ሲኤንኤን ለዓመቱ ምርጥ ያጫት ኢትዮጵያዊት ፍረወይኒ መብራህቱ

አነስተኛ አቅም ያላቸው ሴቶች በዝቅተኛ ዋጋ እንዲያገኙት የሚረዳ የሚታጠብ ሞዴስ የምታመርተዋ ፍረወይኒ መብራህቱ

ፍረወይኒ መብራህቱ በዘንድሮው የሲኤንኤን 'ሂሮ ኦፍ ዘ ይር' (የዓመቱ ምርጥ) ውድድር ውስጥ ለመጨረሻው ዙር ከደረሱ አስር እጩዎች አንዷ ናት።

የውድድሩ አሸናፊ የፊታችን ሕዳር 28 ቀን 2012 ዓ. ም. ይፋ የሚደግ ሲሆን፤ በርካታ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ለፍረወይኒ ድምጻቸውን እሰጡ ይገኛሉ።

ትዊተር እና ፌስቡክን ጨምሮ በተለያዩ ማኅበራዊ ሚዲያዎች ለፍረወይኒ ድምጽ እንዲሰጥ ቅስቀሳ እተካሄደም ነው።

ቢቢሲ በአንድ ወቅት ስለፍረወይኒ መብራህቱ 'ማርያም ሰባ'፡ ፍረወይኒ 'የወር አበባ አሁንም እንደ ነውር ይቆጠራል' በሚል ርዕስ የሠራው ዘገባ እነሆ፦

በዚህ በሰለጠነ ዓለም እስከ ዛሬ ድረስ የወር አበባ አንዱ የሴት ልጅ ተፈጥሮአዊ ክስተት እንደሆነ የማይቀበሉ ኃይማኖቶችና ባህሎች ያላቸው አገራት ጥቂት አይደሉም።

በበርካታ የአፍሪካ አገራትም ሆነ በሌሎች ሴቶች የወር አበባ በሚያዩበት ወቅት ከኃይማኖታዊ ክንዋኔዎች ተከልክለው ነጻነታቸው በኃይማኖታዊው ወይም ባህላዊው ትምህርት እንዲገዛ ይደረጋል።

ህንድ የወር አበባ እንደነውር ከሚቆጥሩበት አገራት አንዷ ነች። 70 ከመቶ በህንድ የሚገኙ የገጠር ሴቶች በግንዛቤ ችግር፣ በድህነትና ሀፍረት የወር አበባ በሚያዩበት ወቅት ንጽህናቸውን በአግባቡ ስለማይጠብቁ ለሞትና በሽታ የተጋለጡ ናቸው።

በዚህ ምክንያት ቆሽሸዋል ተብለው ስለሚፈረጁ 28 በመቶ ታዳጊዎች ከትምህርት ገበታቸው ይቀራሉ።

የጋና ሴቶች የወር አበባ በሚያዩበት ወቅት ወደ ትምህርት ቤት ሲሄዱ እንዳይሻገሩት የሚከለከል 'ኢፊን' የሚባል ወንዝ አለ። ለምን ቢባል በወር አበባ ጊዜ ሴቷ ስለ ምትረክስ ወንዙ ላይ የሚመለኩ አማልክትን ታረክሳለች ተብሎ ስለ ሚታመን ነው መልሱ።

የኢትዮጵያ ገጠር አካባቢዎችም ሴቶች የተለያዩ ችግሮች ይገጥሟቸዋል። ዩኒሴፍ እንደሚለው 75 በመቶ ሴቶች በቂ የንጽህና መጠበቂያ አያገኙም፤ 50 በመቶ የሚሆኑትን ደግሞ በዚህ ምክንያት ከትምህርታቸው ይቀራሉ።

የግል ሕይወትን ተሞክሮለማህበረሰብ ለውጥ

በዚህ ችግር አንድም ሴት ከትምህርት ገበታ መቅረት የለባትም የሚል አቋም ያላት ፍረወይኒ መብራህቱ "የወር አበባ በየወሩ የሚመጣ ስለሆነ ይህ ችግር ለመፍታት ማድረግ ስላለብኝ አንድ ነገር በየወሩ የሚያስታውሰኝ ነገር ነበረኝ" ትላለች።

ወይዘሮ ፍረወይኒን በየወሩ የሚቀሰቅሳት ጉዳይ ለመጀመሪያ ጊዜ የወር አበባ ያየችበትን እድሜ ስታስታውስ ነው። "የትኛዋ ሴት ናት ለመጀመርያ ጊዜ የወር አበባ ስላየችበት ቀን ሳትሸማቀቅ የምታወራ?" በማለትም ትጠይቃለች።።

"ኅብረተሰባችን ስለ ወር አበባ ያለው ግንዛቤ ዝቅተኛ በመሆኑ፣ ታላላቅ እህቶቼና ወላጆቼም የማያወሩት ጉዳይ ስለ ነበር፣ እኔም የወር አበባ ምን እንደሆነ ሳላውቅ ነው ያደግኩት" ስትል በልጅነቷ የነበረውን ሁኔታ መለስ ብላ ታስታውሳለች።

የወር አበባ ያየችበትን የመጀመሪያ ቀን በማስታወስም "የወር አበባዋን ያየች ሴት ባልጋለች ይባል ስለነበረ ጊዜው ደርሶ ቢመጣም፣ ምን ሆኜ ይሆን ይህ ነገር የተከሰተው ብዬ ነበር" ትላለች ወይዘሮ ፍረወይኒ።

ፍረወይኒ እድሜዋ በአርባዎቹ አካባቢ የሚገኝ ሲሆን በመቀሌ ከተማ ማርያም ሰባ የተሰኘ የሚታጠብ የሴቶች የንፅህና መጠበቂያን በማምረት ሥራ ላይ ተሰማርታለች።

በዚህ ሥራዋ ሲ ኤን ኤን "ጀግና ሴት" ብሎ የሰየማት ወይዘሮ ፍረወይኒ በአሜሪካ በኬሚካል ኢንጅነሪግ ዲግሪዋን ሰርታለች።

ፍረወይኒ ዘመናዊ የንጽህና መጠበቂያ ለመጀመሪያ ጊዜ ያየችው ለትምህርት በሄደችበት አሜሪካ እንደ ፈረንጆች አቆጣጠር በ1983 ነበር።

"ለትምህርት ወደ አሜሪካ እንደሄድኩ ታላቅ እህቴ መጀመርያ የወር አበባ ንጽህና መጠበቂያ (ሞዴስ) እንድገዛ ወደ ሱፐር ማርኬት ወሰደችኝ። ያኔ ነበር አገር ቤት ትቼያቸው የመጣሁት ሴቶችስ መች ይሆን ይሄንኑ አይነት አማራጭ የሚያገኙት የሚል ሀሳብ አእምሮዬ ላይ የቀረው" በማለት በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ ሴቶች የሚቀርብ የንፅህና መጠበቂያ በርካሽ ዋጋ ማቅረብ የሚል ሀሳብ የተጠነሰሰው አሜሪካ ሳሉ መሆኑን ያስረዳሉ።

በ1983 ዓ.ም የመንግሥት ለውጥን ተከትሎ ሁኔታዎች ተቀይረው እንደሆነ በማለት ወደ ሀገራቸው ቢመለሱም ልጅ ሆነው ነውር ሲባል ይሰሙትና ያዩት የነበረው ነገር አሁንም ጥዩፍ እንደሆነ፣ መገለል እንዳለ አስተዋሉ።

ሰዎች ስጠይቅ ይላሉ ወይዘሮ ፍረወይኒ "ለምንድነው ስለዚህ ጉዳይ የምትጠይቂኝ ይሉኝ ነበር" በማለት የወር አበባ አሁንም እንደ ነውር እንደሚቆጠር ያስረዳሉ።

ማንኛዋም ሴት የወር አበባ በምታይባቸው ቀናት የምታሳልፋቸው ጊዜያት ከባድ መሆናቸውን የሚጠቅሱት ፍረወይኒ "በገጠር አካባቢዎች ጉድጓድ ቆፍረን እንቀመጣለን አሉኝ። ያኔ የሚፈሰው ደም ልክ እንደተከፈተ የውሃ ቧንቧ መቆጣጠር የማይቻል መሆኑን ሳስብ ከእግር ጥፍሬ እስከ ራሴ መጥፎ ስሜት ነበር የተሰማኝ" ይላሉ።

በአቅም ማነስ ምክንያት በርካታ ሴቶች የወር አበባቸውን በሚያዩበት ወቅት አንሶላ ቀድደው፣ እራፊ ጨርቅ አጥበው ጸሐይ ላይ እያሰጡና እያደረቁ ነው የሚጠቀሙት።

ከዚህ በከፋ ደረጃ ግን በገጠሪቱ ኢትዮጵያ እስከ አሁን የሙታንታንና የወር አበባ ንጽህና መጠበቂያን ጥቅም የማያውቁ ሴቶች መኖራቸውን ይጠቅሳሉ። ይህንን የሴቶች ችግር ከእኛ ሴቶች ውጪ ተረድቶት መፍታት የሚችል ሰው የለም በማለትም ያስረዳሉ።

ለአለፉት 10 ዓመታት 'ማርያም ሰባ' ብላ በልጃቸው በሰየሙት ድርጀት ስም የሚታጠብ ሞዴስ በማምረት በዝቅተኛ ዋጋ በትግራይ እና አፋር ገጠር አካባቢዎች ለሚገኙ ሴቶች ያቀርባሉ።

ማርያም ሰባ የሴቶች ንፅህና መጠበቂያ ታጥቦ መልሶ አገልግሎት ላይ የሚውል ሲሆን ከ18 ወራት እስከ ሁለት ዓመት ማገልገል ይችላል።

በምቾትና ፈሳሽ በመያዝ አቅም አንዴ ጥቅም ላይ ውሎ ከሚወገደው የንጽህና መጠበቂያ የሚለየው ነገር እንደሌለ የሚናገሩት ወ/ሮ ፍሬወይኒ ግማሹ ጥሬ እቃ በአገር ውስጥ ከሚመረት ጨርቅና ጥጥ እንደሚጠቀሙ ይገልጻሉ።

ከንጽህና መጠበቂያ ጨርቁ ጋር ለንጽህና መጠበቂያው የሚሆን ሙታንታም አብሮ ይሰራል።

ተቋሙ ንጽህና መጠበቂያውን ማምረት ሲጀምር በዓመት 200 ሺህ ያመርት የነበረ ሲሆን አሁን ወደ አንድ ሚሊዮን ማሳደግ እንደቻለ ወ/ሮ ፍረወይኒ ይናገራሉ።

ውጣ ውረዶች

በ2014 የህክምና አገልግሎት ለመስጠት ከባለቤቱ ጋር ወደ መቀሌ ዩኒቨርሲቲ የመጣው ዶክተር ልዊስ ዎል የማርያም ሰባን ፋብሪካ ማገዝ እንዳለበት አምኖ ጓዙን ጠቅልሎ ወደ ኢትዮጵያ ለመምጣት ሰባት ወር ወስዶበታል።

ከዚህ በኋላ ግን "ዲግኒቲ ፔሬድ" የሚል ፕሮጀክት በመጀመር የድርጅቱን ምርቶች በመግዛት 150 ሺህ የሚደርሱ ሴቶች ተጠቃሚዎች እንዲሆኑና በወር አበባ ዙርያ ያሉ የተሳሳቱ አመለካከቶች ለመፍታት የሚረዳ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርቶችን እየሰጠ ይገኛል።

ድርጅቱ ሴቶችና ወንዶች ስለ ወር አበባ ማወቅ ያላቸው እውቀት ከፍ እንዲል ስልጠና የሚሰጥ ሲሆን በትግራይ ከ800 ሺ በላይ ሴቶች የዚህ ንጽህና መጠበቂያን እንዲያገኙ በማድረግ ትምህርታቸው ያቋረጡ ሴቶች ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመለሱ ማድረጋቸውን ይናገራሉ።

"ይህ መሰረታዊ ችግር ካልተፈታ ሴት ልጅ ልትደርስበት የሚገባ ቦታ መድረስ አትችልም" የሚሉት ወ/ሮ ፍረወይኒ ሥራውን ለመጀመር የባንኮችን ደጅ በጠኑበት ወቅት የገጠማቸውን ያስታውሳሉ።

ባንኮች ለማሳመን ሁለት ዓመት እንደወሰደባቸው የሚናገሩት ወ/ሮ ፍሬወይኒ "እኔ ደፍሬ ካልጀመርኩት የወር አበባ ለዘላለም የሚያሳፍር ነገር ሆኖ ይቀራል" በሚል ቆራጥነት በእቅዳቸው በመግፋት እንዳሳኩት ይገልጣሉ።

ማንም በልጁ አይጨክንም፤ ይህ ፕሮጀክት ለእኔ ልጄ ነበር። እስከ መጨረሻው መውሰድ አለብኝ ብዬ የሚገጥሙኝ ፈተናዎችን በጽናት ተወጥቻለሁ። "የሴት ልጅ ውበትዋ ደግሞ ጥንካሬዋ ነው" ይላሉ።

አክለውም የወር አበባን በሚመለከት ያለው ግንዛቤና አመለካከት ለመቀየር ግን አሁንም ትልቅ ሥራ የሚጠይቅ ጉዳይ ነው በማለት የችግሩን ግዝፈት ይናገራሉ።