ትራምፕ ወደ እንግሊዝ ምን ይዘው ይሄዳሉ?

ፕሬዝዳንቱና ባለቤታቸው ባለፈው ዓመት እንግሊዝ ሲገቡ Image copyright Getty Images

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ወደ እንግሊዝ የሚያደርጉትን ይፋዊ የሥራ ጉብኝት በማስመልከት በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ፓውንድ ወጪ እየተደረገና ከፍተኛ የሆኑ የደህንነት ሥራዎችም እየተከናወኑ ነው።

በንግሥት ኤልሳቤጥ ጋባዥነት ከሰኞ ጀምሮ ለሦስት ቀናት ለሚደረገው የፕሬዝዳንቱ ጉብኝት፤ እስከ 18 ሚሊዮን ፓውንድ (666 ሚሊዮን ብር) ድረስ ወጪ ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል።

ዶናልድ ትራምፕ ተከሰሱ

የኋይት ሃውስ የደህንነት ሰዎች ወደ እንግሊዝ መግባት ጀምረዋል። ትራምፕን ተከትለው ወደ እንግሊዝ የሚሄዱት የደህንነት ቁሶችና የመጓጓዥ አይነቶች የትኞቹ ናቸው? ትራምፕን አጅበው የሚመጡትስ እነማን ናቸው?

ፕሬዝዳንቱ ወደ እንግሊዝ የሚሄዱት በልዩ ሁኔታ የተሠራውን 'ኤር ፎርስ ዋን' ተሳፍረው ነው። 'ኤር ፎርስ ዋን' በሰሜን ለንደን አቅጣጫ በሚገኘው ስታንስቴድ አየር ማረፊያ ያርፋል ተብሎ ይጠበቃል።

'ኤር ፎርስ ዋን' ተብለው የሚጠሩት ሁለት በልዩ ሁኔታ የተሠሩ ቦይንግ 747-200B አውሮፕላኖች ናቸው። ትራምፕ በእንግሊዝ በሚኖራቸው ጉብኝት ወቅት ሁለቱንም አውሮፕላኖች ጥቅም ላይ ሊያውሉ እንደሚችሉ ይገመታል።

ከኢትዮጵያና ከሌሎች የአፍሪካ ሃገራት ስለተዘረፉ ቅርሶች ምን እናውቃለን?

የአሜሪካ ዜና ወኪሎች ዘገባ እንደሚጠቁመው፤ ትራምፕ በእንግሊዝ ጉብኝታቸው ወቅት ያገቡ ልጆቻቸውን ከነመላው ቤተሰቦቻቸው ስለሚወስዱ ሁለተኛው 'ኤር ፎርስ ዋን' ያስፈልጋቸዋል።

ጥንቅቅ ያለው የ 'ኤር ፎርስ ዋን' አሠራርና አጨራረስ በጦር አውሮፕላን ዝርዝር ውስጥ እንዲካተት ያደርገዋል።

አውሮፕላኑ ከአየር ላይ ጥቃቶች ራሱን መከላከል ይችላል። የጠላት ራዳርን ማፈን ይችላል። የሚሳዔል ጥቃት ቢሰነዘርበት ፍንዳታ የማያስከትል ከፍተኛ ብርሃንና ሙቀት ያለው ጨረር በመልቀቅ የተቃጣውን የሚሳዔል ጥቃት አቅጣጫ ያስቀይራል።

'ኤር ፎርስ ዋን' አየር ላይ ሳለ ነዳጅ መሙላት ይችላል። ይህም ላልተወሰኑ ሰዓታት በረራውን እንዲቀጥል ያሰችለዋል። አውሮፕላኑ ላይ የተገጠሙት ሞባይል የመገናኛ ቁሳቁሶች ፕሬዝደንቱ በየትኛውም የዓለም ክፍል ላይ ትዕዛዝ እንዲሰጡ ያስችላቸዋል።

Image copyright Getty Images

የ 'ኤር ፎርስ ዋን' ተሳፋሪዎች 4,000 ካሬ ጫማ በሚሰፋው አውሮፕላን ውስጥ ዘና ማለት ይችላሉ።

አውሮፕላኑ ውስጥ ሦስት ወለሎች አሉ። እነዚህ ሦስት ወለሎች የፕሬዝዳንቱ ቅንጡ ማረፊያ፣ የህክምና አገልግሎት መስጫ፣ የስብሰባና የመመገቢያ ክፍል፣ ሁለት ኩሽና እንዲሁም የክብር እንግዶች፣ የመገናኛ ብዙሃን አባላት፣ የደህንነት ሰዎች እና የፕሬዝዳንቱ ረዳቶች መቀመጫ ስፍራዎችን ይዘዋል።

በርካታ እቃ ጫኝ አውሮፕላኖችም ከጉብኝቱ ቀን በፊት የፕሬዝዳንቱን መኪኖች፣ ሄሊኮፕተሮች እና ሌሎች ቁሶችን ያደርሳሉ።

እንደ ዋሽንግተን ፖስት ዘገባ ከሆነ ፕሬዝዳንቱ ሁሌም በሄዱበት የሚከተላቸው ''ፉትቦል'' ተብሎ የሚጠራ ቦርሳ አለ። ይህ ቦርሳ በውስጡ ኒውክለር ለመተኮስ የሚያስችል ማዘዣ እና የይለፍ ቃላትን እንደያዘ ይታመናል።

ፕሬዝዳንቱ የጦር ኃይሉ ጠቅላይ አዛዥ እንደመሆናቸው መጠን፤ የኒውክለር ጥቃት መፈጸም አስፈላጊ ሆኖ ቢገኝ በፍጥነት ትዕዛዙን ይሰጡ ዘንድ እንዲያመቻቸው ይህ ቦርሳ ሁሌም ከጎናቸው አይለይም።

ፕሬዝዳንቱ የሚንቀሳቀሱበት መኪኖችን ጨምሮ የሚያጅቧቸው ተሽከርካሪዎች በሙሉ ከእርሳቸው ቀድመው እንግሊዝ ይደርሳሉ።

ዶናልድ ትራምፕ የሚጓጓዙበት 'ዘ ቢስት' ተብለው የሚጠሩ ሁለት ተመሳሳይ ጥቁር ካዲላክ መኪኖች አሏቸው። ሁለቱም መኪኖች ተመሳሳይ የሆነ ዋሽንግተን ዲሲ 800-002 የሚል ታርጋ ቁጥር አላቸው።

የመኪኖቹ አካል እና መስታወት ጥይት የማይበሳው ሲሆን፤ አስለቃሽ ጭስ መልቀቅ የሚያስችል ስርዓት እና በምሽት ማየት የሚያስችል ካሜራ እንደተገጠመላቸው ይታመናል።

በመኪኖቹ ጎማ ላይ የተገጠመው ቸርኬ የመኪኖቹ ጎማ አየር ባይኖረው እንኳን እንዲሽከረከሩ ያስችላል። የነዳጅ ቋቶቹም የእሳት ጉዳት እንዳይደርስባቸው በእሳት መከላከያ ፎም ተሸፍነዋል።

እያንዳንዳቸው 7 ሰዎችን የመጫን አቅም ያላቸው መኪኖቹ፤ በውስጣቸው የህክምና ዕቃ አቅርቦቶች ተሟልቶላቸዋል። ኤን ቢ ሲ እንደሚለው ከሆነ አንድ ፍሪጅ ሙሉ የፕሬዝዳንቱ የደም አይነት በመኪኖቹ ውስጥ ይቀመጣል።

Image copyright EPA

ዶናልድ ትራምፕ በመኪና መንቀሳቀስ ሲጀምሩ በርካታ ተሽከርካሪዎች ያጅቧቸዋል።

ከሚያጅቧቸው መካከል ሞተረኛ ፖሊሶች፣ የደህንነት አባላት መኪኖች፣ የታጠቁ የደህንነት አባላትን የያዙ መኪኖች፣ የህክምና አገልግሎት ሰጪ ቡድን አባላትና ጋዜጠኞች ይገኙበታል።

ትራምፕ ተሽከርካሪዎችን ብቻ ሳይሆን ሄሊኮፍተሮችንም ይዘው ወደ እንግሊዝ ያቀናሉ። ፕሬዝደንቱን የምትጨነው ሄሊኮፍተር 'መሪን ዋን' ትሰኛለች። በዚህ ስም የሚጠራው ሂሊኮፍተር አንድ ብቻ ሳይሆን ሁለት ናቸው።

'መሪን ዋን' ሄሊኮፍተሮችም ሚሳዔል መቃወሚያ እና የግንኙነት ስርዓቶች የተገጠሙላቸው ናቸው።

ፕሬዝዳንቱን በሄሊኮፍተር ሲጓዙ 'መሪን ዋን' ጋር ተመሳሳይ ቅርጽ ያላቸው ሄሊኮፍተሮች ለደህንነት ሲባል አብረው እንዲበሩ ይደረጋል። በእነዚህ ተመሳሳይ አውሮፕላኖች ውስጥም ቢሆን የደህንነትና የህክምና ቡድን አባላት ይሳፈራሉ።

ከትራምፕ ጋር ወደ እንግሊዝ የሚሄዱ ሰዎች 1000 ያህል ሊሆኑ እንደሚችል ተገምቷል።

Image copyright Getty Images

የፕሬዝዳንቱ ጉብኝት የሚጀመረው በበርኪንግሃም ቤተ-መንግሥት በሚደረገው የእንኳን ደህን መጡ የምሳ ግብዣ ይሆናል።

ትራምፕ ከጠቅላይ ሚንስትር ቴሬዛ ሜይ ጋር በሴንት ጀምስ ቤተ-መንግሥት እና በ10 ዶውኒንግ ስትሪት ይወያያሉ።

የለንደን ከተማ ፖሊስ ጉብኝቱን በማስመልከት ''በርካታ ኤጀንሲዎች እና ከፍተኛ ልምድ ያካበቱ አባላት የሚሳተፉበት ኦፕሬሽን ይሆናል'' በማለት አስተያየቱን ሰጥቷል። የከተማዋ ፖሊስ ጨምሮም በፕሬዝዳንቱ ጉብኝት ወቅት ለንደን በርካታ ግዙፍ የተቃውሞ ሰልፎችን ልታስተናግድ አንደምትችል ይጠበቃል ብሏል።

ጸረ-ትራምፕ የሆኑ ቡድኖች የተቃውሞ ድምጻቸውን እንደሚያሰሙ ከወዲሁ አስታውቀዋል።