በጋምቤላ ሁለት የባጃጅ አሽከርካሪዎች በታጣቂዎች ተገደሉ

ጋምቤላ Image copyright Google

በጋምቤላ ክልል ሁለት በባጃጅ ስራ የሚተዳደሩ ግለሰቦች ማንነታቸው ባልታወቁ ታጣቂዎች መገደላቸውን የክልሉ የፀጥታና አስተዳደር የመረጃ ባለሞያ የሆኑት አቶ አልቢኖ ዶክ ሊዩ ገልፀዋል።

ስማቸው እንዳይገለፅ የጠየቁ የአካባቢው ነዋሪ በበኩላቸው ማቾቹ ከጋምቤላ ከተማ 25 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኝ አቦል ወረዳ ላለፉት አምስት አመታት በባጃጅ ስራ ሲተዳደደሩ መቆየታቸውን ተናግረዋል።

"ኢትዮጵያ ውስጥ ትልቅ ተስፋና ስጋት አለ" ኦባንግ ሜቶ

በመቱ ዩኒቨርስቲ ብሔር ተኮር ውጥረት ነግሷል

ግድያው የተፈጸመው ሟቾቹ እንደተለመደው ከስራ ወደ ከተማ ሲመለሱ መሆኑን ነዋሪው ገልፀዋል።

ግድያውን ተከትሎ በከተማዋ መጠነኛ ግርግር የተነሳ ሲሆን፤ የሟቾቹ አስከሬን በአካባቢው ወደ ሚገኘው ሆስፒታል ለምርመራ መወሰዱን ይኼው ግለሰብ ለቢቢሲ ገልፀዋል።

በባጃጅ ስራ የተሰማሩ የከተማዋ ነዋሪዎች ግድያውን በመቃወም አድማ አስነስተው የነበሩ ሲሆን ነዋሪው የድርጊቱ ፈጻሚዎች ማን እንደሆኑ እንዲጣራና ለህግ እንዲቀርቡ ጥያቄ ማቅረቡንም ገልፀዋል።

በምዕራብ ኦሮሚያ ስድስት ሰዎች መገደላቸው ተሰማ

" ሥራ ላይ እያሉ ነው የተገደሉት። ማን ይግደላቸው ማን ግን የሚታወቅ ነገር የለም። የአንደኛው ሬሣ ወደ መቀሌ የአንደኛውን ሬሣ ደግሞ ወደ ሽሬ ሄዷል። የፀጥታ ሰዎች ማጣሪያ እናደርጋለን ብለውናል። እኔ እስከማውቀው ድረስ የተወሰኑ የባጃጅ ሾፌሮች ሁኔታውን ተቃውመው አድማ መተው ነበር፤ አካባቢው በጣም አስቸጋሪ ነው" በማለት ነዋሪው አክሏል።

በግድያው የተሳተፉ ሰዎች እስከአሁን በቁጥጥር አለመዋላቸውን የገለጹት አቶ አልቢኖ ግድያው የተፈጸመው በጥይት እንደሆነና አስከሬናቸው ዛሬ ጧት ወደ ትግራይ መላኩን አረጋገጠዋል።

በአካባቢው ብዙ ችግሮች እንደሚከሰቱ የገለፁት ባለሙያው መንስኤውን ለማጣራት ምርመራ ላይ እንደሆኑም ተናግረዋል።

"ግድያው ብሔር ተኮር ነው ብሎ ለመደምደም ያስቸግራል፤ በአካባቢው በብዙ ጉዳዮች ግጭቶች ይነሳሉም" ብለዋል።