በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ታጣቂዎች በተከፈተ ተኩስ 5 ሰዎች ተገደሉ

ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል Image copyright Facebook

በቤኒሻጉል ጉሙዝ ክልል ዳንጉር ወረዳ ታጣቂዎች በከፈቱት ተኩስ አምስት ሰዎች ተገደሉ።

ቅዳሜ ዕለት ዘጠኝ ሰዎች ቆታ ከምትባል ቀበሌ እቃ ጭነው ሲጓዙ ተኩስ ተከፍቶባቸው አምስቱ ወዲህ ህይወታቸው ሲያልፍ አራቱ ደግሞ መቁስላቸውን ስማቸውን እንዲጠቀስ የማይፈልጉ የአከባቢው ነዋሪ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ጥቃቱ ቀደም ሲል በአካባቢው አጋጥሞ በነበረው ግጭት ስጋት ያደረባቸው ሰዎች ንብረታቸውን በተሽከርካሪ ጭነው ከአካባቢው ለመውጣት በመጓዝ ላይ በነበሩበት ጊዜ ነው።

በካማሼ ዞን ግጭት እጃቸው አለበት የተባሉ በቁጥጥር ስር ዋሉ

ስለክስተቱ ቢቢሲ ያናገራቸው አንድ የዳንጉር ወረዳ ነዋሪ ''መንገድ በድንጋይ የዘጉ ታጣቂዎች ተኩስ ከፍተው አምስት ሰዎችን ገደሉ'' ሲሉ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።

የሟቾች አስክሬን እዚሁ ይቀበር ወይስ ወደ ትውልድ ቀያቸው ይላክ በሚለው ላይ በአከባቢው ነዋሪዎች እና መከላከያ መካከል አለመግባባት እንደተፈጠረም ለማወቅ ችላናል።

''ማምቡክ ከተማ 'በለስ ቁጥር ሁለት' በሚበላው ቦታ አስክሬን የት ይቀበር በሚለ በተፈጠረው አለመግባባት ነዋሪዎች መከላከያዎች ላይ ድንጋይ መወርወር ጀመሩ። ከዚያም መከላከያዎች በከፈቱት ተኩስ አራት ሰዎች ቆሰሉ'' ሲሉ ሌላው የማምቡክ ከተማ ነዋሪ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በቤኒሻንጉል ክልል ባለስልጣናት በቁጥጥር ስር ዋሉ

በግጭቱ የቆሰሉት ወደ መተከል ዞን ፓዌ ሆስፒታል መወሰዳቸው ታውቋል።

የአማራ መገናኛ ብዙሃን በበኔሻንጉል ጉሙዝ ክልል ግጭት ለማረጋጋት ያቀኑትን የአማራ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር የኢኮኖሚ አማካሪ አቶ አየነው በላይን ጠቅሶ እንደዘገበው ጥቃቱ የተሰነዘረው ግንቦት 24/2011 ምሽት 12:30 አካባቢ ሲሆን ንብረታቸውን ከቀያቸው ለማውጣት በመኪና በማጓጓዝ ላይ በነበሩ ወገኖች ላይ ለዘረፋ የተሰማሩ አካላት ጥቃቱን እንደፈጸሙ ተነግሯል።

ዘገባው አክሎም በጥቃቱ የአምስት ሰዎች ህይዎት ማለፉን እና አራት ሰዎች መቁሰላቸውን ዘግቧል።

ሕገወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር መበራከት ምንን ያመለክታል?

ትናንት ደግሞ አስከሬን ወደ ቤተሰብ ለመውሰድ በሚደረግ እንቅስቃሴ በነዋሪዎችና ማንቡክ በሚገኙ የመከላከያ ሠራዊት አባላት መካከል ግጭት ተፈጥሮ የአንድ ሰው ህይዎት ማለፉን፤ ሦስት ነዋሪዎች እና ስድስት የመከላከያ አባላት ጉዳት እንደደረሰባቸው የአማራ መገናኛ ብዙሃን ዘግቧል።

አንድ የማንዱር ወረዳ ነዋሪ በወረዳው ከፍተኛ የሆነ የደህንነት ስጋትና አለመረጋጋት እንዳለ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የቤንሻንጉል ጉሙዝ ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽፈህ ፈት ቤት ኃላፊ የሆኑት አቶ ገለታ ሃይሉ በበኩላቸው "ትናንት ዳንጉሩ ወረዳ ላይ ከዚህ ቀደም በተከሰተው ግጭት ቤተሰቡ ሙሉ ለሙሉ ተገድሎበት የነበረ አንድ ግለሰብ ከተወሰኑ ሰዎች ጋር በመሆን በአምስት ሰዎች ላይ ድርጊቱን ስለመፈጸሙ መረጃ ደርሶኛል" ብለዋል። "ግለሰቡ ቀደም ሲል አባወረኛ በሚባል ጎጥ ላይ ቤተሰቡ ተገድሎበት ነበር። በዚህም በበቀል ነው እነዚህ 5 ሰዎች መንገድ ላይ ጠብቆ ህይወታቸውን ያጠፋው" ሲሉ ገልጸዋል።

በአካባቢው የሠላም ኮንፈረንስ ከተካሄደ በኋላ ግጭት እንዴት ሊፈጠር ቻለ ተብለው የተጠየቁት አቶ ገለታ "ወይይቱ ለውጥ አላመጣም ማለት አይቻልም። ብዙሃን ማግኘት በሚችለው ደረጃ ውይይት ተካሂዷል። ወሳኝ አካላትና ተሰሚነት ያላቸው ሽማግሌዎችና የሃይማኖት መሪዎችን ባሳተፈ መልኩ ነው ውይይቱ እና ኮንፈረንሱ የተካሄደው።" "ከመረጃ ውጭ የሆኑ ግለሰቦች ሊሆኑ ይችላሉ ወይም ደግሞ ይህንን ሊፈጽም የቻለው ለበቀል የተንቀሳቀሰ አካል ስለሆነ እስከታች ላለው ማህበረሰብ የተወሰነ ሥራ ያስፈልጋል" ብለዋል። የዳንጉር ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ካሳሁን አምስት ሰዎች መገዳላቸውን እና ስድስት መቁሰላቸውን ለቢቢሲ አረጋግጠው፤ በወንጀሉ የተጠረጠሩ ሁለት ሰዎች መያዛቸውን እና ሌሎች ሁለት ሰዎች እየተፈለጉ መሆኑን ተናግረዋል።

"ሕይወቴን ብቻ ይዤ መውጣት ነው የምፈልገው"

የወረዳው አስተዳዳሪ በአከባቢው ይህን መሰል ገጭት መከሰት የጀመረው ሚያዝያ 17 በአሽከርካሪ እና በተሳፋሪዎች መካከል በተከሰተ አለመግባባት መሆኑን እና በዚህም በተለያዩ ጊዜያት ወደ 30 የሚጠጉ ሰዎች መገደላቸውን እና የደረሱበት ያልታቁ ሰዎች መኖራቸውን አስታውሰዋል።

በአካባቢው ቀደም ሲል ተከስቶ የነበረውን ግጭት ለመከላከል በቤኒሻንጉል እና አማራ ክልሎች አጎራባች ቦታዎች ላይ ኮማንድ ፖስት ተዋቅሮ ወደ ሥራ የተገባ ሲሆን ከግጭቱ ጋር በተያያዘ 8 አመራሮች እና ሌሎች 69 ግለሰቦች ተጠርጥረው መያዛቸውን ይታወሳል።