በአክሱም ዩኒቨርስቲ ግጭት አንድ ተማሪ ሲሞት በርካቶች ጉዳት ደርሶባቸዋል

አክሱም ዩኒቨርሲቲ Image copyright AKSUM UNIVERSITY

በአክሱም ዩኒቨርስቲ በተማሪዎች መካከል የተከሰተን ግጭት ተከትሎ አንድ ተማሪ ሲገደል አስር ተማሪዎች ደግሞ የመቁሰል ጉዳት ደረሰባቸው።

የአክሱም ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዚደንት ዶ/ር ኪሮስ ግዑሽ ከግንቦት 19/2011 ዓ.ም ጀምሮ በዩኒቨርሲቲው የብሄር መልክ ያለው ውጥረትና ድንጋይ መወራወር መኖሩን ያስታውሳሉ።

ውጥረቱ በደብረማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ከዚህ ቀደም በተፈጠረው ግጭት አንድ ተማሪ መሞቱ መነሻ ሳይሆን እንደማይቀር ጥርጣሬያቸውን ይናገራሉ።

ይሁን እንጂ ዩኒቨርሲቲው የፀጥታ ኃይሎችን በግቢው ውስጥ እንዲገቡ በማድረግ ለማረጋጋት የተለያዩ ጥረቶችን ሲያደርግ ቢቆይም "አልፎ አልፎ የብሔር መልክ ያላቸው ትንንሽ ትንኮሳዎች ነበሩ" ይላሉ።

ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የአክሱም ከፍተኛ ሆስፒታል ሰራተኛ አንድ ተማሪ እንደሞተ ለቢቢሲ አረጋግጠዋል። ባለሙያው ጨምረውም በርካታ ጉዳት የደረሰባቸው ተማሪዎች የህክምና አገልግሎት ለማግኘት ወደ ሆስፒታሉ መምጣታቸውንም ተናግረዋል።

በደብረማርቆስ ዩኒቨርስቲ በተቀሰቀሰ ረብሻ የአንድ ተማሪ ህይወት አለፈ

ዶ/ር ኪሮስ እንዳሉት ሁኔታው ተረጋግቶ ለተማሪዎች ፈተና መሰጠት መጀመሩን ሰኞ ዕለትም ማጠቃለያ ፈተና መውሰዳቸውን ተናግረዋል።

"ነገር ግን ትናንት የኢድ አል ፈጥር በዓል በመሆኑ ትምህርት አልነበረም" የሚሉት ዶክተር ኪሮስ፤ ቀን 4፡30 ገደማ የተወሰኑ ተማሪዎች ድንጋይ መወራወር ጀመሩ ይላሉ። ይህም ሰፋ ወዳለ ግጭት እንደተሻገረና በግጭቱም የአንድ ተማሪ ሕይወት ማለፉን ተናግረዋል።

ሕይወቱ ያለፈው ተማሪ ዮሐንስ ማስረሻ በዩኒቨርሲቲው የመካኒካል ኢንጂነሪንግ ሁለተኛ ዓመት ተማሪ ነበር።

"ፖሊስ ግጭቱን ለማረጋጋት ብሎ አስለቃሽ ጭስ የተኮሰ ሲሆን እርሱን ለመሸሽ ብለው አብዛኞቹ ተማሪዎች ከግቢው ወጥተው ነበር፤ ሟች ተማሪም ከግቢው ውጪ ወደ ቤተክርስቲያን መሄጃ መንገድ ሞቶ ነው የተገኘው። የተማሪውን አሟሟት ለማጣራት አስክሬኑን ወደ አዲስ አበበባ ቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ተልኳል" ብለዋል።

ዶ/ር ኪሮስ እንደሚሉት ሌሎች በግጭቱ ጉዳት ደርሶባቸው በሆስፒታል ተኝተው የሚታከሙ ሦስት ተማሪዎች ያሉ ሲሆን ሌላ ቀላል ጉዳት ያጋጠማቸው በርካታ ተማሪዎችም የመጀመሪያ ሕክምና እርዳታ ተደርጎላቸው ተመልሰዋል።

ጉዳት ያጋጠማቸው ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲውና በተለያዩ ጤና ጣቢያዎች ስለታከሙ ለጊዜው ትክክለኛ የቁጥር መረጃ እንደሌላቸው ገልፀዋል። ቁጥሩ በትክክል ሲታወቅም መግለጫ እንደሚሰጡ አክለዋል።

አስከ ጠዋት 2፡30 ድረስ በግጭቱ የተጠረጠሩ አራት ተማሪዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ከፖሊስ እንደሰሙ ነግረውናል፤ ከዚያም በኋላ በቁጥጥር ሥር የዋሉ ተማሪዎች እንዳሉም ሰምተዋል።

ግጭቱን ለማረጋጋት ዛሬ የአክሱም ከተማ የአገር ሽማግሌዎችና የኃይማኖት አባቶች ከተማሪዎች ጋር ውይይት የተደረጉ ሲሆን ተማሪዎችን የማረጋጋት ሥራ እየተሰራ መሆኑን አክለዋል።

ትናንት ማታ ጀምሮ የመከላከያ ኃይልና የፌደራል ፖሊስም በግቢው ውስጥ መሰማራታቸውንም ነግረውናል።

"አሁንም በስጋት ውስጥ ያሉና የተጨነቁ በርካታ ተማሪዎች ስላሉ ተማሪዎቹን ማረጋጋት ይቀረናል" ሲሉ ዶ/ር ኪሮስ ለቢቢሲ ገልፀዋል።

ዩኒቨርሲቲ ብሎ ለመጥራት የሚያስቸግሩ "ዩኒቨርሲቲዎች"

በዚህ ድርጊት ውስጥ ተሳትፈዋል የተባሉ ተማሪዎችን ፖሊስ በቁጥጥር ስር ለማዋል ጥረት ላይ መሆኑን የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ትናንት አመሻሽ ላይ ባወጣው መግለጫ የገለፀ ሲሆን በተማሪው ሞት ጥልቅ ሐዘን እንደተሰማውም አስታውቋል።

የክልሉ መንግሥት በመግለጫው ላይ ድርጊቱን አስነዋሪ ሲል የገለጸው ሲሆን፤ ግድያውን አጥብቆ እንደሚኮንነውና ፈጻሚዎቹን ወደ ህግ ለማቅረብ እየተደረገ ላለው ጥረት አስፈላጊውን ሁሉ እንደሚያደርግ አስታውቋል።

ግድያውን የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት አጥብቆ እንደሚያወግዝ ክልሉ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ለተማሪ ዮሐንስ ማስረሻ ሞት ምክንያት የሆኑ ወንጀለኞች በአስቸኳይ ተለይተው ለፍርድ እንዲቀርቡ ለማድረግ እና ወደፊትም ተመሳሳይ ችግሮች እንዳይከሰቱ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅርበት እየሰራው ነው ብሏል።

ተያያዥ ርዕሶች

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ