ፊቼ ጨምበላላ፦ የሲዳማ ሕዝብ አዲስ ዓመት

የፌቼ ጨምበላላ በዓል
አጭር የምስል መግለጫ የፌቼ ጨምበላላ በዓል

ገንዘብ ያበደረ እንዲመለስለት የማይጠይቅበት፣ ከብት የማይታረድበት፣ ዛፍ የማይቆረጥበት፣ ያጠፉ ይቅር የሚባሉበት ዕለት ነው- ጨምበላላ።

የሲዳማ ሕዝብ የጨረቃና ከዋክብትን አቀማመጥ በማጥናት አዲስ ዓመት ያከብራል። በዓሉም ፊቼ ጨምበላላ ይባላል። ይህ በዓል መከበር ከጀመረ ከ1800 ዓመታት በላይ ማስቆጠሩን የአገር ሽማግሌዎች ይናገራሉ።

ሜድ ኢን ቻይና- የሀገር ባህል አልባሳቶቻችን

የባህል አጥኚው አቶ ብርሃኑ ሃንካራ ደግሞ ''የፊቼ ጨምበላላ በዓል የሲዳማ ሕዝብ ማንነቱን ከተረዳበት ጊዜ አንስቶ ሲከበር የቆየ ነው'' ይላሉ።

የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና ባህል ተቋም (ዩኔስኮ) በቅርስነት የመዘገበው ይህ በዓል ዛሬ መከበር ጀምሯል።

ፊቼ ጨምበላላ በዓል የሚከበርበት ቋሚ ቀን የለውም። በአያንቱዎች ጥቆማ መሰረት በዓሉ የሚከበርበት ቀን ይቆረጣል። ከዚያም ለበዓሉ ሰፊ ዝግጅት ማድረግ ይጀመራል።

ከዋዜማው አንስቶ በዓሉ መከበር ይጀምራል። ጎረቤት ተሰብስቦም ከእንሰት የሚዘጋጀውን ቦርሻሜ ተብሎ የሚጠራውን ምግብ በወተት ይመገባሉ።

አጭር የምስል መግለጫ ያገቡ ሴቶች ልዩ የሆነ የጸጉር አሰራር አላቸው

ለበዓሉ ከሚበሉ ባህላዊ ምግቦችና ከሚከናወኑ ጭፈራዎች በተጨማሪ የተለያዩ ባህላዊ ሁነቶችም ይካሄዳሉ። ቄጠላ፣ ኛፋሮና የመሳሰሉ ሙዚቃዎችም በበዓሉ ይከወናሉ።

ጤፏን ለማስመለስ እየተውተረተረች ያለችው ኢትዮጵያ

ቄጠላ በተባለው ባህላዊ ሙዚቃ፤ አገር፣ ዘመን፣ የአገር ሽማግሌዎችና ታዋቂ ግለሰቦች እየተወደሱ ይጨፈራል።

አጭር የምስል መግለጫ ቄጠላ የተሰኘው ባህላዊ ጭፈራ በቡድን ሲያዜሙ

''የፊቼ ጨምበላላ ዋነኛ ትርጉም ሰላም ነው'' የሚሉት አቶ ብርሃኑ ሃንካራ፤ አንድነትና ፍቅር የበዓሉ መለያ መሆናቸውን ይናገራሉ።

የተጣሉ ሰዎች በፊቼ ጨምበላላ በዓል ላይ ይታረቃሉ። ሃዘን ላይ የነበሩ ሰዎችም የሃዘን ልብሳቸውን ይቀይራሉ።

ወንዶች አዞ ለመምሰል ቆዳቸውን የሚበሱባት ሃገር

ፊቼ ጨምበላላ ዘንድሮ ያገባች ሴት ሙሽርነቷን ጨርሳ ከሌሎች ሴቶች ጋር የምትቀላቀልበት በዓል ነው።

በተለያዩ ምክንያቶች ከቀዬው ርቆ የነበረ ሰው ለፊቼ ጨምበላላ ወደቀዬው ይመለሳል።

አጭር የምስል መግለጫ በበዓሉ ወቅት ለአካባቢ እና ለእንስሳት ትልቅ ትኩረት ይሰጣል

ለዚህ በዓል ተብሎ እርድ አይፈጸምም፤ ስጋም አይበላም። ክብቶችን መምታትም ክልክል ነው። ላሞች ሳር የበዛበት መስክ ላይ ይሰማራሉ።

በሲዳማ ሕዝብ ዘንድ በፊቼ ጨምበላላ በዓል ወቅት ማረስ ነውር ነው። ለዚህም ምክንያቱ ደግሞ የፊቼ ጨምበላላ በዓል የሲዳማ ሕዝብ ብቻ ሳይሆን የተፈጥሮም ነው ተብሎ ስለሚታመን ነው።ፊቼ የአዲስ ዓመት በዓል ዋዜማ ሲሆን፤ ጨምበላላ ደግሞ የአዲስ ዓመት መጀመሪያው ቀን ነው።

አጭር የምስል መግለጫ የእድሜ ባለጸጎች ሁሉቃ ሲሠሩ

ሲዳማ ከአንድ ዓመት ወደሌላው የሚሸጋገርበት ሂደት ሁሉቃ ይባላል። ሁሉቃ ማለት ከሸምበቆና ከአርጥብ ቅጠል ተሠርቶ የሚቆም ነገር ነው።

የኦነግ ጦር መሪ በትግላችን እንቀጥላለን አለ

ሁሉቃ በቤተሰብና በማኅበረሰብ ደረጃ የሚሠራ ሲሆን፤ አዲስ ዓመት ሲገባ ሰዎችና ከብቶች ይተላለፉበታል። የሲዳማ ሕዝብ አዲስ ዓመትን ሲቀበሉ፤ ዓመቱ የብልጽግና እንዲሆንላቸው 'ፊቼ ጄጂ' ይላሉ።