በአማራ ክልል በአተት ሳቢያ የአምስት ሰዎች ሕይወት አለፈ

አቶ አሞኘ በላይ

በአጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት ሳቢያ የአምስት ሰዎች ሕይወት ማለፉን የአማራ ክልል የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

በሽታው ከሚያዝያ 18/ 2011 ዓ. ም ጀምሮ በሰሜን ጎንደር ዞን ጠለምት ወረዳ እንደተከሰተ የኢንስቲትዩቱ የቅድመ ማስጠንቀቂያ እና የኅብርተሰብ ጤና ስጋት ቅብብል ባለሙያ አቶ አሞኘ በላይ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

"እስካሁን በሦስት ወረዳዎች እነሱም በሰሜን ጎንደር ጠለምት እና በይዳ ወረዳዎች እንዲሁም በዋግህምራ ዞን ደግሞ አበርገሌ በሚባል ወረዳ በሽታው ስለመከሰቱ ሪፖርት ተደርጓል" ብለዋል።

አተት እና ኮሌራ ምን እና ምን ናቸው? በጤና ተቋምና ባለሙያዎች ቤት ለቤት እየሄዱ ባደረጉት ሪፖርት መሠረት፤ እስከትናንት ድረስ 190 ገደማ ሰዎች በአተት መያዛቸውን ባለሙያው ገልጸዋል። "በአተት ምክንያት በተቋም ደረጃ መሞታቸው የተረጋገጠው 5 ሰዎች ናቸው" ብለዋል።

አቶ አሞኘ እንደሚሉት፤ በሽታው የመቀነስ እዝማሚያ እያሳየ ቢሆንም በቁጥጥር ሥር ማዋል ግን አልተቻለም። "አሁን ባለው ሁኔታ ሰሜን ጎንደር ላይ ተቆጣጥረነዋል ማለት ይቻላል። እስከ ሁለት ሳምንት ድረስ ምንም አይነት ህመምተኛ ሪፖርት አልተደረገም" ይላሉ።

ሆኖም አበርገሌ ላይ አልፎ አልፎ ሪፖርት እንደሚደረግ ያስረዳሉ።

"ትናንት ሪፖርት አልነበረም። ቆሟል ማለት አይቻልም። አሁን ሥራዎች እየተሠሩ ነው። ነገር ግን ቆሟል ከእንግዲህም አይነሳም የምንልበት ሁኔታ የለም። ምክንያቱም ሰፊ ሥራ ይጠይቃል" ሲሉ አቶ አሞኘ ይገልጻሉ።

የተከሰተው አተት ነው ወይስ ኮሌራ? በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ፤ "አተት በተለያዩ ነገሮች ሊከሰት ይችላል። በባክቴሪያ፣ በቫይረስ፣ በፕሮቶዞዋ ወይም በምግብና ውሃ መመረዝ ሊከሰት ይችላል።

አተት ከሚያመጡት ውስጥ አንዱ ባክቴሪያ ሲሆን፤ ከባክቴሪያዎቹ ውስጥ ደግሞ አንዱ ኮሌራ ነው፤ ልዩነታቸው ይሄ ነው። አተት ሰፊ ነው። በብዙ ነገሮች ሊከሰት የሚችል ማንኛውም አጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት ማለት ሲሆን፤ ኮሌራ ማለት ግን አተትን ከሚያስከትሉ ባክቴሪያዎች አንዱና በወረርሽኝ መልክ ሲከሰት ነው" ብለዋል።

ጤና የራቀው የፈለገ ህይወት ሆስፒታልአተት በብዙ ነገሮች ሊከሰት ስለሚችል እያንዳንዱ ኮሌራ እየተባለ ሪፖርት በቢደረግ ስህተት ሊፈጠር እንደሚችልም ተናግረዋል።

አክለውም "ናሙና እየወሰዱ ከማረጋገጥ ጎን ለጎን፤ ማንኛውንም ምልክት የሚያሳይ ሰው አተት በሚል መረጃውን እየተቀባበልን የመከላከልና መቆጣጠር ሥራ እንሠራለን" ብለዋል።

ማንኛውም አጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት ያለበት ሰው በፍጥነት በአቅራቢያው ወደሚገኝ የጤና ተቋም መሄድ እንዳለበት አቶ አሞኘ አሳስበዋል።

አሁን የተከሰተውን ችግር ለመከላከል ባለሙያዎችና የህክምና ቁሳቁሶችን ወደቦታው በመላክ ከአጋር ተቋማት ጋር እየሠሩ መሆኑንም ባለሙያው ገልጸዋል።