የኦሮምኛ ድምጻዊ ዳዲ ገላንን ገድሏል የተባለው የእድሜ ልክ እስራት ተፈረደበት

የኦሮምኛ ዘፋኙ ዳዲ ገላን
አጭር የምስል መግለጫ የኦሮምኛ ዘፋኙ ዳዲ ገላን

ድምጻዊ ዳዲ ገላንን ገድሏል የተባለው ተከሳሽ፣ ከተማ ረጋሳ፣ የእድሜ ልክ እስራት ተበየነበት።

የምስራቅ ሸዋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዛሬ ግንቦት 28 2011ዓ.ም በዋለው ችሎት ተከሳሽ ከተማ ረጋሳ ድምጻዊ ዳዲ ገላንን ለመግደል ሆነ ብሎና አቅዶ የካቲት 4 2011 ዓ.ም. ከምሽቱ 5፡30 ላይ በሊበን ጩቃላ ወረዳ በሽጉጥ ሁለት ግዜ ተኩሶ ደረቱን መትቶ መግደሉ ተረጋግጧል ብሏል።

ድምጻዊ ዳዲ ገላን በጥይት ተመትቶ የሞተ ዕለት አሟሟቱ ለደስታ በተተኮሰ ጥይት እንጂ ሆነ ተብሎ የተደረገ አይደለም የሚል እምነት ነበር።

በወቅቱ ቢቢሲ ያነጋገራቸው የድምጻዊው ጓደኛ እና የሊበን ጩቃላ ወረዳ ፖሊስ ፅፈት ቤት ኃላፊ ምክትል ኢንስፔክተር ግርማ ሚደቅሳ ድምጻዊው ለደስታ በተተኮስ ጥይት መገደሉን ገልጸው ነበር።

ኦሮምኛ ዘፋኙ ለደስታ በተተኮሰ ጥይት ህይወቱን አጣ

የኢትዮጵያ ተፈናቃዮች አይንና ጆሮ እንደተነፈጋቸው ተገለፀ

የአስክሬን የምረመራ ውጤት አርቲስቱ ሁለት ግዜ በሽጉጥ ጥይት ተመትቶ መገደሉን ያረጋገጠ ሲሆን አንድ ጥይት የሟች አስክሬን ውስጥ ተገኝቷል ተብሏል።

ፍርድ ቤቱ በተጨማሪም ከሟች አስክሬን ውስጥ የወጣው ጥይት አይነት ተከሳሽ ከሚይዘው ሽጉጥ የተተኮሰ መሆኑ ተረጋግጧል ብሏል።ተከሳሹ ግድያውን አልፈጸምኩ ሲል ቢከራከርም የቀረበበትን ማስረጃ መከላከል ግን አልቻለም።

አቃቤ ሕግ በተከሳሹ ላይ የቅጣት ማክበጃ ሃሳብ የለኝም በማለት ፍርድ ቤቱ ውሳኔ እንዲያስተላልፍ ጠይቋል።

የተከሳሽ ጠበቃ በበኩላቸው ደንበኛቸው ከዚህ በፊት ተከስሰው እንደማያውቁ፣ የተመሩ ሰው አለመሆናቸውን፣ የጦር መሳሪያ አጠቃቀም ላይ ያላቸው ግንዛቤ አነስተኛ መሆኑን እንዲሁም የበርካታ ቤተሰብ አስተዳዳሪ መሆናቸውን በመጥቀስ ቅጣቱ እንዲቀንስ ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል።

ተከሳሹም አቅመ ደካማ የሆኑ ሰዎችን ጨምሮ 9 የቤተሰብ አባላት አስተዳዳሪ መሆናቸውን በመጥቀስ ፍርድ ቤቱ ቅጣቱን እንዲቀንስላቸው ተማጽነዋል።

የግራ ቀኙን ክርክር ያደመጠው የምስራቅ ሸዋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ተከሳሸ ከተማ ረጋሳ ድምጻዊ ዳዲ ገላንን መግደሉ በመረጋገጡ የእድሜ ልክ ጽኑ እስራት በይኖበታል።

ድምጻዊ ዳዲ ገላን ፓለቲካዊ ይዘት ያላቸውን የኦሮምኛ ሙዚቃዎችን በመጫወት የሚታወቅ ሲሆን በዘፈኖቹ በተደጋጋሚ ለእስር ተዳርጎ ነበር።

ተያያዥ ርዕሶች