቅርቦ ፍርድቤቱን የሚጠይቅ ሳይሆን ጋዜጠኛ በመሆኑ ፍርድ ቤቱ ራሱ ወጥቶ እንዲከራከር እንዲፈቀድለት የሚዲያ ሕጉ ያዛል" ይላሉ።

የሚዲያ ሕጉ የተለያዩ ችግሮች ቢኖሩበትም በዚህ ጉዳይ ግን ግልፅ የሆነ ድንጋጌ ነው ያለው ብለዋል።

አንድ ጋዜጠኛ ስህተት ቢሰራ ማረሚያና ማስተካካያ እንዲያወጣ የሚገደድ ሲሆን የሠራው ስህተት ታስቦበትና ታቅዶበት ነው ከተባለም የወንጀል ሕግ ስለሚሆን ያኔ በጋዜጠኛው ላይ ክስ መመስረት ይቻላል ሲሉ ሀሳባቸውን ይቋጫሉ።