የትራምፕ ደጋፊዎች የአሜሪካ - ሜክሲኮ ድንበር ግንብ መገንባት ጀመሩ

የግንባታው አካባቢ Image copyright Facebook, courtesy We Build the Wall
አጭር የምስል መግለጫ በአሜሪካና በሜክሲኮ ድንበር ግንብ መጀመሩን ቡድኑ አስታውቋል

የአሜሪካው ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ ደጋፊዎች አሜሪካ እና ሜክሲኮን ድንበር የሚለያየውን ግንብ ባገኙት የገንዘብ ድጋፍ መገንባት መጀመራቸውን አስታውቀዋል።

የአሜሪካ ወታደራዊ ተቋም የቀድሞ አባል ብሬን ኮልፋጅ በኒው ሜክሲኮ ግዛት የተጀመረውን ግንባታ የሚያሳይ ፎቶግራፍ አጋርተዋል።

ኮልፋጅ አክለውም የግንባታው መሠረት የያዙት ብረቶች የቆሙት በእርዳታ በተገኘ 22 ሚሊየን ዶላር ሲሆን ገንዘቡን በበይነመረብ አማካኝነት ባካሄዱት ዘመቻ እንደሰበሰቡት ተናግረዋል።

የትራምፕ አማካሪ፡ የግንቡ ውጥን ውድቅ ከተደረገ ሰነባብቷል

ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ ግንቡን ለመገንባት ያቀረቡትን ሃሳብ ምክር ቤቱ ውድቅ ካደረገባቸው በኋላ ገንዘብ የማሰባሰብ ሥራውን እንደጀመሩ ገልፀዋል።

ባለፈው እሁድ የቀድሞው የአየር ኃይል አባል ኮልፋግ አዲስ እየተገነባ ያለውን ግንብ ተንቀሳቃሽ ምስልና ፎቶግራፍ በትዊተር ገፃቸው ላይ ለቀውታል።

"ታሪክ ሰርተናል! በመጀመሪያው የተሰበሰበው ገንዘብ ዓለም አቀፉን ድንበር ለመገንባት ውሏል" ሲሉ ኮልፋግ በትዊተር ገፃቸው ላይ ደስታቸውን ገልፀዋል።

ግንቡ የሚሰራው 'ዊ ቢዩልድ ዘ ዎል ኢንክ' በተሰኘ ለትርፍ ባልተቋቋመው ድርጅታቸው ሲሆን ድርጅቱ የተመሰረተው ከገንዘብ ማሰባሰብ ዘመቻው በኋላ ነው።

የቀድሞ የዋይት ሃውስ ባለሥልጣን ስቴቭ ባነን የዚህ ድርጅት አማካሪ ቦርድ ኃላፊ ናቸው።

የቦርዱ ኃላፊ ባነን ለሲ ኤን ኤን እንደተናገሩት አዲስ እየተገነባ ያለው 21 ማይል ርዝመት ካላቸው ሁለት ግንቦች ጋር የሚያያዝ ነው ብለዋል።

የቀድሞ ካንሳስ ሃገረ ገዢ የነበሩትና በአሁኑ ሰዓት የድርጅቱ አማካሪ ክሪስ ኮባች በበኩላቸው ግንባታው 8 ሚሊየን ዶላር ገንዘብ እንደሚፈጅ ገልፀዋል።

ግንባታውን እያካሄዱ ያሉት ቡድኖች በሰሜን ዳኮታ ግዛት የዓሳ አምራቾች ተቀጥረው የሚሰሩ ተቋራጮች ሲሆኑ ፕሬዚደንት ትራምፕ ግንባታውን እንዲያካሂዱ አሳስበዋቸው ነበር።

ትራምፕ 'ብሔራዊ የአደጋ ጊዜ አዋጅ' ሊያውጁ ነው

ከትራምፕ ደጋፊዎች አንዱ የሆነው የ56 ዓመቱ ጄፍ አለን ግንቡ የተገነባው በሰን ላንድ ፓርክ በኒው ሜክሲኮ ግዛት ሲሆን ከሜክሲኮ ሲዩዳድ ጁዋሬዝ በተቃራኒው አቅጣጫ የሚገኝ ነው።

ጄፍ አለን እንዳለው ግማሽ ማይል የሚሆነው የግንቡ ክፍል በዚህ ሳምንት መጨረሻ ይጠናቀቃል።

"ግንቡን ራሳችን እንገነባዋለን፤ ይህ አውሮፓ አይደለም፤ ይህ አሜሪካ ነው፤ ድንበራችችንን ራሳችን እንጠብቃለን" ሲልም ለኤ ኤፍ ፒ ተናግሯል።

ይሁን እንጂ ይህንን የሚያደርጉት ስደተኞችን በመጥላት እንዳልሆነ በመናገር ሚስቱ ሜክሲኳዊት ስትሆን ሴት ልጁም የተወለደችው ሲዩዳድ ጁዋሬዝ ውስጥ መሆኑን ጠቅሷል።

ውሳኔው ላይ የደረሰው ዘረኛ ስለሆነ ሳይሆን ራሱንና አሜሪካን ለመጠበቅ ደህንነቱ የተረጋገጠ ድንበር እንዲኖራት ስለሚፈልግ እንደሆነም አክሏል።

"ሰዎች አገራቸውን ትተው ለመሰደድ ካሰቡም በቀጥታ በመሄድ ማመልከት ይችላሉ" ብሏል -ጄፍ አለን።

በመጨረሻም ግንባታውን እያካሄደ ያለው ድርጅት "ይህ ጅምር ነው፤ በአሜሪካ ደቡባዊ ክፍል ያለውን ድንበር መጠበቅ ዓላማችን ነው"ሲል አስታውቋል።

ባለፈው ሳምንት የአሜሪካ ፍርድ ቤት የትራምፕ አስተዳደር ግንቡን ለመስራት ያቀረበውን የገንዘብ ጥያቄ ውድቅ ማድረጉ የሚታወስ ነው።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ