በአዲስ አበባ የኮሌራ በሽታ ምልክት ታየ

Cholera Image copyright WHO

በአዲስ አበባ ከተማ የኮሌራ በሸታ ምልክት መታየቱን የጤና ጥበቃ ሚንስትሩ ዶ/ር አሚር አማን አስታወቁ።

የጤና ጥበቃ ሚንስትሩ እንዳሉት በአዲስ አበባ ከተማ በአጣዳፊ ተቅማጥ እና ትውከት ህመም ህክምና እያገኙ ካሉ አምስት ሰዎች መካከል የአንዱ በላብራቶሪ የኮሌራ በሽታ መሆኑ መረጋገጡን በትዊተር ገጻቸው አስታውቀዋል።

ዶ/ር አሚር የአጣዳፊ ተቅማጥ እና ትውከት ህመም በአዲስ አበባ፣ በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በትግራይ እና በሶማሌ ክልሎች በአጠቃላይ በ365 ሰዎች ላይ የታየ እንደሆነ እና ከእነዚህም መካከል 9 የሚሆኑት ሰዎች የተያዙት በኮሌራ በሽታ ስለመሆኑ በላቦራቶሪ ተረጋግጧል ብለዋል።

ሚንስትሩ በአጣዳፊ ተቅማጥ እና ትውከት እንዲሁም በኮሌራ በሽታ የተያዙ ሰዎች አፋጣኝ ህክምና እያገኙ እንደሆነ እና በሽታውን የመከላከል ሥራ ለማከናወን ከፍተኛ ዝግጅት እየተካሄደ እንደሆነ ጠቅሰዋል።

አተት እና ኮሌራ ምን እና ምን ናቸው?

በኢትዮጵያ የተፈናቃዮች ቁጥር ማሻቀብ የደቀነው ፈተና

አክለውም ለበሽታው በከፍተኛ ሁኔታ ተጋላጭ ለሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችም በቅርቡ የክትባት አገልግሎት የሚሰጥ ይሆናል ብለዋል። ማንኛውም ምልክቱ የታየባቸውን ሰዎች ወደ ጤና ተቋማት በፍጥነት መውሰድ እንዳለባቸው ሚንስትሩ አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩትም ትናንት ምሽት የኮሌራ ወረርሽኝ በአዲስ አበባ፣ በኦሮሚያ፣ በአማራ እና በትግራይ ክልሎች የመከሰቱን ይፋ አድርጓል።

ኢንስቲትዩቱ ወረርሽኙ በቀላሉ ሊዛመት እና ከፍተኛ ጉዳት ሊያስከትል ስለሚችል ሕዝቡ ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊያደርግ እንደሚገባ ገልጿል። በዚህም የመጸደጃ ቤት በአግባቡ መጠቀም፣ የመመገቢያ፣ የመጠጫ እና የውሃ ማስቀመጫ እቃዎችን በንጹህ ውሃ በማጠብ እና ከድኖ በማስቀመጥ ከዝንቦች እና ከበካይ ነገሮች መጠበቅ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አሳስቧል።

ለማንኛውም አገልግሎት የሚውልን ከቧንቧ፣ ከጉድጓድ፣ ከምንጭ፣ ከወንዝ እና ከመሳሰሉት የተቀዳ ውሃን በውሃ ማከሚያ መድሐኒቶች በማከም ወይም በማፍላት መጠቀም እንደሚገባ፤ ምግብን ከማዘጋጀት፣ ከማቅረብ እና ከመመገብ በፊት ከመጸዳጃ ቤት መልስ እና ሕጻናትን ካጸዳዱ በኋላ እጅን በሳሙና መታጠብ እንደሚገባም ኢንስቲቲዩቱ አስታውሷል።

በአተት ሳቢያ የአምስት ሰዎች ሕይወት አለፈ

ቢቢሲ ከሁለት ቀናት በፊት የአማራ ክልል የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ጠቅሶ በአጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት ሳቢያ የአምስት ሰዎች ሕይወት ማለፉን መዘገቡ ይታወሳል።

የኢንስቲትዩቱ የቅድመ ማስጠንቀቂያ እና የኅብርተሰብ ጤና ስጋት ቅብብል ባለሙያ አቶ አሞኘ በላይ እስከ ባለፈው ሃሙስ ድረስ 190 ገደማ ሰዎች በአተት መያዛቸውን ገልጸው፤ "በአተት ምክንያት በተቋም ደረጃ መሞታቸው የተረጋገጠው 5 ሰዎች ናቸው" ብለው ነበር።

የተከሰተው አተት ነው ወይስ ኮሌራ? በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ፤ "አተት በተለያዩ ነገሮች ሊከሰት ይችላል፤ በባክቴሪያ፣ በቫይረስ፣ በፕሮቶዞዋ ወይም በምግብና ውሃ መመረዝ ሊከሰት ይችላል።

አተትን ከሚያመጡት ውስጥ አንዱ ባክቴሪያ ሲሆን፤ ከባክቴሪያዎቹ ውስጥ ደግሞ አንዱ ኮሌራ ነው።

"አተት ግን በብዙ ምክንያቶች ሊከሰት የሚችል ማንኛውም አጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት ማለት ሲሆን፤ ኮሌራ ማለት አተትን ከሚያስከትሉ ባክቴሪያዎች አንዱና በወረርሽኝ መልክ ሲከሰት ነው" ሲሉ አብራርተዋል።

ኮሌራ አጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት በማስከትል በሰውነት ውስጥ የሚገኝን ፈሳሽ አሟጥጦ በማስወጣት አቅምን በማዳክም በአጭር ጊዜ ውስጥ ለሞት የሚዳርግ በሽታ ነው።

የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ እንደሚያሳየው ቪብሮ በተሰኘ ባክቴሪያ የተበከለ ውሃ እና ምግብ የኮሌራ በሽታን ያስከትላል። በየዓመቱ ከ1.3-4 ሚሊዮን ሰዎች በኮሌራ በሽታ እንደሚያዙ እና ከእነዚህም መካከል ከ21ሺ-143ሺ የሚያህሉት ህይወታቸውን እንደሚያጡ የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ ይጠቁማል።

ተያያዥ ርዕሶች