ቦይንግ 737 ማክስ 8፤ የቱሉ ፈራ ደጋግ ኢትዮጵያዊ ልቦች

በምስጋና መርሀ ግብሩ ላይ የተገኙ እንግዶችና ነዋሪዎች በከፊል Image copyright Netsanet tesfaye

መጋቢት 1/2011 ዓ.ም የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ቦይንግ 737 ማክስ 8 ማለዳ ወደ ናይሮቢ ጉዞውን ማድረግ ቢጀምርም ከስድስት ደቂቃ በላይ አየር ላይ መቆየት አልቻለም። ከ35 ሀገራት የተሰባሰቡ 157 ሰዎችን እንደጫነ እየተምዘገዘገ ጊምቢቹ ወረዳ ቱሉ ፈራ አካባቢ ወደቀ።

ከአደጋው አንድም ሰው አልተረፈም። በአደጋው ሁሉም ሰው እኩል አዘነ። ከሁሉም ግን የቱሉ ፈራ አካባቢ ነዋሪዎች ይለያል። በተለይ የእማማ ሙሉ። ከወጭ ወራጁ ጋር፣ ከኢትዮጵያዊው ኬኒያዊው ጋር ነጠላቸውን አዘቅዝቀው፣ እርጅና ያደከመው አይናቸው እንባ ያዘንባል።

ሁሌም ደረታቸውን እየደቁ፣ የእንባ ጅረት ፊታቸውን ያርሰዋል። የቢቢሲ ባልደረቦች የእኚህን እናት ደግ ልብ በቪዲዮም በጽሑፍም አስነበቡ። ማህበራዊ ሚዲያውም 'ኢትዮጵያዊነት በጠፋበት በዚህ ዘመን፣ አንዱ ሌላውን በሚያሳድድበት፣ አገር ከብጥብጥና ከመፈናቀል ዜና ውጪ በማትሰማበት ወቅት ኢትዮጵያዊ ደግ ልብ ተገኘ' ሲሉ ተቀባበሉት።

"አደጋውን ስሰማ በረራው ጠዋት እንዳልሆነ ራሴን አሳመንኩኝ" የረዳት አብራሪው ጓደኛ

ስለ አደጋው እስካሁን የምናውቀው

'መጥፎ ዕድል' አውሮፕላኑ የወደቀበት ስፍራ ስያሜ እንደሆነ ያውቃሉ?

አንድ የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚ የጊምቢቹ ወረዳ ቱሉ ፈራ አካባቢ እና የሀማ ቀበሌዎች ነዋሪዎችን ደግነት በማሰብ "ለምን አናመሰግናቸውም?" ሲል በፌስቡክ ገጹ መጠየቁን ያስታውሳሉ ኢንጂነር ስንታየሁ ደምሴ።

ኢንጂነር ስንታየሁ ደምሴ ትናንት በቱሉ ፈራ የተካሄደው የምስጋና ፕሮግራም አስተባባሪ ናቸው። ታዲያ እሳቸው ሀሳቡን ለሚቀርቧቸው እና ለማህበራዊ ድረ-ገፅ ተጠቃሚዎች አብራርተው በማካፈል 'ጎበዝ ኢትዮጵያዊ ደግ ልብ ተገኝቷል እስቲ አበጃችሁ እንበላቸው' አሉ።

ሀሳቡ ፋፍቶ በጎ ፈቃደኞችን አሰባሰበ። ስምንት አባላት ያሉት ኮሚቴ ተዋቅሮና ከአካባቢው ነዋሪ ጋር ምክክር ተደርጎ በትንትናው እለት አውሮፕላኑ በወደቀበት አካባቢ ለሚገኙ ነዋሪዎች የምሥጋና ፕሮግራም ተካሄደ።

Image copyright Netsanet Tesfaye

ምስጋናውን ለማድረስ ከአዲስ አበባ ሁለት አውቶቡስ ተንቀሳቅሷል። አንዱ የጋዜጠኞች ቡድንን የያዘ ነው። ሌላው ደግሞ አመስጋኝ አንደበትና ልባቸውን የያዙ ሰዎችን። አቅም ያለው የግል መኪናውን እያሽከረከረ ስፍራው ላይ ተገኝቷል ይላሉ የኮሚቴው አባል የሆኑት አቶ ነፃነት ተስፋዬ።

እንደው ለመሆኑ ከምናውቃቸው መካከል እነማን ተገኙ? ስንል የተለመደ ጥያቄ አከልን። ከሀገር ሽማግሌዎች ተባባሪ ፕርፌሰር አህመድ ዘካርያ እና አቶ ኃይሌ ገብሬ አሉ አቶ ነፃነት ተስፋዬ፣ ኢንጂነር ስንታየሁ አክለውም ሙሐዘ ጥበባት ዳንኤል ክብረት እና አርቲስት አብርሃም ወልዴም ምስጋና አቅራቢዎች ነበሩ አሉን።

አደጋው ስፍራ በየቀኑ እየሄዱ የሚያለቅሱት እናት ማን ናቸው?

"ምርኩዜን ነው ያጣሁት" የካፒቴን ያሬድ አባት

ኢንጂነሩ በማከልም ለህዝቡም ከፍ ያለ ግብዣ እና የማስታወሻ ስጦታ ተበርክቷል አሉን።

ስጦታው ምን ነበር?

የወ/ሮ ሙሉ ፎቶ

የእኚህ ደግ እናት ምስል ለቱሉ ፈራ አዲስ ስም፣ አዲስ መለያ ሸማ ሆኗታል። እናም ፎቶው ጥሩ ተደርጎ ተለብጦ አካባቢው ነዋሪዎች ለመጡበት የቀበሌ አስተዳደር ተሰጥቷል።

አቶ ደቻሳ ጉተማ በትናንትናው የምስጋና መርሀ ግብር ላይ ከታደሙ አባወራዎች መካከል አንዱ ናቸው። "እኛ ያለቀስነው ሟቾቹ ሰው በመሆናቸው" ነው ይላሉ። ሰው ሆነው፣ ለሰው ልጅ ሕይወት መጥፋት በማዘናቸው፣ በባህል በወጋቸው መሰረትም ተዝካር በማውጣታቸው ብቻ "ገለታ ይድረሳችሁ" መባላቸው ደንቋቸዋል።

'እንዳከበራችሁን ክበሩ' የእርሳቸው ምርቃት ነው።

ኢንጂነር ስንታየሁ "በጎ ነገር፣ ፍቅር ብርቅ በሆነበት፣ መተሳሰብ በጠፋበት በዚህ ዘመን የቱሉ ፈራ አካባቢ ሰዎችን ማግኘት መታደል ነው" ይላሉ።

ኢንጂነሩም አክለው እናቶቻችን ሁሉ እማማ ሙሉን ይመስላሉ። እሳቸውን ማመስገን ደግ እንዲበረክት፣ ደግነትም ነፍስ እንዲዘራ ማድረግ ነው ሲሉ አክለዋል።

የእማማ ሙሉን ደግነት ያየች አሜሪካ የምትኖር ኢትዮጵያዊት፣ ገነት በቀለ ትባላለች፣ ለእማማ ሙሉ ስጦታ መስጠት የምፈልገው ልክ ለእናቴ እንደማደርገው ነው በማለት ጃንጥላ፣ ሻርፕ፣ ቅባት ልካላቸዋለች።

እማማ ሙሉ በበኩላቸውም "እኔ ኢትዮጵያውያን በመንደራችን አደጋ ስለደረሰባቸው ወገኔ ተጎዳብኝ ብዬ አዘንኩ እንጂ እንዲህ ያለ ሽልማት አገኝበታለሁ ብዬ አይደለም። እናንተ ግን ይገባሻል ብላችሁ ሽልማት የላካችሁልኝን ፈጣሪ ዋጋችሁን አብዝቶ ይስጣችሁ። ይህንን ሁሉ ሽልማት ብቻዬን ምን አደርገዋለሁ? ሠፈር ስመለስ የአንገት ልብሱን ለጎረቤቶቼ አከፋፍለዋለሁ። ቅባቱንም ልጆቻችን አንድ ላይ ይቀቡታል" ማለታቸውን ሰምተናል።

Image copyright Netsanet tesfaye

ኢንጂነር ስንታየሁ እኛ ልናመሰግናቸው ስለሆነ የሄድነው ከኪሳችን ሳንቲም አዋጥተን ሁለት ሰንጋ አርደን ነበር። የአካባቢው ሰው ግን በአገልግል ፈትፍቶ፣ ቆሎ አዘጋጅቶ ጠበቀን በማለት ደጋግሞ ስለሚዘረጋውና ደግነት ስለማይነጥፍበት የቱሉ ፈራ አካባቢ ነዋሪ ይመሰክራሉ።

አቶ ነፃነት በበኩላቸው ይህ የምስጋና መርሀ ግብር የበጎ ፈቃደኞችን ኪስ ብቻ እንዲዳስስ ነው የፈለግነው ይላሉ። የየትኛውም ድርጅት ድጋፍን በዋናነት አልጠየቅንም። በርግጥ ውሃና ቢራ ያቀረቡ አሉ ሌላው ግን ሀሳቡን ከደገፉ አመስጋኝ ኢትዮጵያውያን የተሰበሰበ ብር ነው ይላሉ።

ኢንጂነር በበኩላቸው ከ100 ሺህ እስከ 150 ሺህ ሳናወጣ አልቀረንም ብለውናል።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ