የወባ ትንኝን 99 በመቶ የሚገድል ፈንገስ ተገኘ

የወባ ትንኝ Image copyright Science Photo Library

በቅርቡ በተሰራ ትናት መሰረት የወባ አስተላላፊ ትንኞችን 99 በመቶ መግደል የሚችል ከሸረሪት መርዝ የሚሰራና ላብራቶሪ ውስጥ የሚያድግ የፈንገስ አይነት መገኘቱ ተገለጸ።

የቤተሙከራ ሥራዎቹ ቡርኪና ፋሶ ውስጥ የተከናወነ ሲሆን በ45 ቀናት ውስጥ ሁሉም በሚባል ደረጃ ትንኞቹ መሞታቸው ታውቋል።

ወባ አጥፊው ክትባት ሙከራ ላይ ሊውል ነው

ተመራማሪዎቹ እንደሚሉት ዋና አላማቸው የትንኝ ዝርያዎችን ማጥፋት ሳይሆን በዓለማችን ትልቁ ገዳይ በሽታ የሆነውን የወባ በሽታ ማስቆም ነው። ከ400 ሺህ በላይ ሰዎች በየዓመቱ በወባ በሽታ ምክንያት ህይወታቸው የሚያልፍ ሲሆን 219 ሚሊዮን ሰዎች ደግሞ በበሽታው ይያዛሉ።

ምርምሩን ቡርኪና ፋሶ ውስጥ ሲያከናውኑ የነበሩት የአሜሪካው ሜሪላንድ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች ትንኞቹን የሚገድለውን ፈንገስ 'ሜታሪዚየም ፒንግሼንስ' የሚል ስያሜ ሰጥተውታል።

''ከዚህ በኋላ የሚቀረው ፈንገሱን ላብራቶሪ ውስጥ በደንብ ማሳደግና ይበልጥ ውጤታማ ማድረግ ነው'' ብለዋል በምርምር ቡድኑ ውስጥ የሚሳተፉት ፕሮፌሰር ሬይመንድ ሌገር።

የቢጫ ወባ ካርድ በቦሌ ለሚወጡ ሁሉ ግዴታ ሊሆን ነው?

ከፈንገሱ ጋር ተቀላቅሎ ትንኞቹን ለመግደል የሚውለው የሸረሪት መርዝ አውስትራሊያ ከሚገኝ ሸረሪት የተገኘ ሲሆን ቡርኪና ፋሶ ውስጥ በምትገኝ 603 ስኩዌር ሜትር ላይ ባረፈች መንደር ውስጥ ነው ሙከራው የተደረገው።

መንደሯ በትልቅ መረብ ከተሸፈነች በኋላ በምርምር የተገኘው ፈንገስ በአካባቢው እንዲረጭና መረቡ ላይ እንዲቀር ተደርጓል። ሙከራው የተሰራባቸውና መረቡ ላይ ያረፉት 15ሺህ ትንኞች ደግሞ 99 በመቶ ሞተዋል።