አሜሪካ የቪዛ አመልካቾችን የማህበራዊ ሚዲያ መረጃ እንደምትፈልግ አስታወቀች

በስልክ ላይ ያሉ የማህበራዊ ሚዲያ መተግበሪያዎች Image copyright PA
አጭር የምስል መግለጫ የቪዛ አመልካቾች የሚጠቀሙትን የማህበራዊ ሚዲያ ስም ማስገባት ይጠበቅባቸዋል

ወደ አሜሪካ ለመጓዝ ቪዛ የሚያመለክቱ ሁሉ የሚጠቀሙትን የማህበራዊ ሚዲያ ዝርዝር መረጃ መስጠት የሚያስገድድ አዲሱ ሕግ ወጣ።

ይህ የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ሕግ እንደሚለው ሁሉም ሰው የሚጠቀመውን የማህበራዊ ሚዲያ ስምና ላለፉት አምስት ዓመታት ሲጠቀምበት የነበረውን የኢሜይል አድራሻ እና የስልክ ቁጥር መስጠት ይጠበቅበታል።

እንግሊዝ አጭበርባሪ ባለሀብቶችን ቪዛ ልትከለክል ነው

የአይኤስ አባል የነበረችው አሜሪካ እንዳትገባ ተከለከለች

ሕጉ ባለፈው ዓመት ለውይይት ሲቀርብ በዓመት 14.7 ሚሊየን ሰዎች ላይ ተፅእኖ ሊያሳድር እንደሚችል ባለሥልጣናቱ ግምታቸውን አስቀምጠው ነበረ።

ይህ ሕግ በዲፕሎማሲያዊ መንገድና በመንግሥት ደረጃ ቪዛ የሚጠይቁ አመልካቾችን አይመለከታቸውም ተብሏል።

ነገር ግን ለትምህርትም ሆነ ለሥራ ወደ አሜሪካ ለመጓዝ ቪዛ የሚያመለከት ማንኛውም ሰው የተጠየቀውን መረጃ አሳልፎ መስጠት የግድ ነው።

"ሕጋዊ የሆኑ ሰዎች ወደ አሜሪካ እንዲገቡ ለማድረግ እና የአሜሪካ ዜጎችን ደህንነት ለማረጋገጥ የቪዛ አመልካቾችን አጣርተን የምንቀበልበት መላ ስናስስ ቆይተናል" ሲል ይህ አንደኛው መንገድ መሆኑን የውጪ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ አስታውቋል።

ቀደም ሲል ይህን መሰል ተጨማሪ መረጃ እንዲያቀርቡ ይገደዱ የነበሩት በሽብርተኛ ቡድኖች ቁጥጥር ሥር ከሚገኙ አገራት የሚመጡ እና ወደ እነዚህ ሃገራት የተጓዙ አመልካቾች ነበሩ።

አሜሪካ ሰሜን ኮሪያን ጨምሮ አዲስ የጉዞ ዕገዳ አወጣች

አሁን ግን ማንኛውም የቪዛ አመልካች የሚጠቀመውን የማህበራዊ ሚዲያ አካውንት እንዲሁም በሌሎች ድረ ገፅም ላይ ያላቸውን ዝርዝር መረጃ በፈቃደኝነት እንዲያሳውቁ ይጠየቃሉ።

ስለሚጠቀሙት ማህበራዊ ሚዲያ የሀሰት መረጃ የሚሰጡ ሰዎች ካሉም የማይወጡት ችግር ውስጥ ሊገቡ እንደሚችሉ ዘ ሂል ለተባለ ሚዲያ ባለሥልጣናቱ ተናግረዋል።

የዚህን ሕግ ሃሳብ ለመጀመሪያ ጊዜ ያቀረቡት ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ሲሆኑ ያቀረቡትም ባለፈው ዓመት ነበር።

በወቅቱ የአሜሪካ 'ሲቪል ሊበርቲስ ዩኒየን' የተሰኘ የሰብዓዊ መብት ቡድን እነዚህ ማህበራዊ ሚዲያዎች ውጤታማ ወይም ሚዛናዊ እንደሚሆኑ የሚያመላክት ምንም ማስረጃ የለም ሲሉ ተቃውመውት ነበር።

ፕሬዝደንት ትራምፕ በአውሮፓውያኑ 2016 የምርጫ ቅስቀሳ ዘመቻቸው በሥልጣን ዘመናቸው ትኩረት ሰጥተው ከሚሰሩበት አንዱ የስደተኞች ጉዳይ መሆኑን ማስታወቃቸው የሚታወስ ነው።

ፕሬዝደንቱ ባለፈው አርብም ሜክሲኮ በደቡባዊ የአሜሪካ ድንበር ተሻግረው የሚገቡ ስደተኞችን መቆጣጠር ካልቻለች አሜሪካ ቀስ በቀስ የንግድ ታሪፍ ጭማሪ እንደምታደርግ ፕሬዝዳንቱ አስጠንቅቀዋል።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ