ፊሊፒንስ 1500 ቶን ቆሻሻ ወደ ካናዳ ላከች

የታሸገው ቆሻሻ

ለብዙ ሳምንታት ከቆየ ዲፕሎማሲያዊ ፍጥጫ በኋላ ፊሊፒንስ 1500 ቶን ቆሻሻ ወደካናዳ መልሳ መላኳ ተሰምቷል። ፕሬዝዳንት ሮድሪጎ ዱቴርቴም ''ወደካናዳ ሄዳችሁ ይህንን ቆሻሻ ድፉት'' የሚል መልእክት አስተላለፈዋል።

የፊሊፒንስ መንግሥት እንደሚለው፤ በአውሮፓውያኑ 2014 መልሶ ጥቅም ላይ የሚውል ነው በተባለ የፕላስቲክ ክምር ስም ቆሻሻ ወደ ዋና ከተማዋ ማኒላ ተልኮ ነበር።

ካናዳ ቆሻሻውን ለማጓጓዝና ለማስወገድ የሚውለውን ሙሉ ወጪ እንደምትሸፍን አስታውቃለች።

ሜድ ኢን ቻይና- የሀገር ባህል አልባሳቶቻችን

ባህልን በኤሌክትሮኒክ ሙዚቃ የቀመመው ሮፍናን

ትናንት በ69 ኮንቴይነሮች የታሸገ ቆሻሻ በሰሜናዊ ማኒላ የምትገኘው ሳኒክ ቤይ ከተባለችው የወደብ ከተማ ተነስቶ ወደ ካናዳ ጉዞውን ጀምሯል።

የፊሊፒንስ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ጸሀፊ የሆኑት ቴዲ ሎክሲን በትዊተር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፤ ቆሻሻውን '' ቻው ቻው'' በማለት በፌዝ ተሰናብተውታል። ከዚህ በተጨማሪም ኮንቴይነሮቹ ሲጫኑ የሚያሳዩ ምስሎችና ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለተከታዮቻቸው አሳይተዋል።

1500 ቶን የሚመዝነው ቆሻሻ ቫንኩቨር ወደተባለች የካናዳ ከተማ እንደሚላክ የታወቀ ሲሆን፤ እዛ ከደረሰ በኋላም ቆሻሻን ወደኃይል በሚቀይር ፋብሪካ ውስጥ ጥቅም ላይ እንደሚውል ተገልጿል። ወደከተማዋ በመጪው ሰኔ ወር እንደሚገባ ታውቋል።

የካናዳ ፓርላማ ጸሃፊ ሾን ፍሬዘር በበኩላቸው ''ካናዳ ስለቆሻሻ አወጋገድ በዓለም አቀፍ ደረጃ የፈረመችውን ስምምነት ከመጠበቅ ወደኋላ አትልም። ለችግሩ በፍጥነት ምላሽ ሰጥተናል'' ብለዋል።

በደቡብ ምስራቅ እሲያ የሚገኙ አገራት ከአውሮፓውያን የተላኩላቸው የፕላስቲክ ተረፈ ምርቶችን "መልሳችሁ ውሰዱልን፤ እንድንቀበል የተደረግነው ተጭበርብረን ነው" ማለት ከጀመሩ ቆይተዋል።

ቻይና ለብዙ ዓመታት ያደጉ አገራትን ቆሻሻዎች ስትቀበል የነበረ ሲሆን፤ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ግን በቃኝ ማለቷን ተከትሎ አገራቱ ቆሻሻ መጣያ አጥተው ነበር።

በዚህ ምክንያት አማራጭ ያጡት በተለይ የአውሮፓ አገራት መልሶ ጥቅም ላይ የሚውል በማለት በብዙ ሺ ቶኖች የሚቆጠሩ በቆሻሻ የተሞሉ ኮንቴይነሮችን ወደተለያዩ አገራት መላክ ጀምረዋል።

የምግብ ምርጫዎ ስለማንነትዎ ይናገራል?

የራስ ተፈሪያን መኖሪያቸውን ከሻሸመኔ ወደ ሐረር ሊያደርጉ ነው

የፊሊፒንስ መንግሥት እንዳስታወቀው፤ "መልሰው ጥቅም ላይ የሚውሉ ፕላስቲኮች ናቸው" ተብለው በአውሮፓውያኑ 2014 የተላኩት ኮንቴይነሮች ሲከፈቱ የካናዳውያን የቤት ቆሻሻ ሆነው ተገኝቷል።

በ2016 የፊሊፒንስ ከፍተኛ ፍርድ ቤትም ቆሻሻው በአፋጣኝ ወደመጣበት እንዲመለስ ውሳኔ አስተላልፎ ነበር። ነገር ግን የካናዳ መንግሥት ባወጣው አዲስ ሕግ መሰረት ቆሻሻ ወደአገሪቱ አይገባም በማለት እንደማይቀበል አስታውቋል።

ፊሊፒንስ በያዝነው ወር አጋማሽ ላይ ለካናዳ አምባሳደር ጥሪ በማድረግ የመጨረሻ መልእክቷን ያስተላለፈች ሲሆን፤ በሳምንታት ጊዜ ውስጥም ኮንቴይነሮቹን የመመለስ ሥራው ተጀምሯል።